Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በግንቦት ሃያ ቱርፋቶች የሰመዓታት ዓጽም ይለመልማል!

0 894

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በግንቦት ሃያ ቱርፋቶች የሰመዓታት ዓጽም ይለመልማል!  

ወንድይራድ  ኃብተየስ  

የህግ የበላይነት የሰላም መሰረት ነው።  ለህግ የበላይነት መከበር መሰረቱ ህገመንግስታችን ነው። የአገራችንን ህገመንግስት በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይሁንታ የጸደቀ ሰነድ ነው። በመሆኑም በአገራችን የሚከናወኑ ማንኛውም  ነገር  መሰረቱ ህገመንግስቱ መሆን ይኖርበታል።  ይህን ህገመንግስት የጸደቀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መክረንበትና ዘክረንበት ነው።  አገራችን የምትመራበትንና የምትተዳደርበትን ዋስትና ካጸደቅን ብኋላ  ማስፈጸሙ የሁሉም ግዴታ ነው።  አንድ የፈረንጅ አባባል ትዝ ይለኛል።  “ተስማምተህ አስምር  ከዚያም መስመሩን በጋራ ተከላከል”። አዎ ህገመንግስታችን የሁላችንም የቃልኪዳን ሰነድ ነው። ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለሚገጥማቸው መልካምም ይሁን መጥፎ ነገሮች በጋራ ለመወጣት  የመተማመኛ  ሰነዳቸው በመሆኑ ይህን ቃል መጠበቅም ሆነ ማስጠበቅ የሁሉም ግዴታ ነው።

ህገመንግስታችን የግንቦት 20 ድል ውጤት ነው። በርካቶች ለዚህ ድል ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ለእነዚያ   ቁርጠኛ  የህዝብ ልጆች  ግንቦት 20  መታሰቢያቸው መዘከሪያቸው መሆን ይገባወዋል። በአሁኑ ሰዓት እያየን ያለነው ግለኝነት እጅግ አሳፋሪ ነው።  ሁሉም የግል ጥቅሙን ለማሳካት ሲዳክር፣ የተቀመጠባትን ወንበር ለጥቅም ማሳደጃነት ሲጠቀምባት ለተመለከተው  ኢትዮጵያዊ ስብዕና ምን ያህል እንደተሸረሸረ ያሳያል።  እነዚያ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ግን  መተኪያ የሌላትን ክቡር ህይወታቸውንና አካላቸውን  ለህዝብ ጥቅም ሲሉ  በየዱር ገደሉ  ገብረዋል።  በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ጥቅም ፈላጊዎች  እንኳን ህይወትና አካላቸውን ለህዝብ ሊሰጡ ይቅርና  የዕለት ጥቅማቸውን እንኳን አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። የግንቦት ሃያ ስኬቶቻችን መሰረቱ  እነዚያ የቁርጥ ቀን የህዝብ ልጆች መሆናቸውን ማሰብ ተገቢ ነው።   

ለአገራችን አንድነት ስጋት እንደሆኑ በሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የሚታሰቡት ትምክህትና ጥበት ናቸው። ለእነዚህ ሁለት ሃይሎች መሸሸጊያ ዋሻ የሚሆነው ደግሞ ቃሉን ባልወደውም “ኪራይ ሰብሳቢነት”  ነው።  ኪራይ ሰብሳቢነት ለአገራችን ቀጣይ ህይወት አደጋ  ነው። አንድ ሀሳብ ወይም ተግባር በበቂ ምክንያት ካልተደገፈ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡  በትምክህተኛው ሃይል ከሚራገቡት አስተሳሰቦች ጥቂቶቹ  የፌዴራል ስርዓታችንን የጎሳ ፖለቲካ ነው፣ የግዛት አንድነትን አደጋ ላይ ጥሏል፣ አንድ አገር አንድ ህዝብ፣ አንድ  ቋንቋ  ወዘተ የሚሉት እጅግ ጊዜ ያለፈባቸው አካሄዶችን ሲያራምዱ  ይታያሉ።  የጥበት ሃይሉ ደግሞ በሌላ ጽንፍ ቆሞ ባለፉት ስርዓቶች እሱና እርሱ ብቻ በደል እንደደረሰባቸው በማስመሰል ሁሉም ነገር የእኔና  ለእኔ ብቻ፣ ሌላውን ግደለው፣ ዝረፈው፣ አባረው፣ ወዘተ የሚል የዘመነ ግሎባላይዜሽን እሳቤ ያልገባው አካሄድን ሲያራምድ ይታያል። እነዚህ ሃይሎች ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠንቅ ናቸው።  በመሆኑም አገራችን  ያላትን  እጅግ ዘመናዊ ቀመርን ያሰፈረውን የህዝቦች አብሮነት  ያረጋገጠውንና የአገሪቱን አንድነት ያስከበረውን ህገመንግስታችንን  ከትምክህትና ጠበብ ሃይል መጠበቅ  ይኖርብናል።   

 

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የዜጎች ሰባዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሠረት ጥሏል።  የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ገና ከመግቢያው ጀምሮ ሕዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ማኅበረሰብ እንዲፈጥሩ፣ በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን  የሚያደርጉ አንቀጾችን ያሰፈረ ሰነድ ነው። ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። በህገ-መንግስታችን የጸደቀው የፌዴራል ስርዓታችን ውጤታማ የሆነው በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን በመደረጉ ነው። የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ዜጎች በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ ወዘተ አድርጓል።

 

ሕገ-መንግሥቱ በፌዴራሉ ሥርዓት ውስጥ በሕዝቦች መካከል ስለሚኖር ዝምድና እና የጋራ መስተጋብር መሠረታዊ መርሆዎችን ያስቀምጣል። የፌዴራሉን ሥርዓት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችሉ የሥልጣን ክፍፍል ቁልፍ መርሆዎችንም የቀመረ በመሆኑ በክልሎችም መካከል ሆነ በፌዴራሉ መንግስት ጋራ ያለውን ግንኙነት በደንብ አስቀምጦታል። የፌዴራል ስርዓቱ  ህዝቦች አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ሁኔታዎችን ስላመቻቸ  ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል  እንዲኖር አግዟል።  ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት መሰረተ ለማት  ያልነበራቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች ዛሬ ላይ የትላልቅ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። መንገድ፣ መበራት፣ ውኃ፣ ቴሌኮም ወዘተ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።  ይህ በመሆኑም ዛሬ ከቀድሞ ጊዜ በተለየ መልኩ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ኢንቨስትመንቶች በመስፋፋት ላይ ናቸው።  እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ  የትምክህትና የጥበት ሃይሉ  ህዝቦችን ሊያቃቅር አገራችንን ሊበትን የሚችሉ  የሃሰት መረጃዎች በማህበራዊ ድረገጾቻቸው በማራገብ ላይ ናቸው። ይሁንና  የእነዚህ ሃይሎች የጥፋት አካሄድ ስለተነቃባቸው  ሰሚ ጆሮ አላገኙም። በቀጣይም ከዚህ ድርጊታው እንዲታቀቡ በቃችሁ ልንላቸው ይገባል።

 

ከዚህ ባሻገር ሕገ-መንግሥቱ ሁሉም ዜጎች የሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በእኩልነት መከበር እንዳለባቸው በግልጽ የሚደነግጉ አንቀጾችን አካቷል።  ዛሬ በአገራችን በፖለቲካዊ አስተሳሰብ መደራጀትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተለመደ ተግባር መሆን የቻለው ይህ መብት ህገመንግስታዊ ዋስትና ስላገኘ ነው። አገራችን የብዙሃን ፓርቲ ስርዓትን  መተግበር  በመቻሏ  በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ።ዜጎች በነጻነት መንግስትንም ሆነ የመንግስትን አሰራር መተቸት የሚችሉበት ስርዓት ተዘርግቷል።  ሃሳብን የመግለፅ መብት በመረጋገጡ ማንም የፈለገውን ሃሳብ የሌሎችን መብት  እስካልተጋፋ ድረስ የመግለጽ መብትም በህገመንግስቱ ተረጋግጧል። ህገ-መንግስቱ የዜጎችን በህግ ፊት ያለምንም ልዩነት እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ደንግጓል። በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም በሰዎች መካከል ልዩነት እንደማይደረግና ሁሉም ሰዎች እኩል ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል።  ይህም ባለፉት 26  ዓመታት  በተግባር ተረጋግጧል።

 

በህገ-መንግስታችን የሃይማኖት ነጻነትንም  አጎናጽፎናል። ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት እየተስተናገዱበት ስርዓት ተመስርቷል። በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር  እውን ሆናለች። ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮታቸውን በነጻነት የሌሎችን መብቶች አክብረው ማስተማር ይችላሉ። ይሁንና የእኔን ሃይማኖት ከፍ ለማድረግ የሌላውን ዝቅ ማድረግ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ ነው።

በአገራችን የታየው ልማትና እድገትም ቢሆን የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አገራችን በታሪኳ አከናውናው የማታውቃቸውን እጅግ ግዙፍ የሆኑ ባለ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መገንባት ችላለች። ለአብነት ያህል ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎችና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም ሰፋፊ የመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታ ወዘተ አገልግሎት የታዩት ዕድገቶች እጅግ ከፍተኛ ከመሆናቸውም ባሻገር የአገራችንን ዕድገት ወደ ፊት በማራመድ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው። እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች መሰረታቸው ህገመንግስታችን ነው። ህገመንግስታችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረጉ ልማታችን ሊፋጠን ችሏል።

 

እንዲሁም ዜጎች መረጃዎችን የማግኘት መብታቸውም ሕግ-መንግሥታዊ እውቅና አግኝቷል። የምንግሥት ሚዲያም የተለያዩ አስተሳሰቦችን በሚያስተናግድበት መንገድ እንዲመራ ሕገ-መንግሥት ያዝዛል። ይህም በመገናኛ ብዙሃኖች ተግባራዊ ሆኗል። ይሁንና አንዳንድ በነጻው ፕሬስ ስም የተቋቋሙ ጋዜጦችና መጸሄቶች ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ያለአግባብ በመጠቀም አገርንና ህዝብን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ባለፉት ሥርዓቶች ይደረጉ የነበሩ የቅድመ ምርመራ እንቅስቃሴዎች በሕገ-መንግሥቱ አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደዋል። በመሆኑም ዛሬ በአገራችን ማንም በነጻነት ሃሳቡን የመግለጽ መብቱ ተጠብቆለታል። ይህ ማለት ቅድመ ሳንሱር በአገራችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተነስቷል።

የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብትም ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና አግኝቷል። የአገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ያልተገደበ መብታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኘው በዚህ ሕገ-መንግሥት አማካኝነት ነው። የሀገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በክልል እና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው እንደተከበረ ተደንግጓል።

በሌላ በኩል  ሕገ-መንግሥቱ ከፌዴራል ሥርዓቱ ለመውጣት የሚሹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚከተሉትን ሕጋዊ ሥርዓትም በግልፅ አስቀምጧል። ይህን ህጋዊ መስመር የሚከተል ማንኛውም መገንጠል የሚፈልግ አካል በህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት በአግባብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተቀምጧል። ህገመንግስታችን ይህን ያህል የዜጎችን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያስጠበቀ እጅግ ዘመናዊ አስተሳሰብን የያዘ ሰነድ ነው። ብሶት የወለዳቸው እውነተኛ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወትና የአካል መሰዋዓትነት የአገራችን ህዝቦች የሚያጣሟቸውን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጎናጽፈውናል። በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ትውልድ የሚያስፈልገው አገርን ከድህነትን ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ እንጂ ስለጦርነት፣ ሞትና ስደት መሆን የለበትም። ህይወታቸውንና አካላቸውን መስዋዕት አድርገው   ለዛሬዋ እኩልነትና ነጻነት ያበቁንን  ለእውነተኛ የህዝብ ልጆች ምስጋና ይግባቸው።    እኩልነትንና ነጻነትን ባሰብን  ጊዜ ሁሉ የእነዚያ  እውነተኛ የህዝብ ልጆች አጽም ይለመልማል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy