Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በግንቦት 20 ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል!

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በግንቦት 20 ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል!

ዳዊት ምትኩ

የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት በብዝሃነት ውስጥ ያለን አንድነት በማጣጣምና ነባራዊ ችግሮችን ወሳኝ በሆነ ሁኔታ በመፍታት አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ይገኛል። በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ባረቀቁት ህገ-መንግስት ላይ አንድ የጋራ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማህበረሰብን ለመገንባት በገቡት ቃል ኪዳን መሰረት ላለፉት 26 ዓመታት በመከባበርና በመቻቻል እንዲሁም አንደኛው የሌላኛውን ባህል፣ እምነትና ትውፊት በማክበር ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በዚህም እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረብና ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነቱን እያጠናከረ ይገኛል።

ታዲያ በዚህ ብዝሃነትን በሚያከብር ስርዓት ውስጥ የሚተገበር ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይበልጥ መጎልበት ይገባዋል። የዚህ ፅሑፍ ዓላማም በቅድሚያ በሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ የሚገኘው ፌዴራላዊ ስርዓት ብዝሃነትን እያስተናገደ ያለበትን ሁኔታ በመቃኘት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይበልጥ እንዲጎለብት የራሴን ዕይታ ማመላከት ነው።

ከፌዴራላዊ ስርዓቱ ቀደም ያሉ ስርዓቶችን የኋሊት ስንቃኛቸው ኢትዮጵያ በቅድመ ፌዴራል ሥርዓት ዘመን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሥር ቤት የነበረች ሀገር እንደነበረች የማንዘነጋው ዕውነታ ነው፡፡

ዛሬ ግን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በሕገ መንግሥቱ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ህገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ እንዲሆንም አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠል መብታቸው መጠበቁን፣ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት የተረጋገጠለት መሆኑ በህግ ተወስኗል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ማንነቶች ራሳቸውን የማልማትና በማያቋርጥ ሁኔታ ኑሯቸውን የማሻሻል መብት እንዳላቸው እንዲሁም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ በሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሀሳብ የመስጠት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ አናሳ ብሔረሰቦች ያለ ምርጫ በልዩ ሁኔታ የሚወከሉበት ከሃያ የማያንስ መቀመጫዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንዲኖራቸው ተደንግጓል። ይህም ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ አስችሏል፡፡

ይህ አሰራር አናሳ ብሔረሰቦች በቁጥር ተበልጠው ድምፃቸው ሳይሰማ እንዳይቀር ቦታ በመስጠት ፍላጎታቸው በሀገሪቱ ምክር ቤት እንዲንፀባረቅ የተሰጠ መብት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሴቶች ከኋላ ቀር አስተሳሰብ ጋር ተያይዞና ያለፉት ገዥዎች ይከተሉት በነበረ የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን አድልዎ በማስቀረት ከወንዶች ጋር እኩል እንዲሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡

ህገ መንግሥቱ ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የማንነቶችን የመኖር ዋስትና በተገቢው ሁኔታ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ታዲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመሬት ባለቤቶች እንዲሆኑ መደረጉ ህልውናቸው ከመሬት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ በህገ መንግሥቱ ለማንነቶች የተሰጠ ትርጉም እያንዳንዱ ማንነት የእኔ የሚለው መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈርና አካባቢ ያለው መሆኑን የሚያመላክት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ማንነቱን ማስጠበቅና ማክበር የሚችለው ግልፅ የሆነ አሠፋፈርና ቦታ ሲኖረው መሆኑ እሙን ነው፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት የተከናወነው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የማጎልበት ጥረት ምንም ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ውስብስብ የብሔር ጭቆናዎች አኳያ አስተሳሰቡን በቀላሉ ማስረፅ አስቸጋሪ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሀገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዩጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እርግጥ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ሊመጣ አይችልም። ተከብሮ እንጂ። ባለፉት 26 ዓመታትም ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ መነሻነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል፡፡ ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ነውና፡፡ እዚህ ላይ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምንነትን ማየት ይቻላል። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከትምክህትና ከጠባብ ኃይሎች ጋር ለሚደረግ ትግል ዓይነተኛ መሳሪያ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን የሚያረጋግጥ ነው።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው፡፡ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት 25 ዓመታት ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም አመለካከቱ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት ይቻላል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኘነትን ከአራት መሰረታዊ ትርጓሜዎቹ አኳያ ማየት ይቻላል። እነርሱም ማንነትን ማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ማወቅ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና አካባቢን ማልማት ናቸው። ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። እንደ አቶ ሕላዊ የሌሎችን ማንነት በማወቅ ረገድም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ያስፈልጋል። እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው። በመሆኑም አራቱን የፅንሰ ሃሳቡን ብያኔና አተገባበርን በአግባቡ በመገንዘብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ይበልጥ ገቢራዊ ማድረግ ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዕውን መሆንና ማበብ የታገለ ድርጅትና እንዲሁም እሳቤውን በመርህ በፅናት በማስፈፀም ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው። እርግጥ ብዙ ሕዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ ግንኙነት ጤናማ ባልሆነ አስተሳሰብ በሚመራበት ጊዜ ግጭት መከሰቱ አይቀርም። በኢትዮጵያ የተማከለ አስተዳደር ከተመሠረተበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በማኅበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተመላበት፣ ግጭት የጠነከረበት፣ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ሰላም ያጣችበት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

እርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ‘የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ፣ አትንኩን’ የማለት ነገር ይታያል፡፡ ይህንን አመለካከት መጠጊያ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ህገ መንግሥቱ አስተሳሰባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግም ሆነ መንግስት የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸውም ሰዎች ቢሆኑም ሃሳባቸውን ለምን ይገልጻሉ የሚል ብዥታ ኖሯቸው አያውቅም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል፡፡ እርግጥ ያለፈው ታሪክ አንድን ሕዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ፡፡ ይህ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ አንድ ብሔር የበላይ በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማጋጋም ትርፍ ለማግኘት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም። የሚፈልግ አካል ካለም ሊሳካለት አይችልም፡፡ ለምን? ከተባለ፤ እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ውጤት እያስገኘ ከመሆኑም በላይ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ላይ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ በመቀጠሉ ነው፡፡

እርግጥ አንዳንድ የትምክህት ኃይሎች ህብረተሰቡን በተሳሳተ ጎዳና ሊመሩት ይችላሉ። አስተሳሰቡ እነርሱ የሚያምኑበትን ‘ከሁሉም የበላይ ነን፣ ከእኛ ወዲያ ለአሳር’ የሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታ በመሆኑ ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ መንገድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ስርዓቱም ይሁን ህዝቡ የማይደግፈውን የዴሞክራሲ ፀር አስተሳሰብን ሁሉም በየደረጃው ሊታገለው የሚገባ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy