Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትምህርትን በማስፋፋት የተገኘው ውጤት በጥራቱም ይደገም

0 309

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትምህርትን በማስፋፋት የተገኘው ውጤት በጥራቱም ይደገም

ብ. ነጋሽ

በኢትዮጵያ ትምህርት ጥቂቶች ብቻ የሚያገኙት ልዩ ስጦታ ነበር፣ ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የሃገሪቱ ህዝብ በገጠር የሚኖር ሆኖ ሳለ ትምህርት ቤቶች ግን በከተሞች ብቻ ነበር የሚገኙት። በከተሞች የነበሩትም ቢሆኑ፣ አብዛኞቹ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች በአውራጃ ከተሞች ውስጥ ብቻ ነው የነበሩት፣ ከአርሶ አደሩ በእጅጉ ርቀው።

ይህ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች ልጆቻቸውን የማስተማር እድል እንዳያገኙ አድርጓል። በዘውዳዊው ስርአት ልጆቻቸውን የማስተማር እድል የነበራቸው ሃብት ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ባለርስት ባላባቶች ነበሩ። እነዚህ ባለርስት ባላባቶች ለልጆቻቸው ፈረስ ጭነው ከተማ እይተመላለሱ እንዲማሩ የማድረግ አቅም ነበራቸው። ቀለብ እየሰፈሩ ልጆቻቸው ከተማ ተቀምጠው እንዲማሩ የማድረግ አቅምም ነበራቸው። በዚህ ላይ ከገባር ጭሰኛ አርሶ አደር በተለየ ልጆቻቸው ኑሮን ለማሸነፍ በእረኝነትና መሰል ስራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያስገድዳቸው የኑሮ ሁኔታ ስለሌለ ባለርስቶቹ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ከዚህ በተረፈ በከተማ ዙሪያ ያሉ ወይም ከተማ ደጋፊ ዘመድ ያላቸው ምናልባት ጥቂት ልዩ እድል የነበራቸው አርሶ አደሮች ካልሆኑ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ልጆቻቸውን አያስተምሩም ነበር።

ከተማ ዙሪያ ያሉትም ቢሆኑ ከአንደኛ ደረጃ ያለፈ ልጆቻቸውን የማስተማር እድል አልነበራቸውም። እርግጥ በተወሰኑ የሃገሪቱ አካባቢዎች የአውሮፓ ሚሺነሪዎች ትምህርት ቤቶችን ያስፋፉበትና በወረዳ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበራቸው አካባቢዎች እንደነበሩ አይካድም። እነዚህ ሚሲዮኖች በሚንቀሳቁባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሩ ልጆች በአንጻራዊነት የተሻለ ትምህርት የማግኘት እድል ገጥሟቸዋል። ይህ ግን እጅግ ጥቂት ያሀገሪቱን አካባቢዎች የሚመከከት እውነት ነው።

በአውራጃ ከተሞች የሚኖሩና ጥቂት የቀናቸው የአርሶ አደር ልጆች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የማግኘት እድል ቢኖራቸውም ከዚያ ያለፈ ትምህርት ማግኘት ግን አይችሉም ነበር። በሃገሪቱ ያሉት የሙያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ከሁለትና ሶስት የሚበልጡ አልነበሩም።

በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን የነበረው ሁኔታም ከዚህ ብዙም የተለየ አልነበረም። እርግጥ ከዘውዳዊው ሥርአት በተሻለ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍተው እንደነበረ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። ከዚያ በላይ ያሉ የትምህርት እድሎች ግን በነበሩበት ነው የቀጠሉት ማለት ይቻላል። የሁለተኛ ደረጃም ሆነ የኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከቀደመው ሥርአት የተለየ አልነበረም። በወታደራዊው ደርግ ተሰሩ ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየአመቱ ከመቶና ሁለት መቶ ያልበለጠ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም የነበራቸው በ1977 ዓ/ም ስራ የጀመረው የጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በ1979 ዓ/ም ስራ የጀመረው የአርባ ምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ ደርግ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ30 ሚሊየን ወደ 45 ሚሊየን ጨምሮ ነበር። ቀድሞ ከነበረው የህዝብ ቁጥር ጋር የማይመጣጠነው የትምህርት ስርጭት ላይ 50 በመቶ ህዝብ ሲጨመርበት የሚፈጠረውን ሁኔታ መገመት አያዳግትም።

በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የነበሩት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 4 ሺህ ብቻ ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ደግሞ 2 መቶ 78 በቻ ነበር። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበሩ አጠቃላይ ተማሪዎች ቁጥር 2 ሚሊየን ገደማ ነበር።

ባለፉት ሃያ አስድስት ዓመታት በትምህርት ልማት ትልቅ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። በአሁኑ ጊዜ በመላ ሃገሪቱ ከ39 ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። የትምህርት ቤቶቹ ቁጥር ከወታደራዊ ስርአት ማብቂያ በኋላ ባሉት አመታት በአስር እጥፍ ነው ያደገው። አሁን በሃገሪቱ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ3 ሺህ 3 መቶ በላይ ናቸው። ይህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በወታደራዊ ደርግ ስርአት ማብቂያ ላይ ከነበረው ከአስር እጥፍ በላይ ጨምሯል። በአጠቃላይ በትምህር ቤቶች ውስጥ ያሉት ተማሪዎችም 27 ሚሊየን ደርሷል። በአሁኑ ጊዜ በመሰናዶ ትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ከግማሽ ሚሊየን በላይ ናቸው። በየአመቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥርም ከ1 መቶ 50 ሺህ በላይ ደርሷል።

የትምህርት ልማትን በተመለከተ ሌላው ድንቅ ስኬት የተመዘገበው በቴክኒክና ሞያ ማሰለጠኛ ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፈት ተግባር ነው። ከ1984 ዓ/ም በፊት በነበሩት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር እድል ያገኙ ከነበሩ ተማሪዎች የቴክኒክና ሞያ ንዲሁም ወደዩኒቨርሲቲዎች የመግባት እድል የነበራቸው እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። የተቀሩት ስርአቱ በየአቅጣጫው የተከፈተበትን የብሄራዊ ነጻነት የትጥቅ ትግል ለመከላከል ላወጀው ጦርነት በገፍ የሚፈለገውን የወታደራዊ ሃይል ወደሟማላት ነበር የሚሄዱት። ገሚሱ ውትድርና ይቀጠራል፤ መቀጠር የማይፈልገውም ቢሆን የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዲሰጥ በግዳጅ ይመለመላል።

በሞያና ቴክኒክ ስልጠና ዘርፍ፣ ከ1984 ዓ/ም በፊት በሃገሪቱ የነበሩ የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማት 16 ብቻ ነበሩ። እነዚህ በሃገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ብቻ የሚገኙ ተቋማት፣ ስልጠና የሚሰጡት በተወሰኑ የሞያ መስኮች ነበር። አሁን በሃገሪቱ የሚገኙ የሞያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ኮሌጆች 1350 ናቸው። ከእነዚህ የመንግስት ማሰልጠኛ ኮሌጆች ባተጨማሪ በተለያየ ደረጃ ስልጠና የሚሰጡ በርካታ የግል የቴክኒክና የሞያ ኮሌጆች አሉ። በአሁኑ ጊዜ የሞያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሌለበት አካባቢ የለም። ይህ የስልጠና ዘርፍ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ባለው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደኢንደስትሪ መር በማሸጋገር መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ሂደት፣ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማቅረብ አኳያ የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በተለይ በአነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንደስትሪ አንቀሳቃሽ ወጣቶችን በመፍጠር ረገድ የማይተካ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

ከ1984 ዓ/ም ወዲህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን – ኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ከ1984 ዓ/ም በፊት በሃገሪቱ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች አስመራ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ 3 ብቻ ነበሩ። አሁን የሲቪል ሰርቪስ፣ የፖሊስና የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ 36 ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ወደስራ የሚገቡ 11 ዩኒቨርሲቲዎች በመገንባት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ በመላ ሃገሪቱ ኮሌጆች ያላቸው የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ይገኛሉ። በአጠቃላይ በእነዚህ የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የገኛሉ።

ትምህርት በመላ ሃገሪቱ በማስፋፋት ረገድ ስኬታማ ውጤት ማስመዝገብ ቢቻልም፣ አብቅቷል ማለት አይደለም። በተለይ በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ላይ አሁንም ክፍተት ይታያል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት አሁንም ከ50 በመቶ አልዘለለም። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የቅበላ አቅም፣ ተደራሽነቱ ከ90 በመቶ በላይ ከደረሰው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጋር ተቀራራቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ አንደኛ ደረጃን ሳይሻገሩ የሚቀሩ በርካታ ዜጎች ይኖራሉ። ወደሞያና ቴክኒክ ተቋማት የሚዘልቁ ወጣቶች ቁጥርንም ይገድባል።

ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የትምህርት ጥራት ነው። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 4ኛ ክፍል ደርሰው ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነበት ሁኔታ ይታያል። 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከ1ኛ ደረጃ ተማሪ የተለየ ብቃት የማይታይባቸው ተማሪዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም። የሞያና ቴክኒክ ስልጠና ወስደው በሰለጠኑበት ሞያ ራሳቸውን ችለው መስራት የማይችሉ፣ በልምድ ከሚሰሩ ሰዎች በእጅጉ ያነሰ ችሎታ ያላቸውን “ሞያተኞች” መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። 2ኛ ዲግሪን ጭምር ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ከሚወጡ ተማሪዎች መሃከል በርካቶቹ ሰርተፊኬት ከመያዛቸው የተለየ የልሂቃኑን ጎራ ለመቀላቀል እጅግ ብዙ የሚቀራቸው የመሆናቸውም ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመሆኑም ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ለትምህርት መስፋፋት የተሰጠው ትኩረትና የተገኘው ውጤት በጥራቱም ላይ መደገም አለበት።     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy