ቻይና ለታዳጊ አገሮችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስምንት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንት ዢ ጃንፒንግ ቃል ገቡ።
ድጋፉ የሚደረገው አገሮችን በመሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር በነደፈችው የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ልዩ መርሃ ግብር መሰረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የ29 አገራት መሪዎች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ ላይ ፕሬዝዳንቱ የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” ዝርዝር እቅድን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው ቃል የገቡት።
ፕሬዝዳንቱ እኤአ በ2014 የታዳጊ አገሮች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ለተመሰረተው የ”ሲልክ ሮድ ፈንድ” 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ያስታወቁት።
በተጨማሪ ቻይና በ”ቤልት” ስር ባሉ አገሮች መካከል ትብብሩን ለማጠናከርና ፈጠራን ለማነቃቃት ሃምሳ ላብራቶሪዎችን በጋራ እንደምታቋቁም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ጃንፒንግ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እስያ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ በኢኮኖሚው ዘርፍ በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋራ ራዕይ በመያዝ በተቀናጀ፣ በተባበረና ዘላቂ ደህነነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘላቂ ሰላም ያለበትን አካባቢያዊ ሁኔታ በመፍጠር ሽብረተኝነትን መዋጋት እንደሚያስፈልገ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” ከደቡብ ፓስፊክ አንስቶ ደቡብና መካከለኛ እስያና አውሮፓን እንዲሁም አፍሪካን የሚሸፍን ሲሆን፤ 60 አገሮችን ያቅፋል።
በኢኒሼቲቩ ቻይና የመሠረተ ልማት ግንኙነቱን ለማሻሻል በበርካታ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ተሰማርታለች። ከነዚህ መካከል ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው የባቡር መስመር የሁለቱን አገሮች ከተሞች በማገናኘት ረገድ ተጠቃሽ ነው።
በተጨማሪም ከጃካርታ – ባንዶንግ፣ ከቻይና – ላኦስ እና ከሀንጋሪ – ሰርቢያ የተገነባው የባቡር መስመርን ጨምሮ በጓዳርና በፔሩስ የተገነቡት ወደቦች የኢኒሼቲቩ እውነታነት ማሳያ ተደርገው ይጠቀሳሉ።
በቀጣይም የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በምድር፣ በባህርና በአየር የመጓጓዣ መስመርና በመረጃና ኮሙኒኬሽን ስርዓት በአካተተ መልኩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ ይጠበቃል።
ከዚሁ መድረክ ጎን ለጎን በተካሄደ የከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ቻይና ለዓለም እድገትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ገልጸዋል።
ታዳጊ አገሮች በተለይም አፍሪካውያን ለእድገትና ብልፅግና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቻይና ታላቅ አጋር መሆኑዋን ነው ያብራሩት።
አብዛኛዎቹ ታዳጊ አገሮች በተለይም አፍሪካውያን ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቻይናን እንደ ስኬታማ የኢኮኖሚ አርአያ እየተከተሏት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም “ኢኒሼቲቩ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግጭት አልባ የሆነ ግዙፍ የኢኮኖሚ ትብብር ራዕይ መገለጫ ነው። የቻይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና ምርጥ ልምዶችን ለመቅሰምም አቅም የሚሰጥ ነው” ብለዋል።
“ቻይና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይም ግንባር ቀደም በመሆን ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ኢኒሼቲቩ አካባቢያዊ ትብብርን በማጠናከር ረገድና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት በማምጣት እንዲሁም የ2030 የልማት አጀንዳን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ኢንሼቲቩ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካውያን ራዕይ ለማሳካት ካወጣው አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ መሆኑን ነው የገለጹት።
”የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” በቻይናው ፕሬዝዳንት ጃንፒንግ እ.ኤ.አ በ2013 የመነጨ ልዩ መርሃ ግብር ነው።
ይህ ልዩ መርኃ ግብር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2030 ይደረስባቸዋል ብሎ ያቀዳቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ያስችላል ተብሎ ይታመናል።
ኢኒሼቲቩ በተለይ በአፍሪካ ለሚተገበሩ የልማት ሥራዎች አማራጭ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር እምነት ተጥሎበታል።