በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የሚመክረው የለንደኑ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የብሪታኒያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ መሪዎች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ እና የአፍሪካ ሀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።
በዚህ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በአሸባሪ ቡድኑ አል-ሸባብ ላይ የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር እና በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ /አሚሶም/ ሀይሎች በጋራ እያካሄዱት ያሉት ዘመቻዎች እያዳከሙት፣ ያለው ድጋፍ እና ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተዋል።
የአሸባሪ ቡድኑ በስሩ ያሉትን ተዋጊዎች የማዘዝ አቅሙ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ተዳክሟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እየሸሸ ያለ ቡድን ቢሆንም አሁንም በሶማሊያም ሆነ ከዚያ ውጪ የሽብር ጥቃት የመፈፀም አቅም እንዳለው ነው ያነሱት።
በመሆኑም አሚሶም እና የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር የተቀናጀ እና የተጠናከረ ጥቃት በቡድኑ ላይ ማካሄድ አለባቸው ብለዋል።
አል-ሸባብን በራሱ ቆሞ የሚዋጋ እና የአገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ የመጠበቁን ሀላፊነት ከአሚሶም መረከብ የሚችል የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር በጥቂት ዓመታት ውስጥ መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ሶማሊያን ለማረጋጋት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአሚሶም እና ለሶማሊያ ብሄራዊ ጦር የፖለቲካ፣ ፋይናንስ እና ሎጀስቲክ ድጋፎችን ሊያደርግ እንደሚገባም ነው በንግግራቸው ያሳሰቡት።
በሶማሊያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ማእቀብ በከፊል መነሳቱን ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ማእቀቡ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
በሶማሊያ የተከሰተው ረሃብ እና ያንን ተከትሎ የመጣው የኮሌራ ወረርሽኝ በአከባቢው ሰላም ላይም ስጋት መሆኑን በመጠቆም፥ ችግሩ ሰፊ ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነትን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
ሶማሊያ በቀጣይም እርዳታ እንደሚያስፈልጋት በመግለፅም የአገሪቱን የፌደራል መንግስት መሰረት ባደረገ መልኩ ዓለም አቀፍ ድጋፉ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ በበኩላቸው፥ በሶማሊያ የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት ለአሚሶም ጦራቸውን ያዋጡ ሀገራት ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን፣ ኬንያ ፣ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ እጅግ የተለየ ጠንካራ ስራዎች በማከናወናቸው እና የላቀ መሰዋዕትነት በመክፈላቸው ባለፉት አምስት አመታት የሶማሊያ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በንግግራቸውም ሶማሊያ ፀጥታ የሰፈነባት፣ የተረጋጋች እና የበለጸገች እንድትሆን ብሪታኒያ ድጋፏን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።