Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተማማኝ ሰላምን የሚፈጥር ሥርዓት

0 354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አስተማማኝ ሰላምን የሚፈጥር ሥርዓት
ዳዊት ምትኩ
ያለፈው ታሪካችን ብዙ እውነታዎችን አስተምሮናል። ያለፉት ሥርዓቶች ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ገዥዎችን ተጠቃሚ ያደረጉት ብቻ ሳይሆኑ፤ ሀገራችንን በሁለንተናዊ መልኩ ጎድተዋታል፡፡ ምጣኔ ሀብቷን አድቅቀዋል፤ ዜጎቿን የበይ ተመልካች በማድረግ ለችጋርና ለስደት ዳርገዋል፡፡ ይህ የታሪካችን አንድ አካል መሆኑ ጨርሶ የሚካድ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በተለይ የጥቂት መኮንኖች ስብስብ የነበረው ወታደራዊው አምባገነናዊ የደርግ ሥርዓት የህዝቡን የትግል ውጤት በመቀማትና አጋጣሚውን በመጠቀም ድሉን ወደ የራሱ አስመስሎ በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ጣጣ ፈጥሮ ማለፉ የትናንት ትውስታችን መሆኑ አይረሴ ነው፡፡
ይሁንና ሕዝቦቿ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ዜጎቿም ተፈቃቅደውና አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መስርተው እርስ በርስ እየተከባበሩ በፈጠሩት ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጣንና ተከታታይ ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበት ሀገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ታዲያ ይህን እየጎለበተ የመጣውንና የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር ጠይቋል፡፡ ይህ በታሪክ ሁሌም የሚወሳ ሃቅ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ወታደራዊው አምባገነን የደርግ ሥርዓት በተደመሰሰበት ማግስት ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች በሀገሪቱ ተፈጥረው ነበር፡፡ በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዙ ፌዴራሊዝም ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ ጎራ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ፅንፎች ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ፡፡
ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ አንደኛው፣ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሀገሪቱ መፍትሔ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን “በእኛ እናውቅልሃለን” የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደ ማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ታዲያ በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ ነበር። ውጤቱም በተራማጅ ኃይሎች አሸናፊነት እልባት ሊሰጠው ችሏል፡፡
ከዚህ በኋላም ቢሆን ሁሉም ነገር ደልዳላ አልነበረም፡፡ መግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ሀገሪቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገና ከፊት ለፊቷ ተደቀነባት፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች የላቀ ስፍራ የያዘው እና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት የሆነው ድህነትን የመዋጋት ዘመቻና ገፅታን የመቀየር ስራ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ የጋራ ጠላት መፍትሔ የሚያገኘው በመንግሥትና በመላ ሀገሪቱ ዜጎች የተባበረ ክንድ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ተገቢው መፍትሔም ተሰጥቶታል፡፡
በእነዚያ ዓመታት ሥልጣን የሚገኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰጥ የይሁንታ ድምፅ እንደሆነም የማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ወቅት ‘ሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሊኖራት አይገባም፤ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፈዴራላዊ ሥርዓት የምትገነባ ሀገር በምንም መልኩ ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም’ የሚሉ ተቃራኒ አመለካከቶች ዋነኛ ፈተናዎች ሆነው ብቅ ቢሉም ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
እናም እነዚህ ውጣ ውረዶች ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እየተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደውና ተማምነው ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትን ማፅደቅ ችለዋል፡፡ ህገ መንግሥቱም የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎችን ሊመልስ በቃ፡፡
ህዝቦቿም ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መግጠም ጀመሩ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አረጋገጡ፡፡ ይህን በጽናት ለመዋጋትም እጅ ለእጅ ተያያዙ፡፡
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመሩ፡፡ ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት መሸጋገርን ተያያዙ፡፡ ውጤቱንም ማጣጣም ጀመሩ፡፡ ህገ መንግሥቱ ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መጡ፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋገጠላቸው፡፡ በእነዚህ መብቶቻቸውም ተጠቃሚ ሆኑ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ነበርና ይህም ሆነ፡፡
በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ሥርዓት በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም ችለዋል፡፡
እናም ሥርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት የቻለ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ሥርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ ቁመና ቢያበቃትም ቅሉ፤ አሁንም ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው፡፡
እናም በእኔ እምነት ተግዳሮቶቹን መፍታት የሚቻለው በሥርዓቱ ብቻ ነው። እርግጥ ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትናንት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች እየፈታ ነው፡፡
ዛሬ ሥርዓቱን ተግዳሮቶቹ እየፈተኑት ቢሆኑም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንገስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በሥርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እየፈቱ ይቀጥላሉ፡፡ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ሌሎች ተግዳሮቶች ቢያጋጥማቸውም ዋስትናቸው ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ሥርዓቱ በመሆኑ በህግ አግባብ መሻገራቸው አይቀርም፡፡ ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy