Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አድሃሪያን ሚዲያዎችን እንታገል!

0 360

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አድሃሪያን ሚዲያዎችን እንታገል!

ኢዛና ዘመንፈስ

በኛ አገሩ አጠቃላይ እውነታ ውስጥ፤ ለመሆኑ አድሐሪያን ሚዲያዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ቀላል እንደማይሆን ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ድረስ ትርጉም ያለው የጋራ መግባባት ላይ ካልደረስንባቸው ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ፤ ምን ዓይነት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ናቸው የሚያስፈልጉን? እውን እንደ ኢሳትና ኦ.ኤም.ኤን ዓይነቶቹ ኢትዮጵያውያን ህዝቦችን ጎራ ለይተን እንድንናቆር ለማድረግ ያለመ መርዘኛ ፖለቲካቸውን እንዲግቱን መፍቀድ ይጠበቅብናልን? ወዘተ የሚለው ነጥብ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላልና ነው፡፡

ለማንኛውም ግን እኔ በግሌ ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት የተጓዘችበትን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ሂደት፤ ከማጓተት ለመቀልበስ እስከ መሞከር በደረሰ ተደጋጋሚ እክል ፈጠራቸው ሲፈታተኑት የሚስተዋሉት ነውጥ ናፋቂዎቹ የሚዲያ ተቋማት በአድሐሪነት ሊፈረጁ ይገባል የሚል ፅኑ አቋም አለኝ፡፡ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተቋማቶቻችንንም ጭምር፤ የሀገራችን “ነፃ” ፕሬስ ሚዲያ ከሚታወቅበት ያፈጠጠና ያገጠጠ ፅንፈኝነት የሚመነጭ አሉታዊ ተፅእኖ ሰለባ እንዲሆኑ ያደረጉበት አግባብ እንዳለ ነው ለኔ የሚሰማኝ፡፡

እንግዲያውስ በዚህ ፅሁፌ አድሐሪያን የመገናኛ ብዙሃን አካላትን አምርሮ ስለመታገል አስፈላጊነት የሚያወሳ ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት የተገደድኩትም ያለ ምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቁንስ በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ገና ከመነሻው ጀምሮ በፀረ ሀገር አንድነት ተፈርጀው ህዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣት ያለመ ጭፍን ውግዘታቸውን ሲያዘንቡበት የምናውቃቸው የግል ፕሬስ ሚዲያ ጋዜጠኞች፤ በአጠቃላይ የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ቁመና ላይም ጭምር በቀላሉ የማይሽር መጥፎ ጠባሳ ትተው ስለማለፋቸው የሚያመለክቱ የአስተሳሰብ ችግሮች፤ እዚያም- እዚህም ጎላ ብለው የሚታዩበት ጥሬ ሀቅ መኖሩን በመታዘቤ ነውና አሁን ወደ ዋናው ነጥብ እንለፍ፡፡

ስለሆነም፤ ይህን ስለ አድሐሪያን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና እንዲሁም ባለሙያዎች መበራከት የሚያወሳ መሰረተ ሃሳብ አንስተን መወያየት ካለብን፤ በቅድሚያ መጠቀስ የሚኖርበት ተያያዥ ጉዳይ ሆኖ የሚሰማኝ ነገር፤ በተለይ ከሽግግሩ ዘመን ጀምሮ እስከ ምርጫ 97 ማግስቱ የጎዳና ላይ ነውጥ ድረስ የነበረው “ነፃ ፕሬስ” ተብዬ የሚዲያ ዘርፍ የተጫወተው አሉታዊ ሚና ነው፡፡ ይህን ስል ደግሞ፤ የሽግግሩ መንግስት የመተዳደሪያ ቻርተር ይፋ ያደረገውን የፕሬስ ነፃነት አዋጅ ተከትሎ፤ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ አሸን መፍላት በጀመሩበት የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ የፊተኛውን ረድፍ ይዘው በመሰለፍ፤ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ አምርሮ የማጥላላት ሰፊ ዘመቻቸውን ሲያጧጡፉት የተስተዋሉት አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፀሐፍት እነ ማን እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ መስሎ ይሰማኛልና ነው፡፡

በግልፅ አነጋገር፤ ከላይ በተመለከተው የጊዜ ክልል ውስጥ የነበረውን የግል ፕሬስ ሚዲያ አጠቃላይ ቁመና ተሸናፊዎቹ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ.ቱባ ቱባ ካድሬዎች፤ በአምሳላቸው የቀረፁት አድርጎ መውሰድ እንደሚቻልና ለዚህ የመከራከሪያ ነጥብ አሳማኝ ምክንያትን እንደ አብነት ማቅረብ እንደማያዳግትም ጭምር ነው እኔ በግሌ ለመጠቆም የምሻው፡፡ እንዲያውም ያኔ ይስተዋል የነበረውን የግሉ ፕሬስ ሚዲያ ጋዜጠኞች ስርነቀል የስርዓት ለውጡን “ውግዝ ከመዓሪዎስ” የማለት ያህል የሚቆጠር ጭፍን ተቃውሞ፤ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ነው ብሎ ከማመን ይልቅ፤ የተሸናፊው ወታደራዊ አገዛዝ ርዝራዦች፤ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ኢህአዴግን ለመቀበል ያለመ ፕሮፓጋንዳቸውን ያጧጧፉበት ነበር ቢባል ነው እውነታውን በተሻለ መልኩ የሚገልፀው፡፡

ከዚህ የተነሳም፤ አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ ለመላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚበጁ ፈርጀ ብዙ በጎ ገፅታዎችን የተጎናፀፈ የመሆኑን እውነት ደፍረው የሚናገሩ ቅን ዜጎች “ለሆዳቸው ያደሩ አፍቃሪ ወያኔዎች” ተደርገው ስለሚፈረጁና ለፈርጀ ብዙ ጥቃት የመጋለጥ ዕጣ ሊገጥማቸው ስለሚችል ተገደውም ጭምር የጭፍን ተቃውሞውን ሰልፍ የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ይፈጠር ጀመር፡፡ ይህ ማለትም ደግሞ፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሒደት፤ መሟላት አለባቸው ተብሎ ከሚታመንባቸው ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ምናልባትም ዋነኞቹ ተደርገው የሚወሰዱት ሃሳብን ያለ አንዳች መሸማቀቅ የመግለፅ ነፃነትና የፈለጉትን የፖለቲካ አቋም የመደገፍ፤ እንዲሁም ያልፈለጉትን የመቃወም ምክንያታዊነት ሞቶ እንዲቀበር የሚያደርግ ተግባር ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡

ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚና አሳሳቢም ጭምር እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የፌዴራላዊው ስርዓታችንን ተጨባጭ ትሩፋቶች ደረጃ በደረጃ እያጎለበተ ቀጥሎ የኢትዮጵያን ህዝቦች ለከፋ ሀገራዊ ውርደት ተዳርገው ከቆዩበት ስር የሰደደ ድህነትና ኋላ ቀርነት ማላቀቅ እንደሚቻል ለዓለም ያሳየበትን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ሲረዱ እንኳን፤ የደርግ ርዝራዦቹ የግሉ ፕሬስ ፀሐፊያን፤ ያንኑ የ “ገንጣይ – አስገንጣይ” ወንጀላቸውን ከማመንዠግ ሊታቀበሉ አለመፈለጋቸው ነበር፡፡ ታዲያ እቺን የጋራ ቤታችን ናት የምንላትን ሀገርና መላ ህዝቦቿን ወደ ተጨባጭ ዕድገትና ብልፅግና እያሸጋገረ ስለመሆኑ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር የተመሰከረለትን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ በማጥላላት እንቅልፍ አጥቶ ማደርን እንደ ጠቃሚ ሙያ የሚቆጥር ሚዲያ አድሐሪ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ኖሯል? ምናባትም አድሐሪነት ብቻውን ላይገልፃቸው ይችላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ወጣም ወረደ ግን፤ ከአዲስ አበባው “የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ሚዲያ” እስከ የባህር ማዶዎቹ ኢሳትና ኦ.ኤም.ኤን በቀጠለ የአጥፍቶ መጥፋት ቅኝት ያለው መርዘኛ የቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ዘመቻቸው የሚታወቁት ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ በሀገር ቤቱ የመገናኛ ብዙሃን ሙያ ዘርፍ ላይ የማይናቅ አሉታዊ ተፅእኖ ሳያሳድሩበት እንዳልቀሩ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም፤ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የፌዴራል ሚዲያ ተቋማትና እንዲሁም የክልል መንግስታት መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲዎች ተቀጥረው ከሚሰሩት ጋዜጠኞች መካከል፤ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞው እያስመዘገበ ያለውን ፈርጀ ብዙ ውጤት፤ በተሟላ መልኩ የመግለፅ ድፍረት የሚያንሳቸው ጥቂት እንዳልሆኑ ይታመናል፡፡

ከዚህ አኳያ የሚገለፀውን ጨለምተኝነትም እንበለው፤ ወይም ደግሞ አድሐሪነት የተጠናወተው ክፉ አባዜ የሙጥኝ የማለት ልክፍት እንደወረርሽኝ ሲዛመት የሚስተዋልበት ተጨባጭ እውነታ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተቃራኒው የሚታይ ሌላም ሚዲያ ነክ ችግር እንዳለብንና መታረም ካልቻለ ጉዳቱ ቀላል እንደማይሆን ነው የሚሰማኝ፡፡ ስለሆነም፤ በተለይ የመንግስት ተደርገው የሚቆጠሩትንና እንዲሁም ደግሞ መሰረታቸው ከኢህአዴግ መራሹ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ዘመን ጋር በተቆራኘ መልኩ ስለሚገለፅ ብቻ፤ የገዥው ፓርቲ ልሳናት እንደሆኑ ተደርገው በሚወሰዱት የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ጋዜጠኞችን የሚመለከተው ችግር ምን እንደሚመስል ጠቁሜ ለማለፍ አሞክራለሁ፡፡

በዚህ መሰረትም፤ ለኔ እንደዋነኛ የተጠቃሾቹ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮቻችን መታረም ያበት አሳሳቢ ችግር ሆኖ የሚሰማኝ ጉዳይ፤ በተለይም ከኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መገለጫዎች ጋር ተያይዞ የሚታይ ድክመትን የሚመለከት ነው፡፡ በግልፅ አነጋር፤ አንዳንድ ያልተገባ ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉና የለመዱ ጋዜጠኞች በግንባታ ሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ተከታትለው እውነታውን የሚገልፅ ወቅታዊ መረጃ ከማቅረብ ይልቅ፤ ያልተሰራውን የልማት ስራ እንደተሰራ አድርገው ሲዘግቡ የሚስተዋሉበት ከሙያው ስነ-ምግባር ያፈነገጠና ሌላው የአድህሮት ችግር ማሳያ ድርጊት እንደሆነ ደፍሮ መናር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም ደግሞ፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን ስነምግባራዊ ግድፈት ተከትሎ የሚፈፀም ሚዲያ ነክ የሙስና ተግባር ያልተሰራውን የልማት ስራ የተሰራ አስመስሎ በመዝገብ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ አግኝተው ተገቢውን የእርምት እርምጃ የመውሰድ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ ከማድረጉም ባሻገር፤ ሚዲያዎቹ ያልሆነውን ነገር ሁሉ ሆኗል ብለው በዘገቡ ቁጥር ህብረሰባችን ለስርዓቱ የሚኖረው አጠቃላይ ግምት እየተዛባ መሔዱ አይቀርምና ነው፡፡

ለዚህ አስተያየቴ የተሻለ አብነት ይሆናል የምለውም ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገችው አንደኛው የዕድገትና ትራንስፍርሜሽን ዕቅድ ዘመን ውስጥ፤ የግንባታ ሒደታቸው ተግባራዊ ተደርጎ እንዲጠናቀቅ ሲባል፤ በጀትን ጨምሮ ሌላም አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ከተሟላላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን መካከል፤ ምን ያህሎቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ማለቅ ሲችሉ እንደተጓተቱና ለምን እንደተጓተቱም ጭምር የሚያስረዳ አሳማኝ ዘገባ ያቀረበ ሚዲያ አለመኖሩን ነው፡፡ ከቶውንም አንዳንዶቹማ፤ የኋላ ኋላ ገሃድ ወጥቶ መገኘቱ የማይቀረውን ጥሬ ሀቅ ሁሉ፤ እንዳሻቸው እያድበሰበሱ በማቅረብ መንግስት በሚመራቸው የዚህች አገር ህዝቦች ዘንድ አመኔታን እንዲያጣና በተራ ዋሾነት እንዲፈረጅ ጭምር ለማድረግ ያለመ ሂሳዊ ዘገባቸውን ሲያስደምጡን፤ አልያም ደግሞ ሲያስነብቡን መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

ስለዚህም፤ እንደኔ የግል ግንዛቤ ከሆነ፤ የፌዴራሊዝም ስርዓታችን ዓይነተኛ መለያዎች ተደርገው መወሰድ የሚገባቸው ሕገ-መንግስታዊ እሳቤዎች በሚፈለገው ስፋትና ጥልቀት እንዲጎለብቱ የማድረግ ወሳኝ ሚና መጫወትን ጨምሮ፤ ሌሎችም ለመላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣፈንታ መቃናት ሲባል ፅኑ መሰረታቸው የተጣለ የስር ነቀል ለውጡ ዋነኛ ግቦች የታለመላቸውን ተልዕኮ እንዲያሳኩ በማድረግ ሂደት ውስጥ ሚዲያው ትርጉም ያለው እውነታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ ነውን? ብሎ መጠየቅ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚያም ባልተድበሰበሰ መልኩ የሚካሔድ ግልፅ የውይይት መድረክ እንዲከፈትና እያንዳንዱ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የሚዲያ ተቋም የሚመራበትን ኤዲቶሪያ ፖሊሲ ጨምሮ፤ የሰራተኞቹን የአስተሳሰብ ቁመና ጤናማነት ትርጉም ባለው ምክንያታዊነት አስደግፎ እየፈተሸ የአመለካከት ብዥታውን እንዲያጠራ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መቻል ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ይሰማኛል፡፡

አለበለዚያ ግን፤ እዚሁ አገር ውስጥ እኛው መሀል ተሰግስገው የፌዴራሉ መንግስት የሚዲያ ተቋማትና ብሎም የየክልሎቹ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲዎችም  ጭምር፤ የኢሳት ወይም ደግሞ የኦ.ኤም.ኤን ፕሮፓጋንዲስቶች ኢትዮጵያን በህዝቦቿ የብሔር ሌላ የልዩነት መግለጫ ምክንያች ሊያተራምሷት የሚሞክሩበትን የጥፋት መልዕክት በመመከት ረገድ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት እንዳይችሉ ለማድረግ ያለመ የሚያስመስልባቸውን፤ የማዘናጊያ ደባ ሲፈፅሙ የሚስተዋሉ ጋዜጠኛ ተብዬዎች ተበራክተዋል፡፡ ዘርፉ ከማናቸውም የሲቪል ሰርቫንት ተቋማት ይልቅ ለቀለም አብዮት ናፋቂዎቹ ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች አሉታዊ ተፅዕኖ የተጋለጠ ከመሆኑ የተነሳ፤ አብዛኛው ጋዜጠኛ ዕርስ በርስ የማይተማመንና ትክክለኛ አቋሙን ለማሳወቅ የማይደፍር ነው ቢባል ተገቢነት ይኖረዋል፡፡   ይህን መሰሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን አጠቃላይ ቁመና ባለበት ሁኔታ፤ የስር ነቀል ለውጡን ጉዞ ለአሳሳቢ የቅልበሳ አደጋ የሚያጋልጡ ችግሮቻችን ተደርገው የሚወሰዱትን የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝት ፅንፈኛ አመለካከቶች ስለመታገል አስፈላጊነት መናገር  ጉንጭ ከማልፋት የዘለለ ውጤት እንዲኖረው አይጠበቅም፡፡

ስለዚህ እንደኔ እምነት ከሆነ፤ የሀገራችንን የመገናኛ ብዙሃን ሙያ ዘርፍ፤ ከላይ በፅሁፌ መግቢያ ለማመልከት በተሞከረው ታሪካዊ ደራው ምክንያት፤ እጅጉን ስር የሰደደ የአድህሮት አመለካከት ችግር እንደተጠናወተው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ እናም ችግሩ ራሱን የቻለ የአስተሳሰብ ትግልን የሚጠይቅ ስለመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ ነው እያልኩ ለዛሬ ያነሳሁትን ሚዲያ ነክ ሃተታዬን እነሆ እዚህ ላይ አበቃለሁ፡፡ ደህና ሁኑልኝ!       

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy