Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያዊያን የዕድገት ጉዟቸውን ቀጥለውበታል!

0 378

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያዊያን የዕድገት ጉዟቸውን ቀጥለውበታል!

አባ መላኩ

ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአስገራሚ የታሪክ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የቀድሞውን የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማስመለስ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ተሰልፈዋል። ጥንካሬ፣ ትጋትና ውጤታማ ቁመና ላይ በመሆን የዕድገት ጉዞውን ተያይዘውታል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ህልውና እንደ አገር በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። በዚያን ወቅት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ተንገራግጯል። የመሠረተ ልማት ግንባታው እንዳይሆን…እንዳይሆን ሆኗል።

ብሔራዊና ኃይማኖታዊ ጭቆና ተባብሶ ህዝብ ተንገፍግፎ ኖሯል። ወጣትና የተማሩ ዜጎች ራሳቸውንና ህልማቸውን ለማዳን ምርጫቸው ስደት ሆኖ ቆይቷል። ጥቂቶችም ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ራዕይ ሰንቀው ለነፃነታቸው መታገልን መርጠዋል። ታዲያ ዛሬ ይህ የነፃነት ታጋዮች ወኔና ተስፋ ለእንዲህ ያለ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሊያበቃን ችሏል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ፣ የወደፊት ተስፋዋም ብሩህ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። ዛሬ ኢትዮጵያ የልማት ሞዴል በመሆኗ ሌሎች በርካታ አገሮች ተሞክሮዋን መቅሰም ፈልገዋል። ምርጫቸው አድርገዋታልም። ይህች አገር – ኢትዮጵያ በብጥብጥና ባለመረጋጋት በሚታወቀው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የሠላም፣ የመረጋጋትና ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ልማት ለማስመዝገብም በቅታለች።

ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት አሥርት ዓመታት ምጣኔ ሀብቷ በፍጥነት አድጓል፡፡ በዚህም በዓለማችን በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ አምስት አገሮች መካከል አንዱ ለመሆን በቅታለች። ይህ ዕድገት እውን ሊሆን የቻለው መንግሥት በቀረፃቸው ትክክለኛና አሳታፊ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካይነት ነው፡፡

እስካሁን በተመዘገበው ዕድገት ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ ተችሏል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ወደ መቶ በመቶ ለመድረስ ተቃርቧል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ረገድም ትልቅ እመርታ ተመዝግቧል። አዳዲስ ከሚገነቡትና የግል ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይጨምር የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ዛሬ ላይ 34 ደርሰዋል።

ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ተደርጎ የተቀረፀው በመከላከል ላይ መሠረት ያደረገው የጤና ፖሊሲም ውጤታማ ሆኗል። መንግሥት በዜጎች መካከል ፍትኃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በአነስተኛ ዋጋ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ላይ ይገኛል።

እንዲሁም የአገሪቱን ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ 6450 ሜጋት ዋት እንዲያመነጭ ተደርጎ በመገንባት ላይ ያለው ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በሁለት እጥፍ የማሳደግ አቅም ይኖረዋል። ግንባታው ሌት ተቀን እየተካሄደ ይገኛል፤ በቅርቡም ለግንባታው መሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ስድስተኛ ዓመት ተከብሯል። ዛሬ ግንባታው ከ57 በመቶ በላይ ደርሷል።  

ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ ነበረች፡፡ በመሆኑም አሁን የቀድሞውን ገናና ታሪኳንና ታላቅነቷን ለመመለስ በትግል ላይ ያለች አገር ሆናለች። በመተባበርና ጠንክሮ በመሥራት ወደ ቀድሞው የመሪነት ሥፍራ ለመመለስ የሚያስችለው ጊዜ አሁን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የበለፀገ አገር ለመሆን የሚረዳትና በግልፅ የሚታይ የህዳሴ ራዕይ አላት፡፡ በዚህ ሂደት የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማፋጠን፣ ዜጎችን የተማሩና በራሳቸው ጉዳይ ላይ ወሣኝ በማድረግ የኢትዮጵያን ድምፅ በዓለም እናስተጋባለን፡፡ ከተራራው አናት ላይ ወጥተንም ከፍ ባለ ድምጽ እንዘምራለን።

ይሁንና የወደፊት ጉዟችንና ስኬታችን ላይ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮት ተደቅኖበታል፡፡ ከልማታችን መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እየተነሳ ይገኛል፡፡

መንግሥት የሚያሰሩ ፖሊሲዎችን በመቅረፅና የግልፅነት ሥርዓት በመዘርጋት ችግሩን ለመፍታት በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ አጋርነትን ይፈልጋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኃላፊነት በመውሰድ የኪራይ ሰብሳቢነት አሠራሮችን ለመዋጋት፣ ፍትህና ተጠያቂነት የሰፈነባት አገር ለመገንባት የየድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል፡፡

የግልፅነትን አሠራር ለማጎልበትና በተለያየ ደረጃ ያለውን አስተዳደር ለህዝብ ተጠያቂ ለማድረግ እንዲቻል የተጀመረውን ትግል በሁሉም መስክ ስኬታማ ለማድረግ መረባረብ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ይሆናል። ይህን ሁኔታ ህዝብ በአግባቡ ተረድቶ ወደፊት ያለውን የግልፅነት፣ የአንድነትና የተስፋ መንፈስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተግቶ እንዲሰራ ይጠበቃል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለቴሌኮምና ለባቡር መስመር ዝርጋታ በልማት ድርጅቶቹ አማካይነት ሰፋፊ ኢንቨስትመንት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህ መሠረተ ልማትና የሰው ሀብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበት የሚካሄድ ነው፡፡

 

በዚህ መንገድ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እና እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ የሚበረታቱበት፣ መሬት፣ ብድርና ሌች ድጋፎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ሌሎች የመንግሥት አገልግሎቶች ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ በማድረግ ልማታዊ ኢንቨስትመንቶቹ ይበልጥ አዋጭ የሚሆኑበትና የሚስፋፋበት ሁኔታ በየጊዜው እየጐለበተ ሄዷል፡፡ ይህም ሆኖ ሳለ ለኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱ ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነቱ የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ወይም ከግሉ ዘርፍ በሽርክና እንዲካሄዱ እየተደረገ ይገኛል፡፡

 

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩት የኢንዱስትሪ መስኮችም የማዳበሪያ፣ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግና የስኳር ኮምኘሌክሶች ናቸው፡፡

 

በዚህም መሠረት ባለፉት 26 ዓመታት መንግሥት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስን ሀብትን መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ ተግባራት ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የሕዝብ ተሳትፎን በማጐልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ችሏል፡፡  

 

በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ የልማት መብቶችና ዓላማዎችን ለማረጋገጥ የግብርና መር የኢንዲስትሪ ልማት ስትራቴጂ ተቀይሷል፡፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትም የተመሠረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሕዝብ 84 በመቶው የሚኖረውም በገጠር ነው፡፡ የሚተዳደረውም በግብርና ሥራ ነው፡፡ አገሪቱ በብዛት ያላት ሀብትም /ጉልበትና መሬት / ከግብርናው ዘርፍ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ሥርዓቶች እጅግ ትኩረት የተነፈገውና ሲበዘበዝም የኖረ ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ህገ መንግሥቱ በሚደነግገው ፍትሀዊና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገው ልማት መሠረት በመንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት የአገሪቱን በአጠቃላይ በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ የሚጠቅም ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

 

ስትራቴጂው ፈጣን ዕድገት ለማረጋገጥ፣ ሕዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ እንዲጠቀም ለማድረግ፣ ኢትዮጵያን ከተመጽዋችነት ለማዳን እና በአገሪቱ የዳበረ የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ወሣኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨባጭ እየተረጋገጠ ያለውም ይኽው ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy