Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እኛው በእኛ ስለእኛው የምንተጋለት ፕሮጀክት

0 388

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እኛው በእኛ ስለእኛው የምንተጋለት ፕሮጀክት

ስሜነህ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ፊት የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋዩን ሲያኖሩ፣ ‹‹የህዳሴ ጉዟችን መሀንዲሶች እኛው፣ ግንበኞችና ሠራተኞች እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ ባጠቃላይ የህዳሴው ጉዟችን ባለቤት እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው፤›› በማለት የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይህን ንግግር በየጊዜውና በየአጋጣሚው እንሰማዋለን፡፡ መጋቢት 24 በመጣ ቁጥርም ከነጭብጨባውና እልልታው እንደ አዲስ እንሰማዋለን፡፡ እነሆ እስከ ባለፈው መጋቢት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ባለቤቶች መሆናችን ማስረጃ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ ታላቅነት በብዙ መልኩ የሚገለጽና ደማቅ ነው።  ስለሆነም ህዝቡ ከላይ በተመለከተው አግባብ እኛው የፋይናንስ ምንጭ መሃንዲስና ሰራተኛ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።ይህ  ደግሞ ህዝቡ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን በማሳያ የሚያጠይቅ እና የፋይናንስ ምንጭ የመሆኑን ምክንያቶች የሚዘረዝር ነው።

ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውለው ሁለተኛው ዙር ቶምቦላ ሎቶሪ  ከሚያዚያ 1ቀን 2009 ጀምሮ ገበያ ላይ መዋሉ የመጀመሪያው ማሳያ ነው።ከቶምቦላ ሎተሪው እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለማሰብሰብ ታቅዷል። እስካሁን 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የመኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪዎች፣ ፍሪጅና መሰል ለእድለኞች የሚሰጡ ሽልማቶች ተገኝተዋል።ሽልማቶቹን የግል ባለሀብቶችና የተለያዩ ተቋማት ያበረከቱት ሲሆን አጠቃላይ ግምታቸውም እስከ 20 ሚሊየን ብር እንደሚደርስ የህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል። ይህ ደግሞ የታላቁን ግድብ መላቅና ለኛ ምን ማለት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው።

የቶምቦላ ሎቶሪው ባለ ሦስት መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርታማ መኖሪያ ቤት፣ የ2016 ስሪት ሃይሉክስ ባለሁለት ጋቢና ተሽከርካሪ፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርታማ መኖሪያ ቤት እንዲሁም አንድ ሊዮንቺ፣ ማቀዘቀዣና የጭነት መኪና ሽልማቶችን ያስገኛል።

ከእነዚህም በተጨማሪ የእርሻ ትራክተር፣ ባለሶስት እግር ባጃጆች፣ ማቀዘቀዣዎች፣ የውሃ ማጣሪያዎች፣ ላፕቶፖች፣ 32 ኢንች ኤል ኢዲ ቴሌቪዥኖች እና ስማርት ስልኮች ለባለ እድለኞች የሚበረከቱ ሲሆን ሎተሪውን የሚገዙት ኢትዮጵያውያን ሽልማቶቹንም ያበረከቱት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የእኛውን የፋይናንስ ምንጭነት በሚገባ ያመላክታል ። ከመጀመሪያው የህዳሴው ግድብ ሎተሪ ሽያጭ በሀገሪቱ በሎተሪ ሽያጭ ከፍተኛ የሆነ 64 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል።

በተመሳሳይ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት 6ኛ አመት ዋዜማ ላይ “ጊዜ የለንም እንሮጣለን ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን”በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ 85 ሺህ ዜጎችን የሚያሳትፍ በትግራይ 12 ፣ በአማራ 40 እና በኦሮሚያ 38 ከተሞች የተከናወነው ታላቅ ሩጫ ከእቅድ በላይ በወጣው ህዝብ መጥለቅለቁ እና ቲሸርት አልቆ ህዝቡ በራሱ መለያ መሳተፉ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። ከህብረተሰቡ ከሚጠበቀው 12∙4 እስከ 12∙6 በመቶ የግንባታ ወጪ ከ70 በመቶ በላይ ወይም 9∙4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም እኛው የፋይናንስ ምንጭ ስለመሆናችን የሚያመላክት ነው ።የመንግስት ሰራተኛው፤የግል ሰራተኛው ተማሪዎች ሳይቀር በየዓመቱ እንደአቅማቸው ቦንድ ገዝተው ቃል ኪዳናቸውን ሲያድሱ ማየት እኛው የፋይናንስ ምንጭ ስለመሆናችን ከማረጋገጥም በላይ ስለምን ለሚለው ጥያቄ የሚያንደረድር ይሆናል።   

 በግንባታው ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሽንጣቸውን ገትረው ሌት ተቀን በመትጋት ላይ መሆናቸው ደግሞ እኛው መሃንዲሶችና የቀን ሰራተኞች ስለመሆናችን ዋነኛው ማሳያ ነው ፡፡ ስለምን ይህ ሆነ? ነው ጉዳዩ።

ኢትዮጵያ ብዙ የውኃ ሀብት እያላት ግን ሀብቷን ያላለማች፣ የሰማይ ዝናብ ከመጠበቅ ያልተላቀቀች፣ ውኃ እያላት የሚጠማት፣ ለም መሬት እያላት ረሃብ ያልተለያት ሃገር ሆና ዘመናትን መቀጠሏ ዋነኛው ምክንያት እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ ስለሆነም የጸረ ድህነት ዘመቻን ጀምረናል።የጸረ ድህነት ዘመቻችን ካለውሃ የሚታሰብ አለመሆኑ ደግሞ መሰረታዊው ምክንያት ነው።  

የዓባይ ወንዝ ምንጭ መሆናችን እና ከላይ የተመለከተው ድህነትን ይዘን መክረማችን የሚፈጥረው ቁጭት እኛው የፋይናንስ ምንጭ እና እኛው የቀን ሰራተኛ ስለመሆናችን ከበቂ በላይ ምክንያት ነው። ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ በጋራ ስለመልማት እንጂ የአባይ ምንጭ ስለሆንኩኝ ለኔ ብቻ የሚል አቋም የሌላት መሆኑና ከዚሁ ጋር ተያይዞም  በዓባይ ወንዝ  ላይ ከሱዳንም ይልቅ የዋና ተጠቃሚነቱን ድርሻ ይዛ ያለችው ግብፅ እስካሁን ካላት ጥቅም በላይ ገና ተጨማሪ የምትፈልግ ዓባይን የራሷ ያህል እንዲያውም የራሴ ብቻ ካልሆነ በሚል ኋላቀር አስተሳሰብ ተጠርንፋ መቆየቷ ሌላውና ቁጭት የሚፈጥር ለህዝባዊው ተሳትፎ መጠናከር በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው፡፡  

ግብፅ በመካከለኛው ምሥራቅ ባጠቃላይ የአረብ ሃገራትን ጨምሮ መላው አውሮፓን እና አሜሪካን በመወትወት ሃገራችን ለልማት የምትፈልገውን ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝና ሌላም ጫና እንዲጨመርላት ቀን ከሌት መትጋቷ እኛው የፋይናንስ ምንጭ ስለመሆናችን ከበቂ በላይ የሚሆን ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡ በሰላም ሊፈቱ ያልቻሉ የውስጥ ችግሮቻችንን ከጎረቤት ባላንጣዎቻችን ጋር በመሸረብ፤  የኤርትራን ትግል በማዳከሚያነት ስትጠቀምበት፤ አዳዲስ የአካባቢ ቅራኔ ውስጥ እጇን በማስገባት፤ በጥቅሉ የውስጥ ችግሮቻችንን በማባባስ፣  እና የሃይማኖት ሰላምን በማደፍረስ  ድህነታችን ላይ ሌላ ድህነት ለመጨመር የማትተኛው ግብጽ እኛው የቀን ሰራተኛ ሆነን በትጋት ለመስራት በቂ ምክንያት ይሆነናል፡፡

ሁሉም አሻራውን ለማሳረፍ የሚረባረበው፤እራሱ የፋይናንስ ምንጭና መሃንዲስ ሆኖ ቀን ከሌት የሚተጋው፤ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከጸረ ድህነት ዘመቻው ባሻገር ኢትዮጵያን በክፍለ አህጉሩ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ስለሚያደርጋትም ጭምር ነው ፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የነደፈችውን ዕቅድ ለማሳካት ድርሻው የጎላ መሆኑም እኛ የፋይናንስ ምንጭ እንድንሆን ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፋይናንስ ምንጭ መሆናችን  ሳለ ከድህነት መውጫ መንገዶች ዋነኛ የሆነ ሌላ አጋጣሚም ፈጥሮልናል። አገራዊ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ረድቶናልና፡፡በተመሳሳይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት የሚያስችል ደረጃ ላይ ጭምር አድርሶናልና።  

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ውሃ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ለውሃ ትራንስፖርት፣ ለአሳ እርባታ ፣ለቱሪዝም እና ለአነስተኛ መስኖ አገልግሎት ይውላል፡፡ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የ2015 ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በየዓመቱ ከሚያገኙት አዲስ ውሀ መያዝ የሚችሉት 4 በመቶውን ብቻ ነው፡፡የበለፀጉት ሀገራት ደግሞ ከ70 እስከ 90 በመቶውን ያጠራቅማሉ፡፡ በዓመት በነፍስ ወከፍ 6ሺ 103 ሜትር ኪዩብ ውሃ በማጠራቀም ሩሲያ ከአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ ግድቦች አማካኝነት በዓመት በነፍስ ወከፍ የምታጠራቅመው ውሃ በተከዜና ጊቤ ሃይል ማመንጫዎች የተጠራቀመውን ሳይጨምር 45 ሜትር ኪዩብ ያህል ብቻ የነበረ የመሆኑም ታሪክ በታላቁ ግድባችን ተረት ሆኖ የሚቀር መሆኑም እኛው የፋይናንስ ምንጭ ለመሆን ከበቂ በላይ ምክንያት ነው።

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መንድር ያለው ሁኔታ የትም ቦታ ያልታየና ያልሆነ በየትኛውም ወቅት ያልተከሰተ የመሆኑ ምክንያትም ይኸው ነው።ሁላችንም በተሰማራንበት የስራ መስክ በጥድፊያ ባለመታከትና ወደር በማይገኝለት ወኔ የበለጸገችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የትጋት መሰረታችን መሆኑን ያረጋገጠልን ፕሮጀክት ስለሆነም እኛው የፋይናንስ ምንጭ፤ እኛው የቀን ሰራተኞችና መሃንዲሶች ሆነን እስከፍጻሜው የምንቀጥል መሆኑ አያጠራጥርም።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy