Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እየተጠናከረ የመጣው ጠንካራ መስክ

0 266

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

እየተጠናከረ የመጣው ጠንካራ መስክ
ዳዊት ምትኩ
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሁሉም አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ማራመድ ላይ ያተኩራል። አንዱን እየጠቀመ ሌላውን የመጉዳት ዓላማ የለውም። ይህም የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን ዜጎች ጥቅም ብቻ ሳይሆን፤ የአካባቢውን ህዝቦች ጥቅም የሚያስከብሩ ጉዳዩች ላይ የሚያተኩር ሃላፊነት የሚሰማው አካል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህን ለመተግበርም ላለፉት ጊዜያት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ተግባሮችን አከናውኗል።

የሀገራችንን የዲፕሎማሲ ጥረት ጉዳይ መዘውሩን የያዘው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው—የሌሎች መስሪያ ቤቶች ተግባራትም እንደተጠበቁ ሆነው ማለቴ ነው። ቀደምት የሀገራችንን የዲፕሎማሲ አካሄድ ስንመለከት የአለፉት ሥርዓቶች በተለይም የደርግ የውጭ ግንኙነት ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ባህሪይ የሚመነጩና በርካታ ጉድለቶችም የነበሩበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም ሀገሪቷን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ድቀትና ለማያባራ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ ከሠላም ታገኝ የነበረውን ጥቅምም እንዳታገኝ አድርጓት ኖራል፡፡
ደርግ ይከተለው በነበረው አምባገነናዊ ሥርዓት ሳቢያ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከጎሮቤት ሀገሮች ጋር በጥርጣሬ ከመተያየታቸውም በላይ ግንኙነታቸው ወታደራዊ አቅምን በማፈርጠም በጠብ መፈላለግ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ በዓይነቱም በይዘቱም ተለወጧል፡፡ በጋራ ጥቅምና ህልውና በማስከበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ህገ – መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት የሰጠ እንዲሁም በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር አድርጓል፡፡
ከዚህ ውሰጥ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ስራም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲው ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡ ውጤታማም ሆናለች፡፡
የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 20 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡
በመሆኑም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱ ነው፡፡ ህዝቡም የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ካሁን በፊት ዘላቂ የልማትና ድህነት ቅነሳና ፈጣን ዘላቂ ልማት ድህነትን የማጥፋት ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራሞች በሚገባ ለማሳካት ተችሏል፡፡
ስለሆነው እነዚህን ለመተግበር ከፍተኛ ገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ሰፊ የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የገንዘብ ምንጮች እንደተጠበቁ ሆነው የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በሚፈቅደው መሰረት በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥረቶች ከለጋሽ ሀገሮችና ድርጅቶች እንዲሁም ከልማት አጋር ድርጅቶች የልማት ገንዘብን ማግኘት ተችሏል፡፡
በዚህም ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ይህን ማስፈጸምና መፈጸም የሚችል የሰው ኃይል በዲፕሎማሲው ዓለም የሚጠይቀውን ግብዓት ማግኘት የግድ ይላል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ፖሊሲውና ስትራቴጂው ምቹ መሰረት ጥሏል፡፡
እንደሚታወቀው በአህጉር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ሠላም የማስከበር ተልዕኮ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ለማስከበር ባላት ቁርጠኝነት በተባበሩት መንግስታት ተመርጣ በኮሪያ ሠላም አስከባሪሳራዊቷን በማሰማራት ቁርጠኝነቷን አሳይታለች፡፡
በተለይም የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን የሠላም ግንባታ ዲፕሎማሲንም የሚያካትት በመሆኑ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሠላም አስከባሪ ኃይሏን በሩዋንዳ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ በሱዳን ዳርፉርና አብዬ በሙሉ ፈቃደኝነትና በብቃት አሰማርታለች፤ አኩሪ ተግባርም ፈጽማለች፡፡ ይህ የሰላም ማስከበር ተግባር የኢትዮጵያን ጠንካራ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ አካሄድን የሚያሳይ ነው፡፡
አንቨስትመንትም የዲፕሎማሲ ተግባር አካል ነው፡፡ አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሠላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ- ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ዋንኞቹ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሠረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳያል፡፡
ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ዋስትና አይደሉም፡፡ የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርም ሀገሪቷ ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች በውጭው ዓለም የሚያስተዋውቃቸው አካል ከሌለ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህም የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አመቺ የኢንቨስትመንት መስኮችን በውጭው ዓለም ለማስተዋወቅ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰሳቸው በአሁኑ ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
ይህም የዳበረና ጠንካራ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጥረታችን ውጤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱና በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡ እነዚህ ጥቅል ውጤቶች ሀገራችን የተከተለችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ መንገዶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ታዲያ ሁሉም ሰው ለሀገሩ አምባሳደር በመሆኑ ጠንካራው የዲፕሎማሲ ስራ ይበልጥ እንዲጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል እላለሁ። አበቃሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy