Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህብረቱ ፓርላማ ምን እያለን ነው?

0 377

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህብረቱ ፓርላማ ምን እያለን ነው?

                                                               ዘአማን በላይ

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ከመሰንበቻው አንድ አስገራሚ መግለጫ አውጥቷል። ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያለው ነው። ዳሩ ግን የህብረቱ ፓርላማ ያወጣው መግለጫ ሀገራችን ከህብረቱ ፓርላማ ጋር ያላትን ይህን ጠንካራ ግንኙነት የሚያውቀው አይመስልም። መግለጫው በጥቅሉ ሲታይ፤ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኘውን የዶክተር መረራ ጉዲና የሸብር ተጠርጣሪነትን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን፣ በሀገራችን ውስጥ በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ቀውስ መንግስት ያካሄደውን ምርመራ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከተ ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን እንደ ዜጋ በርዕሴ ላይ ካነሳሁት “የህብረቱ ፓርላማ ምን እያለን ነው?” ከሚለው መጠይቅ በመነሳት በመግለጫው የተጠቀሱትን ጉዳዩች ዝርዝር ኋላ ላይ የምመለስበት ቢሆንም፤ ለጊዜው ግን በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ጥቂት ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።  

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ አብራ እየሰራች የምትገኝ ሀገር ብቻ አይደለችም። ይልቁንም ከህብረቱ ጋር ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የመሰረተች ሀገር ናት። ለዚህም በህብረቱ ዕውቅና እና ድጋፍ እየተሰጣት ይገኛል። ሆኖም የአውሮፓ ፓርላማ ይህን የኢትዮጵያንና የህብረቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከነ አካቴው አያውቀውም በሚያስብል ሁኔታ መግለጫ አውጥቷል። ርግጥ ፓርላማው በውስጡ ካቀፋቸው አንዳንድ ለኢትዮጵያ በጎ ምልከታ ከሌላቸው ግለሰቦች የተሳሳተ ዕይታ በመነሳት ይህን አስገራሚ መግለጫ እንዳወጣ ለመገንዘብ አያዳግትም። ያም ሆኖ በእኔ እምነት መግለጫው አስገራሚ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት የሚፃረር፣ ህገ መንግስቱን የሚያኮሰምንና ዕውቅና የማይሰጥ እንዲሁም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የሚገባ ጭምር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እናም መግለጫው የተፃፈበትን ወረቀትና ብዕር  ያህል ዋጋ አለው ብዬ ለመቀበል ያዳግተኛል።

እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ በህብረቱና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን በጋራ ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተውን የሁለትዩሽ ግንኙነት ጥላ ሊያጠላበት ይችላል የሚል እምነት አለኝ። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የሀገራችንና የህብረቱ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ ያተኮረ መሆኑን አውሮፓውያኑ በሚገባ የሚያውቁት ይመስለኛል። የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሲመሰርቱም በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎታቸውን በኃይል መጫን እንደማይችሉ ተገንዝበው እንደሆነም እንዲሁ። ለዚህም የራሳቸው ምክንያቶች ያላቸው ይመስለኛል። ይኽውም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የህይወት መስዕዋትነት ጭምር በመክፈል እያደረገች ያለችውን የላቀ ሚና ስለሚገነዘቡ፣ ሀገራችን ልማትን ለማሳለጥና ጅምሩ ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ስለሚያውቁ በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ያላትን ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ስለሚረዱ እንዲሁም ከ800 ሺህ በላይ የጎረቤት ሀገር ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ ብሎም በዓለምና በአህጉር አቀፍ ደረጃዎች ያላትን ተቀባይነት በሚገባ የሚያጤኑ መሆናቸውን በዋነኛ ምክንያትነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። እነዚህ የመንግስታችንና የህዝባችን የማንነት መገለጫዎችና ቁልፍ ተግባራት የአውሮፓ ህብረትም ፍላጎቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ። የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነቱ የማዕዘን ድንጋይ መሆናቸውንም ጭምር።

ታዲያ እነዚህ የግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥኑ እንጂ፤ አንዱ “ጌታ” ሌላው ደግሞ “ሎሌ” ሆኖ የሚከናወኑ አይመስለኝም። አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ የሚሆንበት አሰራር በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ተግባቦት ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይችልም። የኢትዮጵያ ፓርላማ በህብረቱ የውስጥ ጉዳይ እጁን ለማስገባት እንደማይፈልግ ሁሉ፤ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማም ከፖሊሲ አንፃር በውስጥ ጉዳያችን እጁን ሊያስገባ የሚችልበት አመክንዮ የለም። ይህን ዕውነታ የህብረቱ ፓርላማ በሚገባ የሚያውቀው ይመስለኛል።

እናም በእንዲህ ዓይነቱ የጋራ ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት የ“አድርግና አታድርግ” አሰራር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ፓርላማው ቢያውቀውም፣ መልሶ ሊያውቀው የሚገባው ይመስለኛል። ስለሆነም አውሮፓዊያኑ ይህ የዲፕሎማሲ ነባራዊ አሰራር የኢትዮጵያና የህብረቱ ትስስር ከተጠቃሚነታቸው ማዕቀፍ የሚያገኙትን ትሩፋቶች በጋራ በመቋደስ “የቄሳርን ለቄሳር…” በሚል መርህ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። እናም የኢትዮጵያን ህዝቦች የውስጥ ጉዳይ ለኢትዮጵያዊያን መተው ይገባል እላለሁ። ከዚህ ውጭ ልክ በውሸት በክብሩ የሰው ልጅ መብት ታዛ ስር ተጠልሎ ‘የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ’ እንደሚለውና ራሱን በማያውቀው “ሰብዓዊ” ተግባር “ሂዩማን ራይትስ ዎች” እያለ እንደሚጠራው አክራሪ የርዕዩተ-ዓለም ተቋም በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ በመግለጫ ጋጋታ እጅን ለመጠምዘዝ የመሞከር ፍላጎት ነው የሚሆነው። ታዲያ ይህ ፍላጎት አንድም፤ በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙሉ ፍላጎት እንዲሁም ይሁንታ ከዛሬ 22 ዓመት በፊት የተሰናዳውን የሀገሪቱን የበላይ ህግ የሆነውን ህገ መንግስትን አሳንሶ የማየት፣ ሁለትም፤ በ“እኛ እናውቅላችኋለን” አባዜ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት በጠራራ ፀሐይ መጋፋት ከመሆን የሚዘል ሊሆን አይችልም።   

ስለ ሀገራችንና ስለ ህብረቱ በአሁኑ ወቅት ስላለው ጠንካራና ሊሆን ስለሚገባው ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት ማዕቀፍ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ የህብረቱ ፓርላማ ስላወጣው አስገራሚ መግለጫ ዝርዝር ሁኔታ ላንሳ። በመግለጫው ላይ የተጠቀሰው አንደኛው ጉዳይ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኘውን የተጠርጣሪው ዶክተር መረራ ጉዲናን የክስ ሁኔታ የተመለከተ ነው። ይህን አስመልክቶም መግለጫው በተጠርጣሪው ዶክተር ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲነሳ ጠይቋል። ይህ የፓርላማው ጥያቄ ተገቢ ያልሆነ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የሀገራችንን የፍትህ ስርዓት በጣልቃ ገብነት ከውጭ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል ለመቆጣጠር ያለመ ነው። ሲጀመር በአውሮፓም ይሁን በአሜሪካ አሊያም በአሜሪካ የፍትህ ስርዓት ሂደት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉበት ህጋዊ መብት የላቸውም። ይህ አሰራር በሁሉም የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚተገበር ነው። ከዚህ ውጭ የግድ ጣልቃ እገባለሁ የሚል አካል ካለ፤ ለዚያች ሀገር የፍትህ ስርዓት ንቀት አለው ማለት ነው። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ በደፈናው ‘የአውሮፓ ህብረት ለሀገራችን የፍትህ ስርዓት ንቀት አለው’ የሚል እይታ ባይኖረኝም፤ የህብረቱን ፓርላማ ያሳሳቱት አንዳንድ አባላቶቹ ከተጠናወታቸው የ“እኛ እናውቅላችኋለን” አባዜ ውጭ ለየትኛውም ሀገር የፍትህ ስርዓት ሂደት ደንታ ቢስ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።  

ያም ሆኖ ግን እዚህ ላይ የህብረቱ ፓርላማ መገንዘብ ያለበት ዋነኛ ጉዳይ፤ ተጠርጣሪው ዶክተር የተከሰሰሱት ህብረቱ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት አውሮፓ ተጉዘው ሃሳባቸውን ስለገለፁ አለመሆኑን  ነው። ይልቁንም ተጠርጣሪው ዶክተር መረራ በአውሮፓ ቆይታቸው በሀገራችን ፓርላማ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ ሁለት ላይ የተመለከተውንና ማንኛውም ግለሰብ በሀገራችን ፓርላማ በአሸባሪነት ከተሰየሙ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ጋር መገናኘት እንደሌለበት የሚያግደውን ህግ በመተላለፋቸው ነው። በዚህም በአውሮፓ-ብራስልስ ቆይታቸው ግለሰቡ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የግብረ-ሽበራ ተግባር በማከናወን ከሚታወቀውና በሀገራችን ፓርላማ በሽብርተኝነት ከተሰየመው እንዲሁም በኤርትራ መንግስት ተላላኪነት እንደ አበደ ውሻ የሚራወጠውና ራሱን ግንቦት ሰባት እያለ ከሚጠራው የሽብር ቡድን መሪ ከሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተዋል። በዚህም ሆን ብለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል። ምናልባትም የህብረቱ ፓርላማ እንደሚገነዘበው፤ ተጠርጣሪው ዶክተር መረራ ጉዲና እዚህ ሀገር ቤት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ መሪ እንደ መሆናቸው መጠን፤ ስለ ህግ የበላይነት አያውቁም ብሎ ማሰብ አይቻልም። ነገርዬው በምንም ዓይነት ምድራዊ ምክንያት የማያስኬድ ቢሆንም ግለሰቡ የህግ የበላይነትን አያውቁም ቢባል እንኳን፤ “Ignorance of the law has no excuse” (ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም) እንደሚባለው፤ በሀገራችን የተደነገገ ማንኛውንም ዓይነት ህግ አለማወቅ ተጠያቂ ከመሆን ሊያድን አይችልም።

ታዲያ ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ለነበሩት ዶክተር መረራ ይህ እሳቤ የህግ ትምህርት “ሀሁ” ቢሆንም ቅሉ፤ እንደ ማንኛውም ዜጋ እርሳቸው አዋጁን በመተላለፋቸው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ተደርጓል። የህግ የበላይነት ደግሞ በአውሮፓም ይሁን በአፍሪካ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑን የህብረቱ ፓርላማ የሚገነዘበው ዕውነታ ነው። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ ተጠርጣሪውን ዶክተር በተመለከተ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ይኽው ብቻ መሆኑን ፓርላማው ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል።

በህብረቱ ፓርላማ መግለጫ ላይ የተመለከተው ሌላኛው በሀገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በስራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። ፓርላማው በምን ዓይነት የጥናት ስሌት እንደደረሰበት ግልፅ ባይሆንም፤ አዋጁን መንግስት በፖለቲካ ተነሳሽነት ያወጣው ነው ብሏል። እንዲህ ዓይነቱ አስገራሚ ብያኔ ‘ለወሬ ነጋሪ’ እንኳን የማይመችና ከአንድ የተጠናከረ መረጃ አለው ተብሎ ከሚታወቅ ፓርላማ የማይጠበቅ ቢሆንም፤ ሃቁ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመጀመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወጥቶ፣ ከ15 ቀን በኋላ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  እንዲተገበር የተደረገው ባለፈው ዓመት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ለመቀልበስና በምትኩ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ነው። የህብረቱ ፓርላማ ሀገራችን ውስጥ ተፈጥሮ ስለነበረው ሁከት እያወቀ፣ መንግስትም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያደረጋቸውን ተግባራት እየተገነዘበ እንዲህ ዓይነት ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የማይጣጣም ግርድፍ ብያኔ ማስቀመጡ እጅግ የሚደንቅ ነው። የህብረቱ ተወካዮች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሀገራችን ሲመጡ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያደረገችውን ክንዋኔ በማድነቅ እየገለፁ፤ ፓርላማው የአዋጁን መንፈስ ሊረዳ አለመቻሉ ጥያቄን የሚያጭርና ምናልባትም ከመግለጫው በስተጀርባ ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙ አካላት እንዲሁም እንደ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ዓይነት የርዕዩተ-ዓለም አክራሪዎች አለመኖራቸው ማንም ርግጠኛ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመጀመሪያው ስድስት ወራቶች የሀገሪቱን ሰላም በተሻለ ሁኔታ አስተማማኝ ማድረጉን የህብረቱ ፓርላማ የሚያውቀው ይመስለኛል። አዋጁ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የወጣ ቢሆን ኖሮ፤ በመሃል ላይ በአዋጁ ውስጥ የነበሩት እንደ የሞባይል ኔት ወርክና የማህበራዊ ቁጥጥር፣ በዋና ዋና የልማት ተቋማት ዙሪያ መንቀሳቀስ እንደማይቻል፣ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ተጠርጣሪዎችን መያዝና ብርበራ የማካሄድ እንዲሁም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መልዕክቶችን ክልከላና ቁጥጥር የመሳሰሉ ገደቦች ይነሱ ነበርን? እኔ በበኩሌ እነዚህ ወሳኝ ገደቦች የተነሱት ፖለቲከኞችን ለማጥቃት ሳይሆን፣ የሀገሪቱ ሰላም በየጊዜው እየተሻሻለ በመሄዱ ነው። አሁንም ቢሆን አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ሲወገዱ አዋጁም ሙሉ ለሙሉ መነሳቱ አይቀርም። እናም የህብረቱ ፓርላማ መግለጫ መንግስት በአዋጁ ላይ እነዚህን ወሳኝ የተባሉ ክልከላዎችን በማንሳት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት እንኳን ለመመልከት ያልፈቀደ በመሆኑ በሚዛናዊነትና በቅንነት የቀረበ ነው ለማለት አይቻልም። ይህ ደግሞ እዚህ ሀገር ውስጥ ስር እንዲሰድ ለሚፈለገው ዴሞክራሲ ምንም ዓይነት ጠቀሜታ አይኖረውም።

ኧረ ለመሆኑ በየትኛው ሀገር ውስጥ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለፖለቲካ ፍጆታ ሊውል የሚችለው? አንድ ምሳሌ ላንሳ የህብረቱ አባል ሀገር የሆነችው ፈረንሳይ ስላወጀችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ። እንደሚታወቀው የፈረንሳይ ህገ መንግስት አንቀፅ 36 ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግልፅ ተመልክቷል። በእኛ ሀገር ህገ መንግስት አንቀፅ 93 ላይ እንደተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት ነው።  የፈረንሳዩ አዋጁ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወታደራዊ ተቋማት የፖሊስን የፀጥታ አጠባበቅ ስራ የመረከብ፣ እንደ መሰብሰብና የማንኛውንም ግለሰብ ግላዊ ይዞታ በቀንም ይሁን በማታ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የመበርበር፣ የፕሬስ ቅድመ-ምርመራ የማድረግንና የተለያዩ ትዕይንቶችንና ምልክቶችን የማገድ…ወዘተ. የመሳሰሉ መሰረታዊ የነፃነት መብቶችን የመገደብ፣ ለመደበኛው የሀገሪቱ ህግ ተገዥ የማይሆኑ ግለሰቦችን የማባረር ወይም በሪፐብሊኩ የግዛት ወሰን ውስጥ የመኖር መብት የሌላቸውን ሰዎች ከሀገሪቱ የማስወጣት ስልጣንን እንደሚያካትት የህብረቱ ፓርላማ በሚገባ ያውቀዋል። በቅርቡ በመዲናዋ ፓሪስ በጂዊሾች ሆቴል ላይ በደረሰ የሽብር ፍንዳታ ምክንያት 137 ንፁሃን ዜጎች በመሞታቸው ፈረንሳይ እስከ አሁን ድረስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ናት። እናም የህብረቱ ፓርላማ የፈረንሳይን ሁኔታ በምንም ዓይነት ስሌት ፖለቲከኞችን ለማፈን ነው ሊል አይችልም። ምክንያቱም ፈረንሳይ አዋጁን ገቢራዊ ያደረገችው ለሶስት ጊዜያት በሽብር ተግባር በመመታቷ ነው። አዋጁም በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ከሁከትና ከሽብር ተግባር እየተከላከለ ነው። ታዲያ ጉዳዩ ለእኛ ሀገር ሲሆን ‘ፖለቲከኞችን ለማፈን ነው’ ማለትን ምን አመጣው?…በእውነቱ ለዚህ ጥያቄዬ የህብረቱ ፓርላማ ምላሽ ምንም ሊሆን የሚችል አይመስለኝም ሲጀመር መግለጫው እውነትን የተከተለ አይደለምና።

ሌላው በህብረቱ ፓርላማ መግለጫ ላይ የተነሳው ሀገራችን ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ በኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተካሄደውን ምርመራ የሚመለከት ነው። ፓርላማው በሁከቱ የሞቱና የቆሰሉ ዜጎችን አስመልክቶ በውጭ ገለልተኛ ወገን ሊጣራ ይገባል ሲል ጠይቋል። ጥያቄው እዚህ ሀገር ውስጥ እየተመሰረተ ያለውን ራሱን በራሱ የሚያርም ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ብቻ አይደለም። ከዚህ በዘለለ “እኛ ካላጣራንላችሁ እናንተ ልትሰሩት አትችሉም” የሚል ንቀትንም በውስጡ የያዘ ጭምር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በዋነኛነት ግን እዚህ ሀገር ውስጥ ለተፈጠረ ችግር መፍትሔው የሀገሬው አሰራር እንጂ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሊሆን እንደማይችል ፓርላማው አልተገነዘበም፤ ወይም ሊገነዘበው አልፈለገም።

ሆኖም ኢትዮጵያ በተከሰተው ሁከት ሳቢያ የጠፋውን የሰው ህይወት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደምን የትኛውንም የውጭ ሃይል ለማስደሰት የምትፈፅመው ተግባር አይደለም። ይልቁንም ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የዜጎቿን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለድርድር የማታቀርብ ስለሆነ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። እናም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገለልተኛነት የተቋቋመውና ተጠሪነቱ ለእርሱ የሆነውን የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንዲያጣራ አዝዟል። በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ችግሩ ተከስቶባቸው በነበረባቸው አካባቢዎች የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ህይወት ማለፉን ገልጿል። ለዚህም የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዲሁም ግለሰቦች ተጠያቂ መሆናቸውን አስታውቋል። ይህም የኮሚሽኑን ገለልተኝነት የሚያሳይ ነው።

ርግጥ የዚህ ሀገር ባለቤቶችና ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንጂ የውጭ ሃይሎች አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። የራሳችንን ችግር መፍታት የሚገባን በራሳችን የዴሞክራሲ ማሳለጫ መንገድ እንጂ በውጭ ሃይሎች ችሮታና ፈቃድ ላይ በሚመሰረት የዴሞክራሲ መዘውር አይደለም። አይሆንምም። በመሆኑም የኢፌዴሪ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሰሉ የዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋሞች ምንም እንኳን ከአቅም ጋር በተያያዘ የራሳቸው ችግር ሊኖርባቸው ቢችልም፤ ተግባራቸውን ለህዝቡ በመወገን በገለልተኝነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። የህብረቱ ፓርላማ ይህን ጅምር የዴሞክራሲ ሁኔታ መደገፍና ማገዝ ሲገባው ‘ስለ እናንተ ሌሎች እንጂ እናንተ አታውቁም’ ለማለት መሞከሩ ምን ያህል በተሳሳተ መረጃ እንደሚመራ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።  

ለነገሩ ከእኛ በላይ ስለ እኛ የሚያውቅ ሊኖር አይችልም። ማንም የእኛን ተቋማት ተክቶ ስለ እኛ ሊሰራ አይችልም። የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስርዓቱ ራሱን በራሱ የሚያርምበት አንዱ መንገድ በመሆኑ ከማንኛውም የውጭ ሃይል ጋር በእኩልነት ሚዛን ላይ ሊቀመጥ አይችልም። ይቀመጥ ቢባልም፤ የኮሚሽኑ ስራ ሙሉ ለሙሉ ወደ ህዝብ የሚያጋድል ሲሆን፤ የውጭ ሃይሎች ግን ከፖለቲካ ፍላጎት ውጭ ሊሆኑ ስለማይችሉ ብያኔያቸውም ወደዚያው ማጋደሉ አይቀርም። ይህም የውጭ ሃይሎቹ ልክ እንዳሁኑ መግለጫ ዓይነት ለፍርደ ገምድልነት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል። በውጤቱም የሀገራችንን ዴሞክራሲ ከማቀጨጭ በስተቀር ምንም ዓይነት ረብ ያለው ነገር ሊሰሩ አይችሉም። ስለሆነም ፓርለማው የሀገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ራሱን በራሱ ለማረም የሚያደርገውን ጥረት መደገፍና ማበረታታት ሲገባው ስለ ገለልተኝነት ማውራቱ አግባብ ያለው እሳቤ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከተው ጉዳይም በህብረቱ ፓርላማ ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነው። እዚህ ላይ ፓርላማው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ለማንም ተብለው ሳይሆን ማንኛው ዜጋ ሰው በመሆኑ ብቻ የተቸረው የተፈጥሮ መብት መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት ሲፈልግ ለዜጎች የሚሰጠው ሳይፈልግ ደግሞ የሚከለክለው መብት አይደለም — የሰው ልጅ የማይገሰስ መብት ነውና። ያም ሆኖ ላለፉት 26 ዓመታት መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን ሀገራችን ውስጥ ለማረጋገጥ በህገ መንግስት እውቅና ከመስጠት ጀምሮ በተግባር እስከ መተርጎም ድረስ ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል። የህብረቱ ፓርላማ ግን ይህን እውነታ ለማየት የፈለገ አይመስልም። ከዚህ ይልቅ የርዕዮተ – ዓለም አቀንቃኞችን አሉባልታ ለመስማት ተገድዷል ማለት ይቻላል።

ርግጥ ለጉዳዩ ጀማሪ ከመሆናችን አኳያ በሀገራችን ውስጥ ከግንዛቤና ከአፈፃፀም ችግሮች በተነሳ ሰብዓዊ መብቶች በሚፈለገው መጠን ተረጋግጠዋል ማለት አይቻልም። ገና ሊተገበሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸው አያጠያይቅም። ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ነድፏል። የድርጊት መርሃ ግብሩ በሽግግር ይዘት ላይ የሚገኘውን የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝና የዴሞክራሲ ስርዓት በተቀናጀ መልኩ በዘላቂነት ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። መርሃ ግብሩ በህገ መንግስቱ ላይ የተጠቀሱ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ገቢራዊ ከማድረግ ባሻገር፤ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለትራፊክ ፖሊሶችና ለአሽከርካሪዎች መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህ በተጨማሪ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለእናቶች፣ ለህፃናት ማቆያ ቦታ እንዲኖራቸው እንዲሁም በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ ጥቃቶች ለደረሰባቸው ሴቶች ጊዜያዊ መንከባከቢያና የመርጃ ማዕከላት በጥናት ተለይተው እንዲገነቡ ብሎም በሐሰት ማስረጃና በስህተት ለእስር የተዳረጉ ዜጎች ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ለመዘርጋት የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባትን የመሳሰሉ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል። ታዲያ እነዚህን እውነታዎች የህብረቱ ፓርላማ ሊሰማቸው አይፈልግም። እናም በእኔ እምነት እነዚህን ተጨባጭ ሀገራዊ ሃቆችን ለማወቅ አለመሻት ዳተኝነት እንጂ ሌላ ትርጓሜ ሊሰጠው አይችልም። በአጠቃላይ በርዕሱ ላይ ያነሳሁትን “የህብረቱ ፓርላማ ምን እያለን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፤ የህብረቱ ፓርላማ እያለን ያለው ‘የሀገራችሁ ሉዓላዊነት ቦታ የለውም፤ ለህገ መንግስታችሁ እውቅና አልሰጥም እንዲሁም እኛ እንጂ እናንተ ስለራሳችሁ አታውቁም’ ነው። ሆኖም ይህ አስተሳሰብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ የሌለውና የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈፅሞ ሊያደምጡት የማይፈልጉት መሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy