Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰፈር ላይ ምጣዶች

0 913

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የሰፈር ላይ ምጣዶች!”

አክራሪ ዲያስፓራ ተቃዋሚዎችን አብዛኛዎቹን ባሰብኩ ጊዜ የሰፈር ምጣድ የሚለው ፅሁፍ ትዝ ይለኛል።
እንዴት መሰላችሁ እንደምታውቁት በኢትዮጵያዊያን አኗኗር ብዙ ሰፈር ላይ ብዙ ነገሮቻችን የጋራ ናቸው። ከዚህም መሐል አንዱ የሰፈር ምጣድ ነው። ይህ ምጣድ ከዘመናት በኋላ ማን እንደገዛው አይታወቅም። የተተወ ምጣድ ነው። የሰፈር ምጣድ እንደ ተዘዋዋሪ ችሎት በተለኮሰበት ይጣዳል። ይህ የሰፈር ምጣድ ሜዳ ላይ ጉልቻ ተጎልቶ እሳት ከተቀጣጠለ በኋላ ካለበት ሳብ ተደርጎ ይጣዳል። ከጠፋም ይረሳል፤ ቢሰበርም ጠያቂ የለውም ባለቤቱ አይታወቅምና እሳት በተለኮሰበት የሚጣደው የሰፈር ምጣድ ከትክል ምጣድ ይለያል። ትክል ምጣድ ቋሚ ንብረት ነው። ባለቤት አለውና ማንም አይወስደውም። አድራሻ አለው፤ ዙሪያው ስለታጠረለት እሳት አይባክንም። ስለማይዟዟርም የመሰበር፣ የመጎዳት አደጋው አነስተኛ ነው። ቢሰበርም ከፍሎ የሚያስጠግነው ባለቤት አለው። ደበቅ ያለ በመሆኑ የሚታዬው እንጀራው/ ፍሬው ነው። የሰፈር ምጣድ ግን በአደባባይ ተጋግሮበት በድብቅ ይበላል። በድብቅ የተጋገረበት ትክል ምጣድ ግን በግልፅ ያጠግባል።

የሰፈር ምጣድ በተለኮሰበት ሁሉ የሚጣድ የራሱ የሆነ አድራሻ የሌለው የጎዳና ንብረት ነው። እሳት የሚነድበት ታዋቂ ምጣድ ነው። ይህ ታዋቂነት ግን ባለቤት የለውም።
ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ አብዛኞቹ ዲያስፓራዎች እንደ ሰፈር ምጣዱ ናቸው። እንዴ ምን ለማለት ነው ብትሉኝ አንዱ ይነሳና የአማራ ማሕበር ይላል እሳት ይለኩስና ይጥድባቸዋል፣ አንዱ ይነሳና የጎንደር ማሕበር ጥሪ ይላል ይነሱና ይሰበሰባሉ እሳት ይለኩስባቸውና ይጠቀምባቸዋል። ሌላው ተነስቶ የኦሮሞ ሌላው ተነስቶ የትግሬ ይላል ሁሉም በየተጠራበት ለምን ተሰብሰብ እንደተባለ ሳያውቀው የጠራው ባለቤቱ ሳይታወቅ መሰብሰብ ነው፤ አክቲቪስቱ ነፃ፤ አውጭ ነጭ ባዩ እነሱን እንደ ሰፈር ምጣድ በጎጥ በመንደር በዘር እየሰበሰበ እንጀራውን ይጋግርባቸዋል። ጋግሮ ሲያበቃም ይጥላቸዋል። የሚያስታውሳቸው እንጀራው አልቆበት እንጀራውን መጋገር ( ኑሮውን መደጎም) ሲፈልግ ነው። ሌላ ጊዜ ግን እንደ ሰፈር ምጣድ ይሰበሩ ይፍረሱ ምን ይሁኑ አያስታውሳቸውም።

ባለፈው ጊዜ አስቴር አወቀ በዳሸን ስፖንሰር አድራጊነት ግዮን ዘፍናለች ኮንሰርቷ ላይ እንዳትገኙ BOYCOTT አድርጓት ኮንሰርቷ ተበላሸ ጥቂት ሰው ብቻ ተገኘ። ከሚገርማችሁ ጠሪው ማን እንደሆነ ለጥሪው ባለቤቱ ሐላፊነት የሚወስደው ሰው አይታወቅም፡፡ ዝም ብሎ አንድ ወረቀት በማሕበራዊ ድህረ ገፅ ጥሪ ከተለጠፈ በቃ እንደ ሰፈር ምጣድ ዝም ብሎ መለኮስ ነው። ማን ነው ምንድን ነው? እንዴት ነው? የለም። አሁን ደግሞ ዶክተር ቴዎድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ተቃወሙ በቃ እንግዲህ ይህ ሰው ምን ሰራ? ለምን እንሰለፋለን? ምን አደረገ የለም። እንደ ሰፈር ምጣድ ሁሉም ተገኙ ላላቸውና ለሚለኩስባቸው ዝም ብሎ ማገልገል ነው እንደ ተዘዋዋሪ ችሎት ጠሪው ለማይታወቅ አድራሻ ለሌለው ተቃውሞ ስንትና ስንት ሺህ ኪሎ ሜትር መንጎድ ነው። ሌላው ግን ከጀርባ ከእንግሊዛዊው ጋር እነርሱን ባለቤት የሌላቸው ተንከራታች ምጣዶቹን ተጠቅሞ እንደለመደው እንጀራውን ይጋግራል ኑሮውን ያበስላል።ባለቤት የሌለው ምጣድ መሆን እንዴት ያስጠላል። እንዴት ይሰለቻል።

እነዚህ ሰዎች ሁሉም ተጠቅሞ ይጥላቸዋል ለአሙቁሉኝ እንጂ ለሕይወት አይፈለጉም። እንደ ላብራቶሪ አይጥ ሁሉም የፓለቲካ ተቀባይነቱን፤ ቢዝነሱ መሞከሪያ ያደርጋቸዋል። የሰሙትን ሁሉ ያስተላልፋሉ ለለኮሰባቸው ሁሉ ይጋግራሉ። ስሜት ስለሚነዳቸው ፍሬን ወይም ማብረጃ የላቸውም። መገለባበጥ ስለማይደክማቸው ሁሉም ያውቃቸዋል አውቆም ይንቃቸዋል። የሰፈር ምጣድ ተፈልጎ የሚገኝ ነው፤ ስለ መጥፋቱም የሚቆጭለት ወገን የለም። እሳት ካልተቀጣጠለ ማንም አያስታውሰውም። ሁሉም ጋግሮበት አንድ ጥግ ላይ ይተወዋል። እንዲሁ እንደ ባዘነም ይኖራል።

አዎን አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ሰልፍ የሚወጣው አክራሪ ፓለቲከኛ ዲያስፓራም እንደ ሰፈር ምጣዱ ነው። የሚፈለገው የሚቀጣጠል ነገር ሲኖር ነው፤ ከዚያ ውጭ ማንም አያስታውሰውም። ሁሉም የሚመጣው መሪ ነኝ፣ አክቲቪስት ነኝ የሚል ሁሉ እንጀራውን ጋግሮበት አንዱ ጥግ ላይ ጥሎት ይሄዳል። ባለተረኛው አክቲቪስት ነኝ ባይ እንጀራ ጋጋሪ እስኪመጣ ደግሞ ዲያስፓራው መንከራተቱን ይቀጥላል።

አሁንማ የሚቃወሙት ነገር መብዛቱ አንድን ነገር ለይቶ ባለቤት ኖሮት ጠርናፊ ኖሮት መቃወም ያባት ነው። አድራሻ መሪ ባለቤት ለሌለው ተቃውሞ ግን መሰለፍ፣ መሰለፍ ምን የሚሉት ነው። የምንቃወመውን እንወቅ ለመጣው ሁሉ አንሰለፍ፤ እንቃወም ለተባለው ሁሉ አንቃወም። እናንተ እንዴት ከዲያብሎስ ታንሳላችሁ ዲያብሎስ እንኳን ስሙ የአመፅ ልጅ ተቃዋሚ ሆኖ የሚቃወመውን ግን ያውቃል እናንተ ግን አታውቁትም። ሁሉንም ትቃወማላችሁ ዘፋኙን፣ ጋዜጠኛውን፣ ባለስልጣኑን፣ ካድሬውን፣ መሪውን፤ ፀሐፊውን፤ ደራሲውን መንግስትን አሞገሰ ደገፈ የምትሉትን ሁሉ በቃ። ተሳደቡ ሲባሉ መሳደብ፤ ጩኹ ሲባሉ መጮህ፤ ለያውም አላማና ግብ የሌለው ጩኸት፤

በመጨረሻም አንድ ነገር ልበል እውነት ለኢትዮጵያ አገራችን መፍትሔ እንዲመጣ የምትፈልጉ ከሆነ መጀመሪያ እስኪ እናንተ ራሳችሁን ከጥላቻ፤ ከዘረኝነት፤ ከክፋት፤ ሕዝብን በጎጥ ከመከፋፈል፤ ከሰፈር ምጣድነት ራሳችሁን ነፃ አውጡ። ያኔ ሁሉም ጥሩ ይሆናል ቢያንስ በቅንነት በመነጋገር መፍትሔውን እናመጣለን።
እዚሁ አበቃሁ እናንተ ቀጥሉ ….

Kibrom Adhanom Ghebreyesus

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy