Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ

0 622

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት አመፅና አድማ ማስነሳት ወንጀል በ6 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ።

የፌደራል አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሹ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ዓላማን ለማራመድ፣ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር፣ የህብረተሰቡን ወይም የህዝቡን ክፍል ለማስፈራራትና የሀገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ በማሰብ ተንቀሳቅሷል።

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰ አመጽ እና አድማን መሰረት በማድረግ በተለይም በፌስቡክ ገጹ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን የተቀሰቀሰውን አመፅና ብጥብጥ ለማስቀጠል ቅስቀሳ ማድረጉም በክሱ ተጠቅሷል።

ከሳሽ አቃቤ ህግም የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም በማቀድ፣ መዘጋጀት እና ማነሳሳት ወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሽ ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ የቀረበበትን ክስ ተከላክሏል፡፡

አቃቢ ህግም ግለሰቡ በተከሰሰበት አንቀፅ መሰረት ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ ከፌስ ቡክ ገፁ የሰነድ ማስረጃዎችን እና የሰው ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ የተከሰሰበትን አንቀፅ በመቀየር በአንቀፅ ስድስት መሰረት የሽብር ተግባር እንዲፈፀም በማነሳሳት ወንጀል የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡

አቃቢ ህግ ተከሳሽ ባደረገው የሽብር ወንጀል ማነሳሳት ተግባር ከፍተኛ የንብረት ጉዳት በመድረሱ ቅጣቱ ከፍ እንዲል የቅጣት ማክበጃ ያቀረበ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ በቀላል ደረጃ እንዲመደብለት መስማማቱን ገልጿል፡፡

ተከሳሽ በበኩሉ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን፣ ታማሚና አቅመ ደካማ እናቱን እና ሁለት ህጻናትን እንደሚረዳ፣ ለኢትዮጵያ የደም ባንክ ደም በመለገስ የዜግነት ሃላፊነቱን መወጣቱን በቅጣት ማቅለያነት እንዲያዝለት ጠይቆ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎታል።

የፌደራሉ ከፍተና ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ትናንት ከሰዓት በዋለው ችሎት፥ ተከሳሽ በስድስት አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው አንዳርጌ በተከሰሰበት የሽብር ቡድን ተሳትፎ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ተከሳሹ ራሱን ግንቦት ሰባት ብሎ ከሚጠራው የሽብር ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ ከሽብር ቡድኑ አመራሮች በዋናነትም በሽብር ወንጀል ጥፋተኛ ከተባለው ከአበበ ገላው ጋር መረጃ መለዋዋወጡ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

በማህበራዊ ድረ ገፅ በተለይም በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ በመፈፀም፣ በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የሽብር ቡድኑ ከሚጠቀምባቸው ሚዲያዎች ጋር ከጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 13 ቀን 2008 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ መረጃዎችን በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፉን አቃቢ ህግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱን ክዶ የተከራከረ ሲሆን፥ አቃቢ ህግ በድረ ገጽ እና በፌስ ቡክ አድራሻው የተለዋወጣቸውን ሰነዶች እና የሰው ምስክር አቅርቦ አሰምቷል፡፡

በዚህም መሰረት በትናንትናው ዕለት የጥፋተኝነት ፍርድ ተፈርዶበታል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠትም ለነገ ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy