Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተዛቡ ቀደምት ግንኙነቶችን የሚያርመው ፌዴራላዊ ሥርዓት

0 382

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተዛቡ ቀደምት ግንኙነቶችን የሚያርመው ፌዴራላዊ ሥርዓት/ ዳዊት ምትኩ/

                                         

ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ይወልዳል። የዛሬ 22 ዓመት ገደማ እውን የሆነው የአገራችን ህገ መንግስት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መሰረትን የጣለ ነው። በዚህ ዴሞክራሲያዊ ሰነድም በርካታ ቁም ነገሮች ሰፍረዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ካለፉት ሥርዓቶች የወረስናቸውን የተዛቡ ግንኙነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለች አገር ናት። ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል። ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ አንዳንድ ወገኖች ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም። አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዕድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ ገጥመው ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ነው። በሥርዓቱ ውስጥ ዜጎች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል። ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትም ተሸጋግረዋል። ውጤቱን ከማጣጣም ባለፈ የህዳሴያቸውን ፈር ቀዳጅ መንገድ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ሥርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ አድርጓቸዋል። እርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ በመሆኑ ይህ ውጤት ከተገኘ 26 ዓመታት እየሆነ ነው።

የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው። ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ያም ሆኖ ያለፉት ሥርዓቶች በህዝቦች መካከል የፈጠሩት የተዛባ ግንኙነቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት እጥረቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚታዮ ግጭቶች መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው አይካድም። እርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ይመስለኛል። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በገፉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ ነባራዊ ክሰተት ነው። በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚመላለሰው የሰው ልጅ ቀርቶ ህይወት የሌላቸው ግዑዛን ነገሮችም በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ።  

እርግጥ ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስዔ የሚታይ ነው። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባትና። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ዳሩ ግን ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያለፉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረም በሚያደርገው የእኩልነትና የፍትህ ተግባራት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። የተዛቡ የህዝቦች ግንኙነቶችን በማስተካከል በሚደረጉ የፍትህና የእኩልነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለፉትን ስርዓቶች በመናፈቅ አሊያም በዚያኛው ዓይነት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሀገራችን እንድትመራ የሚፈልጉ አካላት ግን ይህን ሁኔታ ሊገዳደሩት ይሞክራሉ—ምንም እንኳን ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ለዚህ የሚሆን መፈናፈኛ ባይሰጣቸውም።

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው። መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግስቱ ገልፀዋል። ላለፉት 26 ዓመታት እያከናወኑት የመጡትም ይህን እውነታ ነው።

ምንም እንኳብ ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች መካከል የተዛቡ ግንኙነቶችን ፈጥረው ቢያልፉም፣ ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በእኩልነትና በፍትህ ዴሞክራሲያዊ መንገዶች እነዚህ ችግሮች እየተቀረፉ ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና ፍትህንና እኩልነትን ከማጠናከር አኳያም ረጅም ርቀት ተጉዟል። እርግጥ ሥርዓቱ ራሱን እያረመና እንደ ማንኛውም ጀማሪ የፌዴራል ስርዓት ያሉበትን ችግሮች እየነቀሰ እንዲሁም ካለፉት ክስተቶች እየተማረ በሀገሪቱ ህዝቦች በመታገዝ በአስተማማኝ መንገድ ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታም አሁን የተገኘውን የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ይበልጥ በፅኑ መሰረት ላይ እያኖረና የተዛቡ ቀደምት ግንኙነቶችን እያረመ የሚቀጥል ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy