Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዲፕሎማሲው ስኬት !!

0 1,240

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዲፕሎማሲው ስኬት !!

                                                            ይነበብ ይግለጡ

ዲፕሎማሲ አንድ ሀገር ከጎረቤቶችዋና ከሌላውም አለም አቀፍ ማሕበረሰብ ጋር ያላት ግንኙነት ወሳኝ ሂደት ነው፡፡ ሀገራችን ከጎረቤቶችዋም ሆነ ከተቀረው አለም ጋር የረዥም ግዜ ዲፕሎማቲክ ግንኙነትን የመሰረተች ነባርና ጥንታዊት ሀገር ነች፡፡በተለይም በዚህ ዘመን ከአለም ጋር የመሰረተችው የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ሰፊ መሰረት የገነባበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ኢትዮጵያ ከውጭው አለም ጋር መገናኘት የጀመረችበት ግዜ ራቅ ያለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡

በነገሥታቱ የሩቅ ዘመን ታሪክ ውስጥ የውጭ ግንኙነቶቻችን እንደአሁኑ የገዘፈ ደረጃ ባይደርሱም ለዛሬው መሰረት የጣሉ ሆነው አልፈዋል፡፡ከቀድሞው ዘመናት እንግሊዝ  ስዊድን ፈረንሳይ ኢጣሊያ ሩሲያ በኃላም የአሜሪካ መንግስታት ቀደምት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር መመስረት የቻሉ  ሀገራት ነበሩ፡፡

በተለይ የሩሲያ መንግስት ከጥንት ጀምሮ ሌላ ተጨማሪ ምንም ነገር ሳይፈልግ ኢትዮጵያን ፍጹም ወዳጅ አድርጎ ይጠብቅና ይከላከል የነበረ ነው፡፡በቅኝ ገዢነት የተሰማራበት የአለም ክፍል የለም፡፡በእርግጥ በዲፕሎማሲ ግንኙነት ውስጥ ሀገራት የየራሳቸው አላማና ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

ጥንት በዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስም ወደሀገራችን ይገቡ የነበሩ መልእክተኞች ቆንስላዎች ጉዳይ አስፈጻሚዎች በኃይማኖት ስም ይመጡ የነበሩትም ጭምር በሀገር ስለላ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው፡፡የኢትዮጵያን አቅምና ማንነት አስተዳደርዋን በመፈተሽ የሕዝቡን ስነልቦና በማጥናት ለቅኝ ግዛት ወረራቸው ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ሽፍን ተልእኮ አንግበው ነበር የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ለመመስረት ወደ ሀገራችን የሚገቡት፡፡

ለዚህም ቢሆን በጥንት ዘመን የነበሩት ቀደምት አባቶች ሴራውን ለማምከን አልሰነፉም፡፡ እንደዛሬው ትምህርትና እውቀት ባልተስፋፋበት ዘመንም ቢሆን ልበ ብርሀኖች ስለነበሩ ኢትዮጵያ ከየትኛውም መንግስት ጋር ፍጹም ወዳጅነትን የምትፈልግ መሆንዋን ለማንም ጠላት እንዳልሆነች ሲገልጹ ሲያሳውቁ ኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ገፍቶ ለሚመጣባት ጠላት የማትሰንፍ የማትተኛ ለመመከትና ክብርዋን ለመጠበቅ ምን ግዜም ዝግጁ መሆንዋን ከመግለጽም አልፈው ይሄንኑ እውነት በተግባር ለአለም ለማሳየት በቅተዋል፡፡

ኢጣሊያ መጀመሪያ በፍቅር ቀርባ በስተኃላ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ማሰብዋ ተዘጋጅታ ትግራይ ላይ ሠራዊት ማስፈርዋን የተረዱት ንጉስ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ በታላቅ ሀገራዊ ፍቅርና ወኔ ተመልተው መላውን ሕዝብ ከኢትዮጵያ አራቱም ማእዘናት ለሀገሩ እንዲሰለፍ በማዝመት ዘምተውም አድዋ ላይ ጦርነት ገጥመው ድል አድርገዋል፡፡

ለመጀመሪያ ግዜ በአለም ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በጥቁር ሕዝቦች መሬት በጦር መሳሪያና ድርጅት በትጥቅ ግዜው የፈቀደውን ዘመናዊ ታንክ መድፍ አውሮፕላን ይዞ ዘመናዊ የወታደራዊ ሳይንስ እውቀት ባላቸው የኢጣሊያን ጀነራሎች የሚመራውን ወራሪ ሠራዊት ባልተጠበቀና ባለልተገመተ ፍጥነት ወታደራዊ ብቃትና ፍጹም ጀግንነት በመደምሰስ በመላው ጥቁርአለም ታሪክ ውስጥ እንዲመዘገብ አድርገዋል፡፡

የኢጣሊያን ምርኮኞችን አለምን ባስደነቀ የዲፕሎማቲክ ብቃት በምሕረት ወደ ሀገራቸው መልሰዋል፡፡ጥንትም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶችዋም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በጋራ በመኖር መርሕ የምታምን ሀገር መሆንዋን ለአለም ደግማና ደጋግማ ያሳየች ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ የጎረቤቶችዋን ሰላም የራስዋ ሰላም አድርጋ የምትወስድ ጎረቤቶችዋ ሰላም ከሌላቸው ይሀው ችግር ተዛማች መሆኑን የምትረዳ በአካባቢዋም ሰላም እንዲሰፍን ተግታ የምትሰራ ሀገር ነች፡፡ በዚህ መርሕ የበርካታ የአለማችንን ሀገሮች ቀልብ ለመሳብና ወዳጅነትም እንዲፈጠር ለማድረግ ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ ለሁሉም ወዳጅ ነች ለማንም ጠላት አይደለችም በሚለው እምነትዋ ዛሬ በአለማችን ሰፊ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መመስረት የቻለች በርካታ የአለማችን ታላላቅ መንግስታት መሪዎች በየወቅቱ እየመጡ የሚጎበኙዋት ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡

ይህ የሚያሳየው በአለም ተቀባይነት ያለው የዲፕሎሚቲክ ግንኙነት መመስረት መቻልዋን ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት የመጀመሪያው ጽሕፈት ቤትና ከመስራች ሀገሮች አንድዋ፤ የአውሮፓ ሕብረት ቢሮውን የከፈተባት ከኒውዮርክና ከቤልጂየም ቀጥላ አዲስ አበባ ሶስተኛ አለም አቀፍ መዲና ለመሆን የበቃችበት ትላልቅ አለም አቀፍ ስብሰባዎችን ኮንፈረንሶችን ተቀብላ የምታስተናገድ ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ የዲፕሎማቲክ ስራዎችዋ ውጤትም ነው፡፡

በቀጠናውም ሆነ በአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን የበቃችበት፤በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚገኙት የአለማችን ሀገራት በአስረኛ ደረጃ በአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ የምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤትም በሙሉ ድምጽ አባል ለመሆን የበቃችም ነች፡፡  

የተገኘው ውጤት ራሱን ችሎ በአለም አቀፍ ደረጃ የተሳካ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከመመስረትና ከመፍጠር ጋር ተያይዞ የተገኘ ነው፡፡ በሶማሊያ የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር  ከአሸባሪዎች ጋር ያደረገችውና የምታደርገው ትንቅንቅ የከፈለችው መስዋእትነት ያስመዘገበችው ከፍተኛ ወታደራዊ ድልና ውጤት በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ሰላም እንዲሰፍን የተጫወተችው የሽምግልናና የአደራዳሪነት ሚና ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ በአለም ደረጃ ጎልታ እንድትወጣ ያደረጓት ስራዎች ናቸው፡፡

ከ250 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳንን ስደተኞች እንዲሁም ያለማቋረጥ ድንበር አልፈው የሚገቡትን የኤርትራ ዜጎች ከ100 ሺህ በላይ የሚገመቱትን በሰላም ተቀብላ ማስተናገድዋ ብቁ ለሆኑት ወጣቶች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረግዋ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተቀባይነት አሳድጎታል፡፡ይህንን የሚያደርጉ ሀገራት በአለማችን ብዙ የሉም፡፡

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መኮንኖችን እንዲሁም አውሮፕላን በረራ ተማሪዎችን ተቀብላ  በሀገር ውስጥ አስተምራ ማስመረቅ መቻልዋ ኢትዮጵያ በዲፕሎማቲክ መስኩ ለተጎናጸፈችው ትልቅ ስኬትና ድል ተመራጭ ለመሆንዋም ማሳያ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ የተመዘገበው ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፤የከተሞች መዘመንና መስፋፋት፤ የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ መቻልዋ፤ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተግባር ማዋልዋ፤በርካታ ግድቦችንና በተለይም በአፍሪካ አንደኛ በአለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ግዙፉን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለማንም የውጭ እርዳታ በራስዋ አቅም በሕዝብና በመንግስት ርብርብ ለመገንባት መቻልዋ ከአፍሪካም አልፎ አለም አቀፍ ተቀባይነትዋን በዲፕሎማሲው መስክ እንዲጎላ አድርጎታል፡፡

በኢትዮጵያ የታየውን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በምሳሌነት የሚወስዱ የአፍሪካና የሌሎችም አሕጉራት ታዳጊ ሀገራት እየተበራከቱ መምጣታቸው ኢትዮጵያ በተጨባጭ ሀገርን የለወጡ ስራዎችዋ ያተረፈችውን የዲፕሎማቲክ ተቀባይነት ይመሰክራል፡፡ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስኬታማነቱን እያረጋገጠ በመራመድ ላይ ይገኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy