የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለሚያከናውኑት ኢንቨስትመንት መጎልበት አገራቱ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጀርመኑን ምክትል መራሄ መንግስትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እንደገለጹት አገራቱ በልማት ትብብር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በተሻለ መልኩ እንዲቀጥል የአገራቱ መንግስታት መደገፍ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።
በተለይም በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንዲሰሩ አገራቱ በጋራ በሚከውኗቸው ተግባራት ዙሪያ ተነጋግረዋል ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የጀርመኑ ምክትል መራሄ መንግስትና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በሶማሊያ ጉብኝት አድርገው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በሶማሊያ የተገኘውን ሠላምና መረጋጋት በማስቀጠል፣ በመልሶ ግንባታ ስራዎችና በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መስራት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች መክረዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች በተለይም በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በጋራ ለመስራትም ተነጋግረዋል።