Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የገፅታ ግንባታችን እየዳበረ ነው!

0 255

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የገፅታ ግንባታችን እየዳበረ ነው!

ዳዊት ምትኩ

አገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገፅታ ግንባታ ስራዋ እየተቀየረ ነው። ሁሉም ሀገራት የሚመኟትና አብረዋት ለመስራት የሚፈልጓት ሆናለች። የቅርብ ጊዜውን ብናስታውስ እንኳን ቻይናና እንግሊዝን ጨምሮ በበርካታ አገራት የስራ ጉብኝትና በርካታ ስምምነቶችን አድርገዋል። በተመሳሳይ የኳታር፣ የሶማሊያ፣ የፖላንድ፣ የሲንጋፖር ወዘተ መሪዎች የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። ይክም አገራችን ከሁሉም አገራት ጋር ተቀራርባ ለመስራት በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ያረጋግጣል። ኢትዮጵያ ገፅታዋን እየቀየረች ነው። ይህም ኢትዮጵያ ከምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚመነጭ ነው።

ዲፕሎማሲያችን የሠላም ግንባታ ዲፕሎማሲንም የሚያካትት ነው። ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሠላም አስከባሪ ኃይሏን በሩዋንዳ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ በሱዳን ዳርፉርና በአብዬ ግዛት እንዲሁም በሶማሊያ በሙሉ ፈቃደኝነትና በብቃት አሰማርታለች፤ አኩሪ ተግባርም ፈጽማለች፡፡ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብም በጁባ የሰላም አስከባሪ ሃይል ለመላክ ተስማምታለች። ያለፉትና አሁን እየተከናወኑ ያሉት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸው የስትራቴጂውን ትክክለኛነት አስረጅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፖሊሲው ኢንቨስትመንትን በመሳበ ረገድም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፤ ባለፉት ዓመታት። እርግጥ አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሠላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ውስጥ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሠረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ዋስትና አይደሉም፡፡ የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርም ሀገሪቷ ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች በውጭው ዓለም የሚያስተዋውቃቸው አካል ከሌለ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እናም በዚህም የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመመራት በዋነኛነት የስራው ባለቤት የሆነው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አመቺ የኢንቨስትመንት መስኮችን በውጭው ዓለም በማስተዋወቁ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰሳቸው በአሁኑ ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

እርግጥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባልተነካ እምቅ ሀብትና የሰው ጉልበት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህን ህብረት በኢንቨስትመንት ለመጠቀም እንደ ቻይና፣ ህንድ ፣ ሱዳን፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣  ሳውዲ አረቢያ፣ የመን፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ ካናዳና አሜሪካ የመሳሳሉ ሀገራት በመስኩ ተሰማርተዋል፡፡

ይህም የዳበረና ጠንካራ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጥረታችን ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱና በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ፖሊሲው በርካታ ባለሃብቶችን በመሳቡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ይህን በመመርኮዝም የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የኢንቨስትመንት አዋጁን ደጋግሞ በመከለስ የበለጠ ተወዳዳሪ፣ ሳቢና ግልጽ በማድረግ አሻሽሎታል። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንቱ ሳቢና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለማድረግ ያለመ ተግባር ነው፡፡ በዚህም መንግስት ያቀደውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም። መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን በመገንዘብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ተወላጆች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ዘንድ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

በተለያዩ ወቅቶች እዚሀ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ የዲያስፖራ ጉባኤዎችና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተጠቃሽ ናቸው። እርግጥ መልካም ገፅታችንን ለማጉላት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት አለበት። ይህም ሲሆን ሀገር ታድጋለች፤ የህዝብም ተጠቃሚነት ይጎለብታል። እያንዳንዱ ዜጋም በየደረጃው ተጠቃሚ ይሆናል። አዎ! ሀገራችን የምትከተለው የጋራ ልማትና ትብብርን የሚያጠናክረው አቅጣጫን በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንበት ካሰብነው የለውጥና የመታደስ ስፍራ በእርግጠኝነት መድረሳችን የሚቀር አይደለም።

ከፖለቲካም አኳያ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 26 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡

በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ የቀጣናው አዋኪ ከሆነው ከኤርትራው ገዥ ፓርቲ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡ ይኸውም የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ጽኑ እና ቁርጠኛ እምነት መያዙ መቻሉ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው፤ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱና ህዝቡም በየደረጃው የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን እንደሆነ በጥብቅ ያምናል፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ የገፅታ ግንባታ ስራ እየጎለበተ መምጣት ችሏል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy