የግብርናው ዘርፍ ለውጥ ለኢንዱስትሪው መስፋፋት መደላድል ሆኗል
አባ መላኩ
በአገራችን ፈጣን ዕድገት ማረጋገጥ የሚቻለው እጥረት ያለብንን ካፒታል በከፍተኛ ሁኔታ የሚቆጥብ እንዲሁም በስፋት ያሉንን መሬትና ጉልበትን መጠቀም የሚያስችል የልማት ስትራቴጂን መተግበር ሲቻል መሆኑን የኢፌዴሪ መንግስት ታሳቢ በማድረግ ግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ፖሊሲ በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ በመረባረብ ላይ ይገኛል። የአገሪቱን ተጨባጭ ሃብት መሬትና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል ሰፊ የሰው ሃይል ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት የተፈጥሮ ሃብት በተላይ ነዳጅ ያላት አገር አይደለችም። በመሆኑም የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረቱ የህዝብና የመንግስት ቅንጅት ነው።
መንግስት ካፒታልን መቆጠብ የሚያስችል ግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን የኢኮኖሚ ፖሊሲን መተግበርን አማራጩ በማድረጉ አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። ግብርና መር የልማት ስትራቴጂ ሲባል ግብርናው ለኢንዱስትሪው ግብዓት በመሆን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ማለት ነው። የኢንዱስትሪው ዕድገት የሚወሰነውም በግብርናው እድገት ላይ በመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ ማፋጠን የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን መገነዘብ ተገቢ ነው።
አገራችን ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ መከተል በመቻሏ በአንድ በኩል ካፒታልን በቁጠባ ለመጠቀም ከማስቻሉም ባሻገር በስፋት ያሉንን መሬትና የሰው ጉልበትን በላቀ ደረጃ ለመጠቀም አስችሎናል። ግብርናው ላለፉት 15 ዓመታት ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢም ከፍተኛ ለውጥ ማሳየት ችሏል፤ የአርሶ አደሩ የፍጆታ አጠቃቀምም በአይነትም በመጠንም ለውጥ በማሳየት እሴት የተጨመረባቸውን የፋብሪካ ውጤቶች ተጠቃሚ ወደመሆን በመሸጋገር ላይ ይገኛል። ይህም በአገራችን በመስፋፋት ላይ ለሚገኙት የግብርና ምርቶችን ፕሮሰስ ለሚያደርጉ ቀላል ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ነው።
በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ዕውን ሲሆን ለኢንዱስትሪው ግብዕትነት አስተማማኝ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር የወጪ ንግዱንም መሻሻል እንዲያሳይ አግዟል። የወጪ ምርት ማደግ ለካፒታል ክምችት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው። በርካታ አርሶ አደሮች ዛሬ ላይ ወደ ኢንቨስተርነት በመሸጋገር በየገጠሩ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎችን በማልማት ላይ ይገኛሉ።
መንግስት ኢንዱስትሪዎች በአገራችን እንዲስፋፉ ለማድረግ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ደረጃ እንዲመራ የኢንደስትሪ ፓርኮችን የሚገነባና የሚያስተደድር የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን የተሰኘ ተቋም በ2007 ዓ ም በአዋጅ አቋቁሟል። ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያለማል፣ ያከራያል ወይም ይሸጣል። በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያለማል። መንግስት ለዚህ ተቋም በሰጠው ትኩረት ተቋሙ አድርጓል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከመገንባታቸው በፊት ወደ አምስት የሚሆኑ ኢንዱስትሪ ዞኖችና መንደሮች በአገራችን የነበሩ ሲሆን ሁሉም በግሉ ዘርፍ የተመሰረቱ ነበሩ። በመሆኑም እነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች ለአረንጓዴ ልማት፣ ለአካባቢ እድገት፣ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት እምብዛም ትኩረት የሰጡ አልነበሩም።
አሁን የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀድሞ ከነበሩት የኢንዱስትሪ ዞኖች ወይም መንደሮች በእጅጉ የተለዩ ናቸው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመንግስት የሚገነቡ መሆናቸው፤ ኢንቨስተሮች የአንድ መስኮት አገልግሎት ማለትም የገቢዎችና ጉምሩክ አገልግሎቶች፣ የኢንቨስትመንት ዕድሳት፣ የቪሳ ዕድሳት፣ የሥራ ፈቃድ ዕድሳት እና ሌሎች አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ማግኘታቸው፤ መሰረተ ልማት አቅርቦት (ንግድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም፣ውሀ ወዘተ) የተሟላላቸው መሆናቸው፤ በተጨማሪም እንደ ፍሳሽ ማጣሪያ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት የተሟላላቸው መሆናቸው እንዲሁም በየጊዜው ለሚያጋጥማቸው ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት መቻላቸው ተጠቃሾች ናቸው።
ከዚህም ባሻገር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የከተሞችን የተቀናጀ እድገት ያፋጥናሉ፣ ለዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ፣ በተመሳሳይ ለኢንደስትሪ ልማት የሚያግዝ መሰረተ ልማትን በቀላሉ ለማስፋፋት ስለሚያስችሉ ወጪ ቆጣቢ ናቸው፣ በፓርኮች አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ፋብሪካዎች በአንድ ክላስተር ማሰባሰብ ስለሚቻል የምርት ከብክነትን ያስወግዳሉ። ይህም አለም አቀፍ የምርት ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል፤ የከተማ መሬትን በአግባብ መጠቀም ያስችላል፤ በአነስተኛ ስፍራ ላይ ለበርካተ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል።
መንግስት የኢንደስትሪው ዘርፍ እንዲጎለብት እያከናወነ ካላቸው በርካታ ስራዎች መካከል በተመረጡ የአገራችን ትላልቅ ከተሞች የኢንደስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ ይገኛል። የእነዚህ ፓርኮች ግንባታ የአገሪቱን ቀጣይ እድገት ታሳቢ በማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመጋጋቢ ወይም ተመሳሳይ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች በአንድ አካባቢ እንዲደራጁ ታስቦ የክላስተር አሰራር የተከተለ ነው።
እየተገነቡ ያሉ ፓርኮች አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠብቁ በመሆናቸው ከአካባቢ ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገው የተገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክነት ነጻ ናቸው። የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀረፅ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ማሰለፍ ነው። አገራችን እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መከተል ያስፈለገበት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች የአገሪቱን እድገት ያማከሉ እንዲሆኑ እንዲሁም በእቅድ የሚመሩ ለማድረግ ነው።
መንግስት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለውን የኤሌክትሪክ ሃይል ለማሟላት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል። በቅርቡም ወደ ስራ የሚገቡ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ስራ ሲጀምር አገራችን ወደ አስራ አንድ ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ከታዳሽ ሃይል ማግኘት ስለምትችል በዘርፉ የሚታይ ችግር ይቀረፋል።
በተመሳሳይ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲስፋፉ የተመረጡት አካባቢዎች ለምርትና አቅርቦት ትራንስፖርት አመቺነት ተጠንቶ ነው። በዚህም አገሪቱን ከወደብ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመዓከል የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች እንዲሁም የባቡር መስመር በመዘርጋት ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታም የትራንስፖርት ወጪን መቀነስ የሚያስችል በመሆኑ ምርቶቻችን ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል። በመሆኑም መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማልማት በዕቅድ የተያዙ አካባቢዎች ሁሉ በባቡር መስመር እንዲያያዙ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ደረጃ መንግስት በአገሪቱ ከአስር በላይ የኢንደስትሪ ፓርኮችን የሚገነቡበትን ስፍራዎች በመምረጥ ወደ ግንባታ ተሸጋግሯል። ለኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከተመረጡ ስምንት አካባቢዎች አዲስ አባባ ሶስት ክላስተሮች ማለትም ለሚ አንድና ሁለት እንዲሁም ቂሊንጦ አካባቢ፣ ሃዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ባህርዳርና ጅማ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት የአገር ውጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች በቀላሉ ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ ስለሚያደርጉ ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ትርፋማ እንዲሆኑ እያደረጉ ነው። ምክንያቱም ባለሃብቶች ፋብሪካ ለመገንባት ቦታ የማፈላለግና ሼድ መገንባት ሳይጠበቅባቸው መንግስት ባዘጋጃቸው ሼዶች ውስጥ ፋብሪካቸውን በመትከላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት የተሸጋገሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ሼዶችን በማልት ለባለሃብቶች ማከራየትና መሸጥ መብት አለው። በሁሉም የኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሁሉም አገልግሎቶች ማለትም የገቢዎችና የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ስጪ ተቋማት ስለሚሟሉ የገቢም ሆነ የወጪ ምርቶችን ለመቅረጥም ሆነ ለሌላ ተግባራት ባለሃብቶች ውጣ ውረድ የለባቸውም። በተመሳሳይ መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም በቀላሉ ማግኘት ይችላል።
የኢንደስትሪ ሼዶች ግንባታ በአካባቢ ብክለት እንዳያስከትሉ ታሳቢ ተደርገው የሚገነቡ በመሆናቸው ለአከባቢ ተስማሚ ናቸው። የለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ደረቅንም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ አካባቢ እንዳይበክል ተደርጎ ስለተገነባ በአካባቢ ላይ ምንም ጉዳት የሚያስከትል አይደለም። ፍሰሽ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታ በአግባብ የተዘረጋ በመሆኑ ፋብሪካዎቹ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ብክነት የለም። ይህ አሰራር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችን አንዱ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀረፅ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣትና አገራችንን ከበለጸጉት ሀገራት ጎን ማሰለፍ ለልማታዊ ባለሀብት ቀጥተኛ ድጋፍ በመስጠት የኢኮኖሚ ልማቱ ዋና ሞተር እንዲሆን ለማስቻል ነው። የግብርና ግብዓቶችንና ጉልበትን በሰፊው በሚጠቀሙ፣ ከፍተኛ እሴት በሚጨምሩና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ሁነኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም ባላቸው ቀላል ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው። በዚህም ባለፉት አመታት መንግስት በአግሮ ፕሮሰሲንግ መስክ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው።