የጎራ መደበላለቅ አትፍጠሩ /ኢብሳ ነመራ/
በያዝነው ወር አጋማሽ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ሁለት ተቃራኒ ዜናዎች በአንድ ላይ ተሰራጭተው ነበር፤ ጎንደር ከተማን የሚመለከቱ ዜናዎች። አንደኛው ዜና በጎንደር ከተማ በሁለት ቢሊዬን ብር ወጪ ለሚገነባው የጨርቃ ጨርቅና አልባሣት ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ የሚል ነው፤ ሌላኛው በጎንደር 10ኛው ቦብም ፈነዳ የሚል ነው። ጎንደር ሰሞኑን ቦምብ ስለመፈንዳቱ ከገለልተኛ ወገን ያገኘሁት መረጃ ባለመኖሩ እውነት የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁለቱንም ዜናዎች የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። ሁለቱም ዜናዎች የስኬት ዜናዎች ናቸው፤ አንዱ የልማት እቅድ ስኬትን፣ ሌላኛው ደግሞ የጥፋት እቅድ ስኬትን ያበሰሩ ዜናዎች ናቸው። በሁለቱም ዜናዎች የተጠቀሱት ስኬቶች ሠላማዊ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው። አንደኛው አካባቢውን በማልማት የጎንደር ነዋሪዎችን በሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ለህዝብ የተገባን የልማት እቅድ ማሳካት፤ ሌላኛው ሠላማዊ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን ህይወት በመቅጠፍ፣ አካል በማጉደል፣ ንብረት በማውደም የከተማዋን ህዝብና መንግሥትን በማስፈራራት የፖለቲካ ዓላማን ማሳካት። ልዩነቶችም አሏቸው፤ ፍጹም በተቃራኒ ጠርዝ ላይ የሚያቆም ልዩነት። አንደኛው ልማት ሲሆን ሌላኛው ሽብር ነው። ሽብር ከልማት አኳያ ሲታይ ይህን ይመስላል።
እንግዲህ፣ የሽብርተኝነት ነባር የዓለማችን ክስተት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጎልቶ የወጣ ክስተት ለመሆን በቅቷል። ሽብርተኝነት በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ነው። ሠላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ህዝብ በፍርሃት እንዲዋጥ በማድረግ በውክልና ሥልጣን የተሰጠው መንግሥት የአሸባሪዎቹን ኃይማኖታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ወይም ፖለቲካዊ ፍላጎትን እንዲቀበል እንዲጠይቅ ለማስገደድ የሚደረግ ሥልት ነው። በሌላ በኩል የህዝቡን ሠላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ በህዝቡ ላይ የሚፈፀም ዘግናኝ የሽብር ጥቃት እንዲቀርለት የአሸባሪዎቹን ጥያቄ እንዲቀበል የሚያስገድድ አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባትን ያለመ ሥልት ነው።
የሽብር ጥቃት በሽምቅም ይሆን በመደበኛ ጦርነት ውጊያ ገጥሞ በወታደራዊ የበላይነት የማግኘትን ሥልት ስለማይከተል ወታደራዊ ኃይል ዋነኛ ዒላማው አይደለም። የሽብር ጥቃት ሥልት መድረሻ ህዝብ በፍርሃት እንዲርድ፣ መንግሥት በፍርሃት እንዲንበረከክ ማድረግ በመሆኑ ዋነኛ ዒላማው ሠላማዊ ዜጎች ናቸው። በመሆኑም የትኩረት ነጥቦቹ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው ሠላማዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉባቸው ሥፍራዎች ናቸው። የሽብር ጥቃት ዓላማ በበርካታ ሰዎች ላይ ፍርሃት ማሳደር በመሆኑ የጥቃቱ ውጤት ዜና በስፋት እንዲሰራጭ ማድረግ ይፈለጋል። በሌላ አነጋጋር አሸባሪዎች ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ይፈልጋሉ። የጥቃቱ ወሬ ካልተሰራጨ የሽብር ጥቃት የከሸፈ ያህል ነው የሚቆጠረው። ታዲያ ወሬው እንዲዳረስ ወይም ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ የሽብር ርምጃው ሰለባ ሠላማዊ ሰዎች ቁጥር በርካታ እንዲሆን፣ የጥቃቱም ዓይነት ዘግናኝ እንዲሆን ይፈለጋል። በአጠቃላይ የሽብርተኝነት ስኬት የሚለካው ሠላማዊ ሰዎች ላይ ባደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት ልክ፣ በጉዳቱ የዘግናኝነት መጠንና ወሬው በተዳረሰበት ስፋት ልክ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተለያዩ ቡድኖች የሽብር ዒላማ ሆና ቆይታለች። በተለይ እስከ 1999 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ንጹኃን ኢትዮጵያዊያን ሞትና አካል መጉደል ምክንያት የሆኑ በርካታ የሽብር ጥቃቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያንን የሽብር ጥቃት ዒላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች መኖራቸው ይታወቃል። በውጭ አገር በተለይ ይፋ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሥር ተሸሽገው የሽብር ጥቃት ከሚፈጽሙት ቡድኖች በተጨማሪ፣ እንደማንኛውም የዓለም አገር የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ሥጋትም አለባት። በአገሪቱ ጠላቶች ሥር ተጠልለው በይፋ የሽብር ጥቃት አውጀው ከሚንቀሳቀሱት መካከል ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ብለው የሚጠሩ እንዲሁም ግንቦት 7 የተባለው ቡድን ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት የመፈፀም ዓላማ እንዳላቸው የታወቀው በሥውር ክትትል በተገኘ የደህንነት መረጃ አይደለም። ቡድኖቹ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሽብር ጥቃት የመፈፀም ሥልትን እንደሚጠቀሙ በይፋ አውጀዋል።
ያም ሆነ ይህ፣ የኢፌዴሪ መንግሥት ይህን የአገሪቱ ህዝብ ላይ በይፋ የታወጀ የሽብር ጥቃት ለመከላከል አሽባሪዎቹን ለይቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት አስፈርጇል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት 7፣ አልሸባብና አልቃይዳ የተባሉ ቡድኖችን ነው። የለየላቸውን (notorious) አሸባሪ ቡድኖችን በአሸባሪነት መፈረጅ ሠላማዊ የፖለቲካ ተቃዋሚ መስለው ህዝብ ውስጥ ሊወሸቁ የሚችሉበትን ጭንብል በመግፈፍ እንዲጋለጡ ለማድረግ ያግዛል። ሠላማዊ ተቃዋሚዎች ባለማወቅ ወይም በስህተት የአሸባሪዎቹ ቡድኖች መሸሸጊያና መጠቀሚያ ላለመሆን ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያግዛል። የአሸባሪዎቹን ጥቃቶች የመከላከል የክትትል፣ የምርመራና የፍርድ ሂደት የተቀላጠፈ እንዲሆንም ያግዛል።
የኢፌዴሪ መንግሥት የለየላቸው አሸባሪዎችን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማስፈረጅ በተጨማሪ፣ ሽብርተኝነትን መከላከል የሚያስችል የፀረ ሽብርተኝነት ህግ አውጇል። በ2001 ዓ.ም በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ያስፈለገው የሽብርተኝነት ድርጊት በባህሪው ከሌላ ደረቅ የነብስ ግድያ፣ ንብረት የማውደም የሽፍታና የውንብድና ተግባሮች የተለየ ባህሪ ስላለው፣ ይህን ልዩ ባህሪውን መሠረት በማድረግ ለመከላከል እንዲቻል ነው።
የኢፌዴሪ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ በአንቀፅ 3 ላይ የሽብርተኝነትን ምንነት ይተነትናል። በዚህ አንቀጽ መሠረት የሽብርተኝነት ድርጊት፣ የፖለቲካ ኃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የኅብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የአገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማግኘት ወይም ለማፍረስ፤ በሰው ላይ የሚፈፀም የግድያ ወይም የአካል ጉዳት የማድረስ፤ የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ የማጋለጥ፤ እገታ ወይም ጠለፋ የመፈፀም፤ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ፤ በተፈጥሮ ሃብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይም የባህል ቅርስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ፤ ማንኛውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ የማጋለጥ፣ የመያዝ፣ በቁጥጥር ሥር የማድረግ፣ የማቋረጥ ወይም የማበላሸት ርምጃዎችን ያጠቃልላል። እነዚህን ድርጊቶች ለመፈፀም መዛትም እንደ የሽብርተኝነት ድርጊት ነው የሚቆጠረው። በሽብርተኝነት የተገለጹትን ድርጊቶች ለመፈፀም መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳት ወይም መሞከር የተከለከለ መሆኑም በአንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል።
የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ አንቀጽ 6 ሽብርተኝነትን ማበረታታት የሚመለከቱ ድርጊቶችን ዘርዝሯል። ይህ አንቀጽ የሽብርተኝነት ድርጊትን ማበረታታት አስመልክቶ፣ ማንኛውም ሰው መልዕክቱ እንዲተላለፍላቸው የተደረገው የኅብረተሰብ አባላት በከፊል ወይም በሙሉ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጽሙ ወይም ለመፈፀም እንዲዘጋጁ ወይም እንዲነሳሱ፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታታቸው ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት ሆነ ብሎ ወይም በግድ የለሽነት ያተመ ወይም ያሳተመ ይላል።
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የሽብርተኝነት ወንጀልን ልዩ ባህሪ መነሻ ያደረገ የመከላከልና የምርመራ ርምጃዎችን እንዲሁም የማስረጃና የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን የሚመለከቱ አንቀጾችንም አካትቷል።
የዚህ የኢፌዴሪ የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ዓላማ አንድና አንድ ነው። ይህም የኢትዮጵያን ህዝብ ከሽብር ጥቃት መከላከል፣ ከሽብር ጥቃት ተጠብቆ በሠላም የመኖር፣ የመልማትና የተሻለ ህይወት የመኖር ዋስትናውን ማረጋጋጥ ብቻ ነው። የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ሠላማዊ ዜጎች፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ቡድኖችን ወይም ድርጅቶችን ሥጋት ላይ የሚጥል አንዳችም ድንጋጌ የለውም። በህገ መንግሥቱ ላይ ከሰፈሩ የሰብዓዊ መበቶች፣ ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች ወዘተ…ጋር የሚቃረን አንድም አንቀጽ የለውም።
ይሁን እንጂ፣ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ገና በረቂቅነት ደረጃ ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በአገር ቤት ሠላማዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ በውጭ አገራት – የኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑ አገራት ጭምር የተሸሸጉ ቡድኖችና ግለሰቦች አፋኝ በማለት ሲያጥላሉት መቆየታቸው ይታወቃል። በአገር ውስጥም ቢሆን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቃወሙት ይደመጣል። አሁንም ህጉን የሚቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።
ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 የተሰኙት ቡድኖች አዋጁን መቃወማቸው ምንም የሚገርም ነገር የለውም። አዋጁ የሽብር ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱን ከማቀላጠፍ ባሻገር፣ አሸባሪዎች በህዝብ ውስጥ ተሸሽገው መንቀሳቀስ እንዳይችሉ በማድረግ ጥቃቱን የመከላከል ተጽዕኖም ስላለው በሠላማዊ ዜጎች ላይ ሽብር መፈፀም የሚያስችላቸውን መንገድ ስለሚዘጋባቸው ነው አምርረው የሚጠሉት። የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶችን ከዚያ ቀደም ከተፈፀሙ ጥቃቶች ጋር በማነጻጸር የአዋጁን ጥቃት የመከላከል አቅም መረዳት ይቻላል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ቡድኖች የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለበት 2001 ዓ.ም በኋላ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመደጋገፍ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አንዱም አልተሳካላቸውም። እናም የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ጠላታቸው ነው።
ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ህጋዊ እውቅና ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን የሚቃወሙበት ምክንያት ምንነት ጉዳዩን በገለልተኝነት ለሚመለከቱ ሁሉ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። አንድም ሠላማዊ ኢትዮጵያዊ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን እንደ ሥጋት እንደማይመለከት ግልጽ ነው። በሠላማዊ ዜጎች ዘንድ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ የህዝብ ስሜት በተቃራኒ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን መቃወማቸው ነው ነገሩን እንቆቅልሽ የሚያደርገው።
እርግጥ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ህዝብ መብትና ነጻነት፤ ጥቅምና ፍላጎት መሠረት አድርገው ከመንቀሳቀስ ይልቅ በሠላማዊ እንቅስቃሴ ሽፋን በውጭ አገር ያደፈጡ ህገ ወጥ ተቃዋሚዎችን ዓላማ እንደሚያስፈጽሙ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአንድ በኩል የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ አላላውስ ያላቸውን በውጭ ያሉ ቡድኖች ተልዕኮ ስለሚያስፈጽሙ፣ በሌላ በኩል ይህን ተልዕኮ በማስፈፀም ሂደት ራሳቸውም በፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል ስላለ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን እንዲቃወሙ ያደረጋቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ።
እንግዲህ ሠላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ህጋዊና ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ብቻ መርጠው በአገር ቤት የሚኖሩ መቶ ሚሊዬን ኢትዮጵያዊያንን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ላይ ያላችሁ እይታ ከስሜት የፀዳ፣ ተጨባጭ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የህጉን ይዘትና ዓላማ ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። የሠላም ፈላጊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት አስጠብቃለሁ እያሉ በሌላ በኩል የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን መቃወም የአስመሳይነት አካሄድ ነው። እናም ልዩ ሥውር ተልዕኮ የማስፈፀም ቃል ኪዳን የሌለባችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውዥንብር ፀድታችሁ ረድፋችሁን ለዩ፤ የጎራ መደበላለቅ አትፍጠሩ።