Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፓርላማ አባላት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ሚዲያ መሆን አልቻለም አሉ

0 836

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • የመንግሥት ባለሥልጣናት በዘገባ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ተብሏል
  • ኮርፖሬሽኑ የቀረቡበትን ወቀሳዎች ተቀብሏል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የሥራ አፈጻጸም የቆመለትን ዓላማ የማይወክል፣ የሕዝብ ድምፅ ከመሆን ይልቅ በባለሥልጣናት የሚታዘዝ መሆኑን በመግለጽ የሰሉ ትችቶችን ሰነዘረ፡፡

ፓርላማው የኮርፖሬሽኑን የሥራ ኃላፊዎችንና የቦርድ አመራሮችን ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመጥራት ነው ትችቱን የሰነዘረው፡፡ ‹‹አንዳንድ ባለሥልጣናት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች፣ ኤዲተሮችና ጋዜጠኞች በቀጥታ በስልክ፣ በጽሑፍ መልዕክት ዜናም ሆነ ፕሮግራም እንዳይሠራባቸው፣ እንዲቀር ወይም እንዲሻሻል የሚፈጥሩት ተፅዕኖ እንዳለ ይሰማል፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ አባል አቶ ተክሌ ተሰማ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ በተፅዕኖ በተጠለፉ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ላይም ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ አልማዝ መሰለ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ ‹‹የምክር ቤቱን ሥራዎች በተመለከተ አንዳንድ የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና የግል ሚዲያ ተቋማት ሥነ ምግባርን በጠበቀና በተሟላ ሚዛን ሲዘግቡ የሕዝብ ሚዲያ የሚባለው ኢቢሲ ሥራዎች በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት የላቸውም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ብቻ የሚያጎሉና የኅብረተሰቡን ችግሮች የማይዳስሱ መሆናቸውን በማንሳት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አቶ ጥላሁን ጅግሶ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ኮርፖሬሽኑ ወደ ፓርላማ የሚልካቸው ጋዜጠኞች በተጻፈ የአስፈጻሚ ሪፖርት ብቻ ዘገባ የሚሠሩ፣ ፓርላማው አቅጣጫ ሰጠ ሳይሆን ሚኒስትሩ እንዲህ አሉ የሚያዘወትሩ፣ እውነታዎችን አዛብተው የሚያቀርቡ ናቸው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ከሚተላለፈው ይዘት ይልቅ ማስታወቂያ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ፣ ማስታወቂያዎቹም አሰልቺ መሆናቸውን አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኮንን የሚዲያ ተቋሙ ሕዝባዊ ኃላፊነት እንዳለበት፣ እንዲሁም በራሱ ገቢ መተዳደር ያለበት በመሆኑ የንግድ ፍላጎቱ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በወር 18 ሚሊዮን ብር የደመወዝ ወጪ ያለበት ተቋም መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንን ወጪ ለመሸፈን ተቋሙ ወደ ንግድ እያዘነበለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓላማውን ለማሳካት ፈተና እንደሆነበት የጠቆሙት አቶ ሥዩም፣ ከዚህ ፈተና ለመውጣት መንግሥት የበጀት ድጎማ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሙሉ ለሙሉ ያመኑት አቶ ሥዩም ይህንን ችግር በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት ችግርን የተመለከተ ዘገባ በተሠራበት ወቅት የሜቴክ (የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን) የሥራ ኃላፊዎች በሜቴክ ስለተመረተ አውቶቡስ መስሏቸው እንደደወሉ አስታውሰዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችም ለባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ምቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛው ሠራተኛ እርስ በርሱ ለመጠፋፋት ጥረት የሚያደርግ፣ የራስ ጥቅም የበዛበትና ተቋማዊ የአስተሳሰብ አንድነት የሌለበት መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ዘገባዎች ማለትም ‘እንደ አንድ ለአንድና አሳሽ’ በተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ፣ ‹‹ባለሥልጣናትን እንደዚህ አታፋጡ›› የሚል ወቀሳ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ጠንካራ ኤዲተር (አዘጋጅ) የሌለው ተቋም ነው ሲሉ በግልጽ አምነዋል፡፡ ‹‹ያሉን ኤዲተሮች ፕሮፌሽናል አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ድርጅቱ የቆመለትን መሪ መፈክር ‹‹የህዳሴና የብዝኃነት ድምፅ›› የሚለውን አይወክልም ብለዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ግልጽነት ካደነቁ በኋላ፣ ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት መንግሥት የበጀት ድጎማ ሊያደርግ እንደማይገባና ችግሩ የሪፎርም እንጂ የበጀት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ተቋሙ ፈርሶ በድጋሚ ይመስረት እስከማለት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ግን፣ ‹‹ችግሩን ሰምተን ብቻ የምንተወው አይደለም፡፡ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ለፓርላማው ነው፡፡ ስለዚህ የባህል፣ የቱሪዝምና የመገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሚቀጥለው ሳምንት የውሳኔ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ፤›› ሲሉ አዘዋል፡፡ reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy