Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጅምሩን ማስቀጠል ከቻልን

0 318

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጅምሩን ማስቀጠል ከቻልን /አባ መላኩ/

በ2025 … የአገራችን ባለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ  ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።  አንዳንዶች ይህን የአገራችንን ፈጣን ዕድገት  የውጤታማ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስኬት ማሳያ በማለት ይጠሩታል።  አገራችን ያላትን መሬትና በአብዛኛው ወጣት የሆነ በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ሃይል እንጂ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት ነደጅ ወይም ሌላ ሃብት እስካሁን ባለው ሁኔታ የላትም። ይሁንና መንግስት አገሪቱ ያላትን ሃብት በአግባብ  ማቀናጀት በመቻሉ ፈጣን እድገት በተከታታይ ማስመዝገብ ችሏል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት አላቸው ከሚባሉ አገሮች የምትመደብ አይደለችም። እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትም በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በመንግስትና ህዝብ ጥረት የግብርናውን  ዘርፍ በማልማት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የዓለም ኢኮኖሚ በተንገዳገደበት፣  የሸቀጦች ዋጋ ክፉኛ ባሽቆለቆለባቸው የዛሬ አስር አመት ገደማ እንኳን የአገራችን ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ ዕድገት  በማስመዝገብ ላይ ነው። በዚህ ፍጥነት በመጪዎቹ አስር አመታት የምንቀጥል ከሆነ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደምትሰለፍ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የኢፌዴሪ መንግስት ነባራዊ ሁኔታዎችን መርምሮ አገሪቱ ያላትን ሃብት ማቀናጀት  በመቻሉ በግብርናው ዘርፍ ላይ ርብርብ በማድረጉ አገሪቱን በለውጥ ጎዳና እንድትገግዝ አስችሏታል።  በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ  መንግስት አዲስ ስትራቴጂ በመነደፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚ  ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የሚየስችሉ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው። ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት ዋንኛው ነገር የሃይል አቅርቦትን ማሳደግ ነው።   

 

የኢፌዴሪ መንግስት  ግብርናው ላይ ጠንክሮ መስራት በመቻሉ በአገር ደረጃ በምግብ ሰብል ምርት ራሷን  ችላለች። የምግብ ሰብል ምርት ፍላጎትን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ  መንግስት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው።  በአገራችን የመስኖ ልማት ስራዎች በመስፋፋት ላይ ናቸው። ልምድ በቤተሰብ  አገሪቱ ያላትን  ከፍተኛ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃ  በመጠቀም ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን  ለአካባቢው አገሮች ጭምር  ለውጥ  ማምጣት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነች። ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ መንግስት  በአገሪቱ የውጭና የአገር ድህንነት ፖሊሲ ላይ ኢትዮጵያ ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ካለባት ያላትን የተፈጥሮ ሐብቷን በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ መቻል አለባት በሚል ትክክለኛ አቋሙን አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በፖለቲካው ረገድ እንደአፍሪካ መሪነቷ ሁሉ በኢኮኖሚውም የቀጠናውን አገሮች  ጥቅም ለማስተሳሰር የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን  በማከናወን ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ካሉ የአካባቢውን ህዝቦች ከሚያስተሳስሩ  ፕሮጀክቶች መካከል የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶቿ ተጠቃሾች ናቸው። አገራችን ያላትን  ሃብት  በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የራስዋን ፍላጎት ከማሟላት አልፋ ለጎረቤት አገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል  በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ  ማግኘት  እንዲሁም የቀንዱን አካባቢ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር  በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ማስፈን የኢፌዴሪ መንግስት ዋንኛ የትኩረት መስክ  ነው።

አሁን እየተመለከትን ያለነው የኢትዮጵያ ራዕይ እውን እየሆነ ነው። ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት ከ300 ሜጋ ዋት እጅግም ያልዘለለ የነበረው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አሁን ላይ ከአራት ሺህ በላይ ደርሷል። በቅርቡም ይህ አሃዝ ከ10 ሺህ እንደሚበልጥ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻልባቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም በመፋጠን ላይ ነው። ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ከምታደርጋቸው ጥረቶች መካከል የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ለአብነት አነሳሁ እንጂ በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ በትላልቅ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ በአየር ትራንፖርት ማስፋፋት እያከናወነቻቸው ያሉ ፕሮጀክቶችም ከፍተኛ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ናቸው።

ቀጠናውንም ሆነ አህጉሩን በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስተሳሰር ጥረት ያደረገ እንደኢትዮጵያ ያለ አንድም አገር የለም። ከዚህም ባሻገር በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገራት  በመምራት ላይ የምትገኝ  አገር ለመሆን በቅታለች።  ከዚህ ጎን ለጎንም በርካታ የሰላም አስከባሪ ሃይል ግጭት ወዳለባቸው የአፍሪካ አገራት በመላክ  አካባቢው እንዲረጋጋ  በማድረግ ረገድ  አገራችን ግንባር ቀደም ሚናዋን በመወጣት ላይ ነች።  ይሁንና የኢትዮጵያን ጥረት አንዳንድ አገራት በቅንነት ባይመለከቱትም እንደጅቡቲና ሱዳን ያሉ  አገራት ደግሞ  የኢትዮጵያን ጥረት  በግልጽ ምስክርነት መስጠት ችለዋል።     

ኢትዮጵያና ግብፅ ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ቁርኝት ያላቸው አገራት ቢሆኑም፤ በዓባይ ወንዝ ምክንያት ግንኙነታቸው የሚጠበቀውን ያህል ጠንካራ አይደለም፡፡ ለዚህም ግብጽን በየጊዜው ሲመሯት የነበሩት መንግስታት የዓባይን ጉዳይ የውስጣቸውን የፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃ መሣሪያ አድርገው ሲጠቀሙበት በመቆየታቸው ሳቢያ ነው፡፡ መንግስታቱ ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃን መጠቀም ከጀመረች አገራቸው ለከፍተኛ አደጋ እንደምትጋለጥ በማስመሰል ህዝቡን ሲያደናግሩት ኖረዋል። የቀድሞ የግብጽ መንግስታትና ፖለቲከኞች የቅኝ ገዥዎች ውል በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ከውሃው አንድም ሊትር መጠቀም እንደሌለባት ለህዝባቸው ሲገልጹ ስለነበር ህዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ለዓባይ  ከ85 በመቶ በላይ  ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያን፤ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የበይ ተመልካች እንድትሆን፣ ከወንዙ የመጠቀም መብት እንደሌላት  ተደርጋ ነበር። ይሁንና ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው የኢትዮጵያን ህዝቦች መብትና ጥቅም የሚጠይቅና የሚያስጠብቅ ጠንካራ መንግስት መመስረት ተችሏል። የኢትዮጵያ መንግስት የሚያራምደው ፍተሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህ የአገራችንን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱን አገራት ህዝቦች ከወንዙ ፍተሃዊ ተጠቃሚነት መብትን ያረጋገጠ ነው። ለዓባይ ውሃ ፍተሃዊ ተጠቃሚነት  መርህ መስፈን የአንበሳውን ድርሻ የተወጣችው ኢትዮጵያ ናት። በዚህ ሁላችንም በመንግስታችን አቋም እንድንኮራ አድርጎናል።  

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ቀድሞ የነበሩ የግብጽ መንግስታት ዓባይ የሣሳት ማጥፊያ የውስጥ ትኩሳት ማብረጃ መሳሪያ  አድርገውት ኖረው ነበር። ህዝቡ ውስጣዊ ችግሮቹን እንዳይመለከት የአባይ ጉዳይ ዋንኛ የማስፈራሪያ ጉዳይ በአጠቃላይ የአጀንዳ ማስቀየሻ በማድረግ  አርፈህ ካልተጠክ ኢትዮጵያ ዓባይን ልታስቀርብህ ነው፤ በጥም ትሞታለህ፣ ማደናገሪያ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ልማትና ዕድገት በመልካም እንዳይመለከተው ኖረው ነበር። ይሁንና አሁን እውነታው ገሃድ ወጥቷል። የኢፌዴሪ መንግስት  አብሮ ማደግ አብሮ መለወጥ እንደሚቻል በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አስመስክሯል።

የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን አገሮች  ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍኑና ዘላቂ ተጠቃሚነትና የሚያረጋግጡ  ፕሮጀክቶችን ነድፎ  በመተግበር  ላይ ነው። አገራችን ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እጅ ለእጅ ተያይዛ የማደግና በሰላም አብራ የመኖር ፍላጎት እንዳላት በተግባር አሳይታለች።  ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን የሚከተለው  የኢትዮጵያ መንግስት አገሩን ብቻ ሳይሆን  የአካባቢው አገሮችም የሚጠቀሙበትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  በመተግበር ላይ ነው። አገራችን የጀመረቻቸው ተጠቅሞ የመጠቀም መርህ በሁሉም መስፈርት ተመራጭነት ያላቸው ናቸው።

የኢፌዴሪ መንግስት በባህሪው ህዝባዊነትን ተላበሰ መንግስትነ ነው። በመሆኑም የሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች  ሁሉ ከጎረቤት አገራት ጭምር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያራግጡ እንጂ ኢትዮጵያን ጠቅመው ሌላውን የሚጎዱ አይደሉም። በአካባቢው አገሮች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚቻለው  የአንዱ ዕድገት በሌላው ጉዳት ወይም ኪሳራ ላይ የተመሰረተ  ካልሆነ ብቻ ነው። ለዚህም ነው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋንኛ መሰረቱ የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ነው።  ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ  ስትቀርጽ ጀምራ  የአካባቢውን ሁኔታ በአግባብ በመተንተን የህዝቦችን ዘላቂ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የነበሩ የግብጽ መሪዎች የሄዱበትን መንገድ ከመከተል ይልቅ ሁሉም አሸናፊ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መከተልን  መርጣለች። ኢትዮጵያ እንደአፍሪካ ህብረት እንደመስራችነቷ መቀመጫነቷ እንዲሁም የቀጠናው ፖለቲካልና ኢኮኖሚያዊ መሪነቷ ይህን የሚመጥን ተግባራትን በማከናወን ላይ ነች። የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሁሉ ከአገራችን አልፈው ጎረቤት አገራትን የሚጠቅሙ፣ መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክሩ፣ የአካባቢው አገሮች ተያይዘው የሚያድጉበትን  መንገድ የሚተልሙ ናቸው።  የአገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የጎረቤት አገራትን ችግር የሚጋራና መፍትሔ አፈላላጊ በመሆን እንጂ ኢትዮጵያ በየትኛውም የጎረቤት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ  ይከለክላል። ይህ የመንግስታችን ባህሪ ማንነት ትላንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ወደፊትም የሚኖር ለአገራችን መለወጥ መሰረት ነው፡፡

የአገራችን ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው።  ይህን ዕድገት ለማስቀጠል  ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ይፈልጋል። በመሆኑም መንግስት ከፍተኛ የሃይል ማመንጫዎችን  በመገንባት የሃይል ፍላጎታችንን  በማሟላት እንዲሁም ለአካባቢው አገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ  ለማግኘት  የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን  በመተግገበር  ላይ ይገኛል። መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የያዘውን የአገሪቱን የሃይል አቅርቦት ወደ የ10ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ  የያዘው እቅድ የጊዜ መጓተት ቢታይበትም ማሳካት ግን ተችሏል።  ይህ እጅግ የተለጠጠ ዕቅድ በታዳጊ አገር ይቅርና በስልጣኔ ገፍተናል በሚሉ አገሮች  በአምስት ዓመት መተግበር ከባድ ቢሆንም አገራችን ግን እውን አድርጋዋለች።

በተመሳሳይ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው። በዚህ ወቅት የሃይል አቅርቦቱን ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ በማቀድ መንግስት ለተግባራዊነቱ በመስራት ላይ ይገኛል። ይህን ዕቅድ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ  እንደቀድሞው ሁሉ ያላሰለሰ ጥረቱን ማድረግ ይጠበቅበታል። የአገራችንን ህዳሴ እውን የሚሆነው በሁላችንም ጥረት በመሆኑ በተቻለን አቅም ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል።   

    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy