Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግብፅ ወደ ናይል ትብብር ማዕቀፍ ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግብፅ ወደ ናይል ትብብር ማዕቀፍ ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ የትብብር ማዕቀፍ አባል ሃገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውድቅ ማድረጉ ተገልጿል።

የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፈጥሮ ሀብትን በጋራና በፍትሃዊነት ለመጠቀም፥ ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኬኒያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የተስማሙበት ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስቱ አባል ሃገራት ስምምነቱን በምክር ቤቶቻቸው ሲያፅድቁ ሌሎች አባል ሃገራት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

የትብብር ማዕቀፉን አንቀጾች ባለመቀበል ግብፅ ከትብብሩ ብትርቅም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የትብብሩ አንቀጾች እየተቀበለች መምጣቷን፥ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ጌታሁን ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ግብፅ ወደ ናይል ትብብር ማዕቀፍ ለመመለስ ጥያቄ አቅርባ፥ ከአባል ሃገራቱ በተዋቀረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተመረጡ የሱዳን፣ ሩዋንዳና ዩጋንዳ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ሲመረምሩ ቆይተዋል።

በመጋቢት ወር በዩጋንዳ ኢንተቤ በተደረገው የሚኒስትሮች ጉባኤ ግብፅ ወደ ትብብር ማዕቀፉ ለመመለስ ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ሆኗል።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ጌታሁን፥ ግብፅ በ1959 የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት መሰረት የውሃ አጠቃቀም ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል የሚል ሀሳብ ይዛ መቅረቧ ጥያቄው ውድቅ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራሉ።

የግብጽ ሃሳብ ኢትዮጵያ እንደሃገር የማትቀበለውና የትብብር ማዕቀፉ የቆመላቸውን ምሰሶዎች የሚያፈርስ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተፋሰሱ ሀብት ያልተጠቀሙ ሃገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የትብብር ማዕቀፉ ሲዘጋጅ እንደሃገር የተደረገው ክርክርም ይህን ለማስቀረት ያለመ እንደነበርም አንስተዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝ፣ አለቃቀቅና ማህበራዊ ተፅዕኖን አስመልክቶ ቀጣይ ጥናት እንዲያካሂዱ የተመረጡት ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎችም፥ ጥናቱን በምን መልኩ ለማካሄድ እንደተዘጋጁ ለሶስቱ ሃገራት ሪፖርታቸውን አቅርበው ሃገራቱ ምላሻቸውን ለኩባንያዎቹ ማቅረባቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም በጥናቱ ከግድቡ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ባለፈ ያለውን አወንታዊ ተፅዕኖና ጠቀሜታ በጥናቱ እንዲካተት ሃሳቧን አቅርባለችም ነው ያሉት።

ባለፈው ወር በግብፅ፣ ትናንት ደግሞ በአዲስ አበባ ሶስቱ ሃገራት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነት በተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ ኩባንያዎቹ ጥናት ማካሄድ ጀምረዋል።

በሁለቱ ውይይቶች ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ በቀጣይ በካርቱም የሶስትዮሹ ውይይት የሚቀጥል ይሆናል።

ሚኒስትሩ ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ለጣቢያችን እንደተናገሩትም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 58 ነጥብ 4 በመቶ ተጠናቋል።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy