Artcles

ሁለቴ መሳሳት ቂልነት ነው

By Admin

May 13, 2017

ሁለቴ መሳሳት ቂልነት ነው/ብ. ነጋሽ/

ብ. ነጋሽ

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ከመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ በዘጠና ቀናት ውስጥ በሃገሩ የሚኖሩ ዜጎች እንዲወጡ ማወጁ ይታወቃል። ይህ አዋጅ በሃገሪቱ በህገ ወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም ይመለከታል። አሁን አዋጁ ከታወጀ ከአርባ አምስት ቀናት  በላይ ተቆጥረዋል፤ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ/ም በአዋጁ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያበቃል።

በጊዜ ገደቡ ውስጥ የሚወጡ በህጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ መመለስ እንደሚችሉ፣ በመሆኑም ከሃገሪቱ በሚወጡበት ጊዜ የጣት አሻራ እንደማይሰጡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው አዋጅ ይደነግጋል። በአዋጁ የተሰጠውን ገደብ በማያከብሩት ላይ ደግሞ፣ በጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት አሰሳ ተካሂዶ ህገ ወጥ ነዋሪዎች በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ ነው የተደነገገው።

አዋጁን ችላ ብለው የሚቀሩ ሰዎች የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል። ከ15 እስከ 50 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የገንዘብ መቀጫ እንደሚጣልባቸው ነው አዋጁ የሚገልጸው። ከምህረት ጊዜው መጠናቀቅ በኋላ ለህገ ወጦች ከለላ የሰጠ ወይም የቀጠረ ግለሰብ ወይም ተቋም በሃገሪቱ የወንጀል ህግ መሰረት እንዲጠየቅ እንደሚደረግም አዋጁ ይገልጻል።

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው አዋጅ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞችን፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞችን፣ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎችን፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ የሌላቸውን፣ ለኡምራና ሃጂ ተጉዘው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ ምዕመናንን የሚመለከት ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት በህገወጥ መንገድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን በሰላም ወደሃገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ የጀመረው አዋጁ ይፋ በተደረገ ማግስት ነበር። የኢፌዴሪ መንግስት  ህግ ተላልፈው በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ/ም ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የሚመክርና አቅጠጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ልኮ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚህ መሰረት መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ሳይጉላሉ ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው የሚመልስ አስተባባሪ ኮማንድ ፖስት ተቋቁማል። በሀገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ስራውን የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቷል።

የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ጨምሮ ሁሉም የባለድርሻ አካላትን ያካተተ በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይልና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ አስመላሽ ኮማንድ ፖስት በሳዑዲ አረቢያ ዘጠኝ ማዕከላት ተቋቁሞ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ጅዳ ባለው ቆንጽላ ጽህፈት ቤት አማካኝነት ለዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። የሳኡዲ አራቢያ መንግስት ባስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሃገራቸው ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ከአራት ዓመት በፊት እንደተደረገው ወደ የመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትና ቀጣይ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት መዘጋጀቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሃገራዊና አለማቀፍ አጋር ድርጅቶችም ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበልና ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳውዲ አረቢያ ዜጎችን በማስመለስ ሂደት ላይ አብሮ ለመስራት ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ሃገራዊና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር መክረው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚሁ መሰረት በውይይቱ የተገኙ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው ከማስመለስ እስከማቋቋም ድረስ ከመንግስት ጋር አብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይ አለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (IOM) ከሳዑዲ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በመቀበልና መልሶ በማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል። እንዲሁም የጀርመኑ ጂ አይ ዜድ፣ የጉድሳ ማሪታን ማህበር፣ የኢትዮጵያ የስደተኞች ማህበር ከስደት የሚመለሱና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ልማት ኤጀንሲ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ክህሎትና ልምድ ያላቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ኤጀንሲው እንዳስታወቀው የተለያየ ክህሎትና ልምድ ይዘው ከሳዑዲ የሚመለሱ ዜጎች በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሥራ የሚያገኙበት ሰፊ ዕድል አላቸው።

ተመላሾቹ በሳዑዲ ቆይታቸው ባካበቱት ልምድ ሀገራቸው ላይ በአነስተኛ መነሻ ካፒታል አምራች የሚሆኑበት እድል እንደሚመቻችም ኤጀንሲው አስታውቋል። ክህሎትና ልምድ ኖሯቸው የመነሻ ካፒታል ለሌላቸው ተመላሾች ተጨማሪ ስልጠና፣ የማምረቻ ቦታና የማምረቻ መሳሪዎች በብድር የሚያገኙበት ዕድል መኖሩንም አመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የግል መገልገያ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ፈቅዷል። በዚህም መሰረት ተመላሾቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በሳዑዲ አረቢያ በኖሩበት ወቅት ያፈሯቸውን የግል መገልገያ ዕቃዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ ማስገባት ይችላሉ። ኢትዮጵያውያኑ ለዓመታት ይኖሩበት ከነበረው ሳዑዲ ዓረቢያ ተገደው ሲወጡ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት የሚችሏቸው 21 ዓይነት የግል መገልገያ ዕቃዎች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ከአነዚህ መሃከል የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የጋዝ ምድጃ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር፣ ፕሪንተር ወዘተ ይገኙበታል።

የኢፌዴሪ መንግስት በህገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ከላይ የተዘረዘረውን ጥረትና ድጋፍ የሚያደርገው የሳኡዲ አረቢያ መንግስትን ለማገዝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ የሚያዘው አዋጅ ቀነ ገደቡ አብቅቶ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኢትዮጵያውያኑ ላይ ሊደርስ የሚሉትን አስከፊ መንገላታትና በህግ ማስከበር ሰበብ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል ነው።

እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያኑ ወደሳኡዲ አረቢያ የተሰደዱትና በዚያ በህገወጥነት የሚኖሩት ለመዝናናት እንዳልሆነ ይታወቃል። የስራ እድል ፍለጋ እንዲሁም የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መኖር የሚቻልበትና ጠንክረው ከሰሩ ሃብት ማፍራት የሚቻልበት እድል አለ። ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የስራ እድልና ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተነስተው ወደመካከለኛ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ዜጎችን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

በተለይ መንግስት ለወጣቶች ያመቻቻው የስራ ፈጠራ እድልና ድጋፍ የዜጎችን የስራ እድልና የሃብት ፈጠራ የበለጠ ይደግፋል። ከሳኡዲ አረቢያ ለሚመለሱት ዜጎች ደግሞ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ መንግስት ገልጿል። በመሆኑም የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያስቀመጠው የግዜ ገደብ ተጠናቆ ሁሉንም ኢትዮጵያዊና መንግስትን የሚያሳዝነው እንግልትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመፈጸሙ በፊት ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ። ከአራት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠመውን አሳዛኝ ሁኔታ አስታውሱ። አንዴ መሳሳት ያለ ነው፤ ሁለቴ መሳሳት ግን ቂልነት ነው። አናም ያለፈውን አስታውሱ።