Artcles

ሁሉም ሰው ለዚህች ሃገር ሰላምና ብልጽግና የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት!!

By Admin

May 02, 2017

ሁሉም ሰው ለዚህች ሃገር ሰላምና ብልጽግና  የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት!!/ስሜነህ/

አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ተወግዶ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላም ቢሆን ተሃድሶዎችን በተለያየ ጊዜ አድርጓል፡፡ ኢሕአዴግ በድርጅት ውስጥ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት በ1993 ዓ.ም. ተሃድሶ አድርጎ ነበር ይታወሳል፡፡ ከዚያ ወዲህም  የተለያየ የተሃድሶ ንቅናቄዎችን ያደረገ ቢሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን ሰፋ ያለና ሁሉንም አመራርና የመንግሥት ሠራተኞችን  ጭምር ያሳተፈ ነው፡፡ ለዚህም ጥልቅ ተሃድሶ መነሻ ሁኔታዎች መመልከት ተገቢ ነው፡፡  

ከ2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም.በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች ሁከቶች ተቀስቅሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በኦሮሚያ በ15 ዞኖችና 91 ወረዳዎችና ከተሞች ውስጥ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት፣ ሥራ አጥነት፣ የልማት ፕሮግራሞች መዘግየት፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ አለመደረግ፣ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ለሁከትና ለግጭቱ መነሻ እንደነበሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በአማራ ክልልም ተከስቶ ለነበረው ግጭትና ተቃውሞ መንስዔው በተመሳሳይ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትሕ ማጣት፣ የቦታ አሰጣጥ ችግር፣ ኢፍትሐዊ ግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት እንደነበሩ በተመሳሳይ ተመልክቷል፡፡በዚህ አገራዊ ግጭትና ሁከት ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የሃገር ሀብት መውደሙን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አያይዞ ገልጿል፡፡

ለዚህ አገራዊ ቀውስና ተቃውሞ መንስዔ የሆነውን ጉዳይ ለመለየትና ለማወቅ ኢሕአዴግ ባደረገው ግምገማ የመንግሥት የአሠራር ብልሹነት እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ይህንን ለማረምና ለማስተካከል ደግሞ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በመጀመር አመራሩና የመንግሥት  ሠራተኛው እንደዚሁም በየደረጃው የሚገኙ አደረጃጀቶች በጥልቅ ተሃድሶው እንዲያልፉ አድርጓል፡፡

በዚህ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች የተደፈቁበት እንደነበር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታኅሳስ 22 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንዳረጋገጠ  ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በዚህ መስረት   ‹‹በየደረጃው በተካሄዱ የግምገማ መድረኮች፣ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ድረስ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር፣ እንዲሁም ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል አመለካከትና ተግባር ድርጅቱን፣ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንዲሆን፣ የህዳሴያችን አደጋዎች መሆናቸው እንዲጋለጡና በየደረጃው ብቁ ትግል የተካሄደባቸው መሆኑን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተግባብቶበታል›› ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከዘመናት የጭቆናና የግፍ ሥርዓት አውጥቶ ሰላም የሰፈነባት አገር መገንባት መቻሉ አያከራክርም።የሃገሪቱን ድንበር ከአሸባሪዎች የመጠበቅ አቅሙም የዳበረ መሆኑ በተመሳሳይ አያከራክርም። ያም ሆኖ ግን በዴሞክራሲያዊና በመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ብዙ የሚቀረው እንደሆነ ከላይ የተመለከቱት የግጭት ሰበቦች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለይ ከወጣቱ የሥራ ፈጠራ ውስንነት፣ ከሙስናና ከብልሹ አሠራር፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ወዘተ ችግሮች የኢሕአዴግ መገለጫዎች እስኪመስሉ ድረስ ስር ሰደው መገኘታቸውም የዚሁ ማሳያ ነው፡፡  

በዚህ የተነሳ ኢሕአዴግ ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮችን ከሥልጣን ማገዱ፤ማሰሩና እንደደረጃቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉ ተገቢ ነው።   የኢሕአዴግ በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄ የነበሩ መጥፎ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች ወደ ጥሩ የመለወጥ ዓላማን አንግቦ የተካሄደ የንቅናቄ መድረክ እንደሆነም ከእነዚህ እርምጃዎች መገንዘብ አይከብድም። በጥቅሉ የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞው የኢሕአዴግ መስመርን በማስተካከል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየትና ለእነዚህም ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያስቻለ ነው ብሎ ለመውሰድ ይቻላል፡፡

ከዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሌላኛው ቁምነገር መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለውይይት እንዲጋብዝ ማስቻሉ ነው። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር የኢሕአዴግ አንዱ አቋም እንደሆነም ጥልቁ ተሃድሶ አረጋግጧል ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር በመጀመር በአገሪቱ ያለውን የኃይል ሚዛን ሊያስተካክል የሚችል ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑ የሚያመላክተውም ይህንኑ ነው ፡፡

በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሲባል የአመራር ለውጥ ተደርጓል፡፡ ለውጡ ደግሞ ትምህርትን መሠረት ያደረገ መሆኑ  ሌላ በጎ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡በዚህ ንቅናቄ የአመለካከት ለውጥ ተፈጥሯል፡፡የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት እየተሄደበት ያለው  መንገድ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ይህ እንቅስቃሴ በየደረጃው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በዚህም መሪ ድርጅቱ በመምራት፣ ኅብረተሰቡ ደግሞ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡

ጥልቅ ተሃድሶው አገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደመለሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት  መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ማንኛውም የፓርቲ አካሄድ አስተማማኝ መሆኑ የሚለየው በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በመረዳት እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹  ይህንን የምናረጋግጠው ከሕዝባችን አመለካከት እንጂ ረብሻውን ከሚፈጥሩ ጥቂት ኃይሎች ተነስተን አይደለም፡፡ በዚህ ግምገማችን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ሕዝባዊ መንግሥት እንደመሆናችን መጠን መነሻችንም መድረሻችንም ሕዝቡ ነው›› ማለታቸው የማይዘነጋና  ነው፡፡

የአገሪቷን ስሟንና ክብሯን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ሳይባል በአገር ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር ያለበት መሆኑን የተመለከቱ አስተያየቶች በየመድረኮቹ ጎልተው ከወጡት መካከል ይገኙበታል። ከዚህ በፊት የነበሩትን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና የነበረውን ብሔራዊ አንድነት የበለጠ አጠናክሮ መሄድ ተገቢ እንደሆነ በመጠቆም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርስበትን መንገድ መቀየስ አንዱ ስትራቴጂ ይሆናል፡፡ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ደግሞ ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር  እያደረገ ያለውን ድርድር የበለጠ ማጠናከር ያለበት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡  

ጥልቅ ተሃድሶውና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች የነበራቸው ክፍተት ታርመውና ተስተካክለው ወደፊት የተሻለች አገር መገንባት ተገቢ ይሆናል። በዚህች አገር ላይ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለውን አማራጭ ይዞ መቅረብና ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ ጉልበትና አቅም ተሰጥቷቸው ሕዝቡ እንዲመርጣቸው መደረግ አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በዚህች አገር የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ዜጎች አማራጭ ማግኘት ከቻሉ፣ ከአማራጮች መካከል ደግሞ ያመኑበትን መምረጥ ከቻሉ፣ በጋራ ስለአገር መሥራት ቀላል ይሆናል፡፡ስለእያንዳንዱ ችግር ምንጭና መንስዔ ከኅብረተሰቡ ጋር መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ የጋራ መግባባቱ እንደ ድርጅት ከተደረሰ በኋላ ሳይዛነፍ ወደ ሕዝቡ መውረድ አለበት፡፡ ከዚህ  በመቀጠልም  በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለይቶ ከሕዝቡ ጋር መሥራት ተገቢ ነው፡፡