Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሊፈታ የሚገባው የፕሮጀክቶች ችግር !!

0 473

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሊፈታ የሚገባው የፕሮጀክቶች ችግር !!

                                                      ይነበብ ይግለጡ

ሀገራዊ የልማትና የግንባታ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የግዜ ገድብ ውስጥ መጠናቀቅ የሚገባቸው ናቸው፡፡ቀድሞውንም የባለሙያዎች ዝርዝር ጥናትና ዳሰሳ ተደርጎበት አዋጪና አዋጪ አለመሆኑ ታይቶ ምን ያህል ፋይናንስ እንደሚያስፈልገው በመንግስት እጅ የሚገኝ ገንዘብና አሊያም በብድር ከውጭ ከሚገኝ ገንዘብ አማራጩ ተወስዶ ይሁንታን አግኝቶ ከጸደቀ በኃላ ወደስራ የሚገባበት ሁኔታ ነው በአብዛኛው ሲታይ የነበረው፡፡

ሀገራችን ግዙፍና ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅምም ሆነ በውጭ ብድርና እገዛ ሰርታ ማሳየት ችላለች፡፡የሚሰሩት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተመልሰው የሚጠቅሙት ሀገርንና ሕዝብን ነው፡፡የታቀዱትን ፕሮጀክቶች ተረባርቦ በማሳካት በግዜ ገደቡ እንዲጠናቀቁ በማድረግ ረገድ የተሳካላቸውም ያልተሳካላቸውም አሉ፡፡በስኬት ያጠናቀቁትን ሳይሆን መፈተሽ የሚገባው በተሰጣቸው የግዜ ገደብ ያልተጠናቀቁትን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ ውሳኔ መስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡

ፕሮጀክቶች ለምን በተሰጣቸው የግዜ ገደብ አይጠናቀቁም? የችግሩ ትክክለኛ ምንጭ ምንድነው? በተመደበለት በጀት ሊያልቅ ያልቻለውስ ለምንድነው? ተጀምሮ የቆመበት የተጓተተበት ምክንያት በማኔጅመንቱ ችግር የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ባለማድረግ  ወይንስ ስራውን እንሰራለን ብለው የወሰዱት ተቋራጮች ቃላቸውን አክብረው ስራውን ለመስራት በለመቻላቸው? ጉዳዩ የሀገርና የሕዝብ ጉዳይ ስለሆነ የገቡትን ውል ባላከበሩት ላይ በተቀመጠው ውልና ሕግ መሰረት ምን እርምጃ ተወሰደ? ለደረሰውስ የንብረት የግዜ የሰው ኃይል ብክነትና ኪሳራ ስራ ለመስራት ተቀጥረው ስራው ሊሰራ ባለመቻሉ ለሚከፈለው የመንግስት ገንዘብ ኃላፊነቱን የሚወስደው ወገን ማነው ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎችን ማንሳት ግድ ይላል፡፡

የመንግስት ገቢ የሚገኘው ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብርና ታክስ ነው፡፡ይህ ገንዘብ በሌላ አገላለጽ የሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡በብድር መንግስት ከውጭ የሚያገኘውም ገንዘብ ቢሆን ሀገሪቱ በሂደት ብድሩን የመክፈል ግዴታ ያለባት በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው፡፡ተጀምረው በተሰጣቸው የግዜ ገደብ ባልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ በአብዛኛው የሚነሳው የክትትልና የቁጥጥር ማነስ ነው የሚለው ጉዳይ ሚዛን አይደፋም፡፡ ውኃ አይቋጥርም፡፡

በየፕሮጀክቶቹ ውስጥ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት ሰጥቶ ፕሮጀክቱን እየተከታተሉ ከዳር እንዲያደርሱ የመደባቸው ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ጥቅማ ጥቅማቸው የተከበረላቸው  ከመኪና እስከ ቤት ውሎ አበል ድረስ የተሟላላቸው ኃላፊዎች ይሄንኑ ከፍተኛ የመንግስትና የሕዝብን አደራ ከመወጣት ውጪ ሌላ ምንም ስራ የላቸውም፡፡

ስራውንና አፈጻጸሙን መከታተል፤ምን ያህል ደረጃ እንደደረሰ ማሳወቅ፤ችግሮች ካሉም ለመንግስት ሪፖርት አድርገው በአጭሩ እንዲፈቱ ስራው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ፕሮጀክቱም ለፍጻሜ እንዲደርስ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም፡፡ችግሮች በእርግጥም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ለመፍታት መጣር ነው የኃላፊዎች የስራ ድርሻ፡፡

ለዚህ ነው የተለያዩ ምክንያቶችን መስጠቱ ተቀባይነት የማይኖረው፡፡እንደነዚህ አይነት ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶች ፈጥነው ለችግሮቹ መፍትሄ በመሻት ወደ ስራ ሊገቡ ይገባቸዋል፡፡ሀገራዊ የልማት እድገቱንና ጉዞውን የሚያጓትት በመሆኑ የጊዜና የሀብት ብክነትም ስለሚያስከትል ወሳኝ የእርምት እርምጃዎች መውሰድ ተገቢ ነው፡፡

ለአብነት ያህል በቅርቡ የአርጆ ዴዴሳ መስኖ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ ባለመሰራቱ በፍጥነት የግንባታው ስራ እንዲጠናቀቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰጠውን ማሳሰቢያ መመልከቱ ይቀላል፡፡በሌሎችም በተጓተቱት ፕሮጀክቶች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ እየተከታተለ ስራው ፍጻሜ እንዲያገኝ መትጋት አለበት፡፡በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማሳሰቢያውን የሰጠው የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካና የመስኖ ፕሮጀክትን ከጎበኘና ከገመገመ በኋላ ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዳስታወቁት የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቱ የመጓተቱ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ መፍትሔ ሊሰጠውና ፈጥኖ ሊጠናቀቅ ይገባል፡፡የመስኖ ፕሮጀክቱ በ2003 ዓ.ም ሲጀመር በዚያው አመት መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር፡፡ዛሬ ስድስት አመት አልፎም አልተጠናቀቀም፡፡በአሁኑ ወቅት አፈፃፀሙ 48 ነጥብ 3 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርዓያ በመስክ ጉብኝቱ  ወቅት የመስኖ ግንባታውን ሂደት በተመለከተ ክትትልና ቁጥጥር አልተደረገም በማለት የገለጹት የችግሩን ክብደትና ግዝፈት ያሳያል፡፡የመስኖ ፕሮጀክቱ የተጀመረው ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ተመድቦለት ነው፡፡

ይህን ያህል በጀት ተመድቦለት ወደ ስራ ቢገባም በክትትልና ቁጥጥር ማነስ ምክንያት በወቅቱ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ተገምግሟል፤በተያዘለት የጊዜ ገድብ ሊጠናቀቅ አይችልም ነው ያሉት ሰብሳቢው፡፡ወደ ሸንኮራ ልማቱ የሚዘረጉ 90 እና 70 ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ያላቸው የውኃ መውረጃ ተፋሰሶች ግንባታም ተጓቷል፡፡ለዚህም ነው የመስኖ ውኃ መውረጃ ተፋሰሶች ግንባታን በተመለከተ ጨረታ ወጥቶ ግንባታው በፍጥነት መጀመር እንደሚገባው ሰብሳቢው ያሳሰቡት፡፡

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ካባ መርጋ በበኩላቸው ለመስኖ ግድቡ ፕሮጀክት ግንባታ ፋብሪካው የሚችለውን ክትትል እያደረገ ቢሆንም የተቋራጮች በስራ ላይ ያለመገኘትና የቁጥጥር ማነስ ይስተዋላል ነው የሚሉት፡፡ለሸንኮራ ልማቱ የሚዘረጋ የውኃ ተፋሰስ ግንባታን የሚመለከተው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መሆኑን በቅርብ ወደ ስራ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ለመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ የውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የአርጆ ዴዴሳ ግድብና ተጓዳኝ ሥራዎች ኃላፊ ኢንጂነር መርጊ ሚሊኬ የግድቡ ግንባታ የዘገየው ሥራው ከመጀመሩ በፊት በግብአት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች በአግባቡ ስላልተፈቱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደአሸዋ፣ ድንጋይ፣ ቀይአፈር እና መሰል ግብአቶች አቅርቦት ላይ በቂ ዝግጅት አልተደረገም ነው የሚሉት፡፡በተጨማሪም የዲዛይን ለውጥ ማስፈለጉ፣የተቋራጮች ዘግይቶ ወደ ሥራ መግባት እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማት ያለመኖር ከዋና ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንገድ መሰረተ ልማቶቹ በመጠናቀቃቸው በአካባቢው ያሉ የግንባታ ግብአቶችን መጫን በመቻሉ ተቋራጮቹ በሙሉ አቅማቸው ስራውን ስለጀመሩ ግንባታውን በአንድ አመት ከስድስት ወራት ውስጥ ማጠናቀቅ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ግድቡ 50 ሜትር ከፍታ እና 502 ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን በዓመት ሁለት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ በማጠራቀም እስከ 80 ሺህ ሔክታር የማልማት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy