Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕብረት የጎደለው የፀረ-አበረታች መድሐኒት ትግል

0 1,417

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በማንኛውም የሩጫ ውድድር ቀድሞ መገኘት አሸናፊ ያደርጋል፤ ያሸልማል፤ ክብር ያጎናፅፋል፡፡ በመሆኑም አትሌቶች የዘወትር ትጋታቸው ከፊት ለመገኘት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ትጋት በውድድር መም አልያም በልምምድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ስለስፖርቱ በሚመክሩ መድረኮችም ቢደገም መልካም ነው፡፡ እስኪ እኔም ጉዳዬን በትዝብት ልጀምር፡፡

ባሳለፍነው ዕሁድ፤ በአትሌቲክሱ ዓለም ትልቅ ስጋት የደቀነው ፀረአበረታች ቅመሞች ጉዳይና ተያያዥ ህጎች እንዲሁም የአድራሻ መረጃ መረብ አሞላልና የአትሌቶችን ድርሻ በተመለከተ፤ ለአንጋፋ አትሌቶችና የአትሌት ተወካዮች የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ተሳታፊዎች አርፍደው በመምጣታቸው ምክንያት መድረኩ ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይቶ ሊጀመር ተገዷል፡፡

ዕለቱ ዕሁድ እንደመሆኑ ማሕበራዊ ኑሮን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች መብዛታቸው ከግምት ይገባል፡፡ ነገር ግን ከተጋነነው መዘግየት ባሻገር አርፍደውም በመድረኩ የታደሙት አትሌቶችና አሰልጣኞች ቁጥር ከተጠበቀው በጣም ያነሰ መሆኑ አዘጋጆቹን እጅግ ቅር አሰኝቷል፡፡ በዚህ ድባብ የተጀመረው የረፋዱ መድረክ በሂደት እየተሟሟቀ መሄዱ አልቀረም፡፡ ለማንኛውም ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ፡፡

ዓለም አቀፍ ጫና

በዕለቱ ስለ አበረታች መድሐኒት ስጋትና በቀጣይ መወሰድ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲሁም ዕርምጃዎች ስልጠናውን የሰጡት በስፖርት ህክምና ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት የስፖርት ህክምና ባለሙያው ዶክተር አያሌው ጥላሁን ናቸው፡፡

ከረጅም ዓመታት ተሞክሯቸው እያጣቀሱ በማይሰለች አቀራረብ ስልጠናውን የሰጡት ዶክተር አያሌው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር እንዲሁም በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድሐኒት ተቆጣጣሪ ድርጅት በኩል የሚደረገው ግፊትና ጫና እየበረታ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

‹‹እስከአሁን በዶፒንግ የተያዙት ኢትዮጵያውያን ላይ የቁጥር ጥርጣሬ አላቸው›› በማለት የተቋማቱን ጫና ይገልጹታል፡፡ ይሄን ግፊት ሊመክት የሚችል ቀጣይ ሥራ ካልተከናወነ አደጋው ያስፈራል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የአትሌቲክስ ጀግኖች ሁሌም አሉ፤ ድሉም ይቀጥላል›› የሚሉት ዶክተር አያሌው፤ ወደፊት አትሌቲክሱ በዋናነት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ የሚችለው በዶፒንግ ምክንያት መሆኑን ያሳስባሉ፡፡

ስጋቱን ተከትሎ አምና የመጀመሪያው መድረክ ቢሰናዳም ‹‹እርሱ እሳት ማዳፈን ነበር›› ይሉታል፡፡ የአሁኑ ግን በተጠናከረ መልኩ የሚሠራበት ጥልቅ መርሐግብር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የአሁኑ ስልጠናም በአንጋፋዎቹ አትሌቶች ይጀመር እንጂ በቀጣይ ወደ ጀማሪዎቹም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ተለዋዋጩ ዶፒንግ

የስፖርቱን ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ የሚገኘው አበረታች መድሐኒት ውስብስብ ባሕሪያት እንዳሉት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከመገለጫዎቹም መካከል ከወራት ወይም ከዓመት በፊት ተራ መድሐኒት የነበሩ ንጥረ ነገሮች በአዳዲስ ሕግ ምክንያት ‹‹አበረታች መድሐኒት›› የሚል ፍረጃ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ለአብነትም 50 ሲ ሲ ጉሉኮስ የወሰደ አትሌት በዶፒንግ ሊያዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁንም በየልምምዱ ጉሉኮስን የሚሰጡ መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም ይሄ ተሞክሮ መቆም አለበት፡፡

ካለፈው የጥር ወር ጀምሮ ‹‹አበረታች ንጥረ ነገር ናቸው›› በሚል የተለያዩ የመድሐኒት ዝርዝሮች መውጣታቸው በመድረኩ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በዶፒንግ ዝርዝር ውስጥ ያልገባው የአስም መድሐኒትን ጨምሮ፤ ‹‹ትራማዶል›› የተሰኘው የራስ ምታት መድሐኒትም በተመሳሳይ መልኩ ተከልክሏል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አትሌት በመረጃ ክፍተት የማያውቀውን መድሐኒት ከመጠቀም እዲቆጠብ ያሳስባሉ፡፡

‹‹አናቦሊክ›› የተሰኘው ምግብ ተኪ እንክብልም በአዲስ መልክ ተከልክሏል፡፡ ቅጣታቸውም ከአራት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እገዳ እንደሚያደርሱ ተገልጿል፡፡ ‹‹ሜልዶኒየም›› የተሰኘውም መድሐኒት እ..አ በ2016 ዝርዝር ውስጥ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የኋላ ኋላ በቋሚነት ተከልክሎ ራሺያዊቷን አትሌት ሻራፖቫ ለቅጣት ዳርጓል፡፡ ሌሎችም የተለያዩ መድሐኒቶች በአዲሱ የክልከላ ዝርዝር ውስጥ በመካተታቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ፡፡

በመድሐኒቶቹ ሽፋን ላይ የሚለጠፈውን እንግሊዝኛ ፅሑፍ አንብቦ መረዳት ብቻ መድሐኒቱን ለመውሰድ በቂ እንደማይሆን የሚናገሩት ዶክተር አያሌው፤ በውጪው ሽፋን ላይ የሚሰፍረው አነስተኛ ፅሑፍ ብዙዎችን እያታለለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከባለሙያ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋቸዋል፡፡

ኧረ መላ መላ

ባለሙያው ፀረአበረታች መድሐኒት ትግሉን የተሳካ ለማድረግ በሰዶ ማሳደድ ሳይሆን በመሠረታዊ ስልጠናዎች ማስወገድ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ አትሌቲክሱ ዘመናዊነትን በፍጥነት መላመድ ሲሆን፤ እንደየእርቀታቸው ባሕሪ የስልጠና መንገዶችን መቀየስ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከልምምድ በኋላ በቂ የዕረፍት ጊዜ ማግኘት፣ ከተክለሰውነት ጋር አብሮ የሚሄድ ርቀትን መምረጥ፣ ከረጅም እስከ አጫጭር ርቀቶች የሚሆን ዘመናዊ የጂምናዚየም ልምምድ ማስፋፋት በተዘዋዋሪ አበረታች መድሐኒትን ለመከላከል እንደሚያስችሉ ታምኖባቸዋል፡፡

በስልጠናው አፅንኦት የተሰጠው ሌላው መፍትሄ አትሌቶች ከታሸጉ ምግቦች ይልቅ ወደ አገራቸው ተፈጥሯዊ ምግቦች እንዲያተኩሩ የሚለው ነው፡፡ በተለይም ታሽገው የሚቀርቡ ድጋፍ ሰጪ ምግቦች ሲለመዱ በሂደት ከሚያስከትሉት ችግር ባሻገር የትኞቹንም የኢትዮጵያ ምግቦች የሚተካ አለመኖሩን ያሰምሩበታል፡፡

ቀጣዩን መፍትሄ በተመለከተ ‹‹ችግሩን ለመከላከል ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል›› የሚሉት ዶክተር አያሌው፤ በፌዴሬሽኑ በኩል አትሌቶች ከማን ጋር እንደሚሠሩ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ለዚሁ ዓላማ በአሰልጠኝና በማኔጀር ስም የሚገቡ ብዙ የባሕር ማዶ ዜጎች ለችግሩ ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

ከመድሐኒቶቹ አይገመቴ መሆን ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመከላከልም ተከታታይ ስልጠናዎችን ለአትሌቶች፣ ለአሰልጣኞችና ለወኪሎች ከመስጠት ጎን ለጎን ለጤና ባለሙያዎችም በስፋት ማስገንዘብ ይገባል፡፡ ለዚህም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የመድሐኒት አስመጪ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው አካላት አብረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሲጠቃለል

በዕለቱ የሰዓት አለማክበርና ጨርሶም የመቅረቱ ክፍተት የተፈጠረው ከመድረኩ አዘጋጆች ወይስ ከተጋባዦች? የሚለው ጥያቄ፤ የሁለት ጎራ አለመግባባትን አስተናግዷል፡፡ በአንድ በኩል መድረኩን በበላይነት ያሰናዳው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ ግብዣውን በአግባቡ ለተሳታፎዎች ማድረሱን ሲገልጽ፤ አንዳንድ አትሌቶች በበኩላቸው የመድረኩ ቅድመ ዝግጅትና ጥሪ በቅጡ የታሰበበት አለመሆኑን ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

የሆነው ሆኖ ፌዴሬሽኑ በአበረታች መድሐኒት ምክንያት ጥቁር ጥላ ያጠላበትን የአገሪቱን አትሌቲክስ ስፖርት ለመታደግ መሰል መዘናጋቶች እንደማያስፈልጉ በምክትል ፕሬዚዳንቱ አትሌት ገብረእግዚሐብሔር ገብረማርያም በኩል ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ አስፈላጊው ማጣራትም እንደሚደረግ በመጠቆም፡፡

በመድረክ የተገኙ ስመ ጥር አትሌቶችም በዕለቱ ሳይመጡ የቀሩ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ወኪሎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምልከታ ማስተካከል እንደሚገባቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ካልሆነ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ብርቱ ሥራ የሚጠይቀው የፀረ አበረታች መድሐኒት ትግሉ ፍሬ ማፍራት ይሳነዋል፡፡

በመድረኩ መገኘት ያልቻሉትን አትሌቶች በመውቀስ አስተያየቱን የጀመረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በዶፒንግ ችግር ዙሪያ ተሰብስቦ መምከር የሚገባቸው አትሌቶች ብቻ ሳይሆኑ ክለቦችም ጭምር መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ምርመራዎች ሲኖሩም ከዓለም አቀፉ ተቋማት ጫና ብቻ በዘመቻ መጀመር ሳይሆን ራሱን የቻለ የምርመራ ካላንደር እንዲኖር መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል፡፡

አትሌት መሠረት ደፋር በበኩሏ ‹‹በፀረ አበረታች መድሐኒት ተጠቃሚነት ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በቂ ናቸው ብዬ አላምንም›› ትላለች፡፡ እንደእርሷ አስተያየት ከሆነ አንዱ አትሌት ከሌላው ጥፋት ትምህርት እንዲወስድ ቅጣቱ የሚታይ መሆን ይኖርበታል፡፡

የዓለም ፀረ አበረታች መድሐኒት ድርጅት ጥፋተኛ አትሌቶችን የሚቀጣባቸው የተለያዩ ሕጎች አሉ፡፡ በአትሌቱ ላይ ከሚተላለፍ ቅጣት ባሻገር ሌሎች እገዳዎች ይኖራሉ፡፡ ከተቀጡ አትሌቶች ጋር ልምምድ አብሮ መሥራት፣ የስልጠና ምክርና ድጋፍ ማግኘት ለተጠያቂነት እንደሚዳርግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ይሄ ቅጣት አሰልጣኞችና ተወካዮችንም ይጨምራል፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ አንድ አትሌት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አበረታች መድሐኒት ወስዶ ሲገኝ በማን አማካኝነት ለችግር እንዳጋለጠው ለሕግ ከተናገረ ቅጣቱ በግማሽ የሚቀንስለት ይሆናል፡፡

ብሩክ በርሄ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy