Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕዝብ በወሳኝነት ሙስናን ይታገላል !!

0 326

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕዝብ በወሳኝነት ሙስናን ይታገላል !!

                                       ይነበብ ይግለጡ

ጥልቅ ተሀድሶ በይፋ ታውጆ ወደስራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባና ክልሎችን ጨምሮ በሙስና በኪራይ ሰብሳቢነት በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ማዛባት ችግር ውስጥ ተዘፍቀው በተገኙ  በተለያየ ደረጃ  በነበሩ አመራሮች ላይ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በትግራይ በኦሮሚያ በአማራ በጋምቤላ በሀረሪክልልና በሌሎችም አካባቢዎች  የመንግስትና የሕዝብን አደራና ኃላፊነት በመርገጥ የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ በብልሹ አሰራርና በሙስና ውስጥ ሲዋኙ በተገኙት አመራሮችና የበታች ሰራተኞች ላይ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ላይ የተፈጸሙት በደሎች ሰፊ የመሆናቸውን ያሕል የተሀድሶው እርምጃ   በሕዝቡ ሰፊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በደል የፈጸሙትን ከኃላፊነታቸው ከማንሳት ጀምሮ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ በተረጋገጠ ማስረጃ በመቀጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ባሉት ወራት ተመሳሳይ እርምጃዎች በተለያዩ ክልሎች ተወስደዋል፡፡  

ሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር ሕብረተሰቡን አስመርሮ አስቆጥቶ ለተቃውሞ የሚያስነሳ ያልተጠበቀ ችግር እንዲከሰት የሚያደርግ መሆኑን  በአይናችን አይተናል፡፡ችግሩን በየደረጃው ለመፍታት በመንግሰት በኩል ቁርጠኝነት አለ፡፡ይህንን የመንግስት ቁርጠኝነት ውጤታማ ወደሆነ ደረጃ ለማሸጋገር ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡

በሀገራችን አይተንና ሰምተን የማናውቀው አይነት ሙስና ነው ተስፋፍቶና ተንሰራፍቶ የኖረው፡፡ ይሄ ጉዳይ ያሳስባል ያስፈራልም፡፡ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ሰርቶና ለፍቶ ሳይሆን ዘርፎና ነጥቆ ባገኘው ሀብት ጡንቻውን ያጎለበተበት፤በዘረጋው የጥቅም ግንኙነትና ትስስር ሰፊ ማሕበራዊ ድር የመሰረተበት ሁኔታ መኖሩን፤የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን በጓደኝነት በቤተሰብና ከቤተሰብ ውጭ ባሉ የሩቅ ግንኙነቶች ውስጥ እንዲታቀፉ አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ሕዝብ በስፋት ይናገራል፡፡

በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ስመ ብዙ መልከ ብዙ ንግዶች በትራንስፖርት፤ በሆቴል፤ በአክሲዮን፤ በኮሌጆች፤ በቤትና በመንገድ ስራ፤ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ፤  በኮንትራት አሰጣጥ ወዘተ ሙያተኛ ላልሆኑ እውቀቱ ለሌላቸው ሰዎች ሆን ተብሎ ስራዎች እንዲሰጡ እየተደረገ የመንግስትና የሕዝብ ኃብትና ገንዘብ እንዲባክን ግለሰቦች እንዲከብሩበት ሲያደርጉ የነበሩት በመንግስት ጉያ ውስጥ ተሸሸግው ራሱን መንግስትንና ስርአቱን ለማዳከም ሲሰሩ የነበሩ ጥገኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እንደነበሩ ተደጋግሞ የተገለጸ እውነት ነው፡፡

ማስረጃ እያጠፉ አርቀው እንዳይገኝ አወሳስበው ሲሰሩ ምን አልባት አንድ ቀን እንጠየቃለን ከሚለው ስጋት በመነሳት እያወደሙ ሲሰሩ የነበሩ ሙሰኞችን ፈልፍሎ የማውጣቱ ስራ ጠንካራና የጎለበተ የመንግስትን ክትትልና የሕብረተሰቡን ትብብር  ይጠይቃል፡፡በሌላውም ሀገር ቢሆን ስልትና ዘዴያቸው የተለያዩ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡አልፈው ተርፈው ለዝርፊያ እንዲያመቻቸው ከሰለጠኑ ማፍያዎች ጋር ቅንጅትና ሕብረት ፈጥረው የሚሰሩበት ሁኔታ በበርካታ ሀገራት ታይቶአል፡፡

ለችግሩ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው መንግስት አሁን በጀመረው መልኩ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ማሳደግ ሲችል ብቻ ነው፡፡የመረጃ ግብአቶችን ከሕዝቡ ውስጥ በስፋት መሰብሰብና ማግኘት ለዚህም ጥበቃ ማድረግ ይገባል፡፡

በእስከ አሁኑ የተሀድሶው እንቅስቃሴ መልካም ጅምሮች ታይተዋል፡፡ሊበረታቱም ይገባል፡፡ ተሀድሶው ቀጣይና ተከታታይ ስራ እንጂ እዚህ ላይ ተጀምሮ እዚህ ላይ ያበቃል የሚባል አይደለም፡፡ተሀድሶው ሂደት ነው፡፡ተሀድሶው የአዲስ ምእራፍ ጅማሬ ጉዞ ነው፡፡የአዲስ ለውጥ የአዲስ አመለካከትና አሰራር መሰረት የሚጣልበት ቀጣይና ተከታታይ ጉዞ ነው፡፡ስር ሰደውና ተንሰራፍተው በኖሩ ችግሮች ውስጥ በአንድ ግዜ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ረዥም ስራ መስራትን ይጠይቃል፡፡የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የኖረውን ኃላቀር ግንዛቤ ከውስጥ ለማውጣት ግዜ ወሳኝ ነው፡፡

በአንድ ግዜ ሳይሆን በሂደትና በግዜ ማእቀፍ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ ሊገኝ እንደሚችል ይታመናል፡፡ተሀድሶው ደረጃ በደረጃ ለውጥ እያስገኘ የሚሄድ ሂደት ነው፡፡ከአሮጌው አመለካከት ወደ አዲሱ አመለካከት የመሸጋገር ጉዞ ነው፡፡ሙስናን ኪራይ ሰብሳቢነትን የመልካም አስተዳደር የፍትሕ ችግርን የሚከላ የሚጠየፍ ሕብረተሰብን በግዜ ሂደት መፍጠርን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጠያቂ ሞጋችና ለምን ብሎ ፈጥርቆ የሚይዝ የሚጠይቅ ሕብረተሰብ ተፈጥሮአል፡፡የትምህርት የእውቀት መስፋፋት የቴክኒዮሎጂውም እድገት ጭምር ለዚህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ሙስና ጥገኛና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል  መንሰራፋቱ ነው ለመልካም አስተዳደርና ለፍትሕ ችግር መፈጠር አቢይ ምክንያት የሆነው፡፡ያለውን የገንዘብ ኃይል በመጠቀም በተለያየ ደረጃ የነበሩ ኃላፊዎችን በመሸንገል የፍትሕ ስርአቱን በማዛባት መንግስት ኃላፊነት ሰጥቶ ያስቀመጣቸውን ሰዎች በመጥለፍ የተዛባ ፍትሕ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈጠር አቢይ ሚና ተጫውቶአል፡፡

ይህንን ማጥራት አሰራሩን በአዲስ መሰረት እንዲገነባ ማድረግ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ነው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ያለው፡፡እውነቱን በመሸፈን ለመደበቅ በመሞከር የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ይልቁንም ይህ አይነቱ እሳቤ ይበልጥ ችግሮችን በማወሳሰብ ያልተጠበቀ ችግር እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል፡፡ችግሩን ከስሩ መርምሮ ሕብረተሰቡ የሚለውንም አዳምጦ በማስረጃም ተደግፎ ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ ከኢሕአዴግና ከሚመራው መንግስት ይጠበቃል፡፡

ተለባብሶ ተሸካክሞ መጓዝ ለሕዝብም ለመንግስት አይበጅም፡፡በፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ጉዞ እየተመመች ያለች ሀገር ተኃድሶውን ተከትላ ስርነቀል የአሰራር ለውጦችን ማምጣት ይጠበቅባታል፡፡መንግስት በእቅድ ይዞ በሚሰራቸው የልማት ስራዎች ግንባታዎች የተለያዩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚያፈሰውን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዴት ነው የሚመራው የሚቆጣጠረውስ ኃላፊነቱንስ ማን ይወስዳል ትልቁ ዝርፊያ በእነዚሁ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ያጠነጠነ ነው የሚለውም የሕዝብ አስተያየት ሚዛን ይደፋል፡፡ትኩረት ሊሰጠውም ይገባል፡፡

በግንባታው በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በከተማ ልማት በገቢዎች በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ በሚፈጸሙ ስራዎች በግዢና በጨረታ ወዘተ ተዘርዝሮ ተነግሮ የማያልቁ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ የሕዝብ አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡

ሕዝብ አያውቅም የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል፡፡ሕዝብ ያውቃል፡፡ከሕዝብ የተሰወረ አንድም ምንም ምስጢር የለም፡፡ግዜውን ጠብቆ ይወጣል፡፡ለሀገሬና ለወገኔ ነው የምሰራው የዜግነት ግዴታዮን መወጣት ይጠበቅብኛል የሚል በቀድሞው ትውልድ የነበረ የሀገር ፍቅር ጠፍቶአል፡፡ለመመለስ መሰራት አለበት፡፡

መንግስትም ቢሆን ገንዘቡን ከየትም አያመጣውም፡፡አንዱም የውጭ ብድር ነው፡፡ሌላውም ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር ነው፡፡ሀገርን ሕዝብን ወገንን ማስቀደም ድሮ የነበሩ ትልቅ እሴቶቻችን ዛሬ ላይ እየተረሱ እየተሸረሸሩ የመጡ በእጅጉ እየጎዱን ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡

ሙስናን  ኪራይ ሰብሳቢነትን የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግርን በተመለከተ ሕዝቡ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች መንግስትም በራሱ በኩል በሚያደርጋቸው ማጣራቶች የሚወሰዱት የተሀድሶ እርምጃዎች በሁሉም ክልሎች መቀጠል አለባቸው፡፡የተዘረፉ የመንግስትና የሕዝብ ንብረቶችን የማስመለስ ስራም በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ መሰራት አለበት፡፡ይህንን ኃላፊነት በቀጥታ የሚወጣ አካል ሊኖርም ይገባል፡፡

በቀደመው ልምድ የተወረሱ ንብረቶች ከባንክና ከፍርድቤት ትእዛዝ ጋር በተያያዘ በሕግ ጥላ ስር ከዋሉ በኃላ አስታዋሽና ተከታታይ አጥተው መኪኖች አንድ ቦታ ተከማችተው የሚበሰብሱበት ከጥቅም ውጭ የሚሆኑበት ስንትና ስንት ለሀገር የሚጠቅሙ ንብረቶች ተመልካችና ባለቤት አጥተው በዝናብና በጸሀይ እየተመቱ የሚዝጉበት ከአገልግሎት ውጭ የሚሆኑበት ሁኔታ በብዙ መስሪያቤቶች በጉምሩክ ማከማቻ ማእከሎች በየፖሊስ ጣቢያው በየፍርድ ቤቱ ጭምር ስናየው የኖርነው እውነት ነው፡፡  

ተገትረው የቀሩ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙ ይችሉ የነበሩ ሕንጻዎች ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ማሽነሪዎች በየቦታው ብዙ ናቸው፡፡ይህ በሀገር ደረጃ ሲታይ ትልቅ ብክነት ነው፡፡መሆን የለበትም፡፡ፍርድቤቱ ከወሰነ በኃላ የሚረከበው መንግስታዊ አካል ወደ ስራ የሚገቡበትን መንገድ ፈጥኖ ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ይሄንን የምናነሳው ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ጋር ተያይዞ በዘረፋ የተገኙ ንብረቶች ወደመንግስት እንዲመለሱ የሚወሰንባቸውን የሚመለከት ነው የሚሆነው፡፡

ከሰሞኑ ከሙስና ችግር ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል በመንግስትና በሕዝብ ኃብትና ንብረት ላይ ሙስና ፈጽመዋል ያላቸውን 211 ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉን የክልሉ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገልጾአል፡፡ግለሰቦቹ የተቀጡት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ሲሆን በ121 መዝገቦች ክስ ተመስርቶባቸው ተገቢውን ማስረጃ በማሰባሰብ ቅጣቱ የተወሰነባቸው 182 ወንድና 29 ሴቶች ናቸው፡፡  

ግለሰቦቹ በተመሰረተባቸው በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም፣በግዢና ጨረታ ሙስና ፣ በተጭበረበረ ሰነድ መገልገል፣በግብር መሰወርና መሰል የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው ፍርዱ የተሰጠው፡፡ግለሰቦቹ በፈፀሙት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከሦስት ወር አስከ 14 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከ300 እስከ 30 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡

የሙስና ባሕሪ ያላቸው አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥቆማዎች ለኮሚሽኑ እንደደረሱት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡አምና በተመሳሳይ ወቅት ሙስና ፈፅመው የተገኙ 190 ግለሰቦች በሕግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ መደረጉን ከኮሚሽኑ የተገኘውን መረጃ በመንተራስ መገናኛ ብዙሐን ዘግበውታል፡፡

በሙስና ተግባር በእጃቸው የተገኘ ከ14 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ እንዲሁም አንድ ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡በተካሄደው የአስቸኳይ የቅድመ ሙስና መከላከል ስራ በጨረታ፣በእቃ ግዢ፣በምግብ ዋስትናና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙስና ሊፈፀምበት የነበረ 18 ሚሊዮን ብር ማስቀረት መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ለሙስና በተጋለጡ የከተማ መሬት፣ የንብረት ግዢና ጨረታ፣ የግንባታ፣ የግብር አሰባሰብና አወሳሰን፣በሰነድና መሰል ተግባራት ዙሪያ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ኮምሽኑ ገልጾአል፡፡ ሕብረተሰቡ ለስራው መሳካት የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናከሮ እንዲቀጥል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ይሄው ተግባር በሁሉም ክልሎች ሊቀጥልና ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy