መተማመንን አጎለበተ እንጂ ለመበታተን ምክንያት አልሆነም!
ወንድይራድ ኃብተየስ
ግንቦት ሃያ የዘመናት ህዝባዊ ትግላችን መሰረት የተጣሉባት የአገራችን መልካም ነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ቀን ናት። የአብሮነታችን ማሰሪያ፣ የአገራችን አንድነት ዋስትና እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት ግንቦት ሃያ መሆኗን መዘንጋት የለብንም። የአገራችን ህልውና አልፋና ኦሜጋ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የግንቦት ሃያ ድል አንዱና ዋንኛው ፍሬ ነው።
ይህ ሰነድ ገና ከመግቢያ ጀምሮ በሕዝቦች መካከል መቻቻል፣ አብሮ መኖር፣ የህዝቦች ፍተሃዊ ተጠቃሚነታችው የሚያረጋግጥ ሃሳቦችን አስፍሯል። የሕገ-መንግሥቱ መሠረታዊ ዓላማ በህዝቦች መካከል ዕኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲጎለብት በማድረግ የአገሪቱን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ማቆም ነው። ይህ ባለፉት 26 ዓመታት በተግባር ታይቷል። አገራችን የይስሙላ እኩልነትና አንድነትን ሳይሆን እውነተኛ እኩልነትንና አንድነትን ማዳበር ችላለች።
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የህዝቦችን ነጻነት በማረጋገጥ ረገድ ከማንኛውም አገር ህገ-መንግስት በተሻለ ሁኔታ የሚጠቀስ ነው። በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39ኝ ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስከመገንጠል የሚፈቅደውን አንቀጽ አንዳንዶች አገሪቱን ወደመበታተን የሚወስድ ነው በማለት ከህገ-መንግስቱ ላይ እንዲነሳ ሲወተውቱ ይታዩ ነበር። ይሁንና በተግባር ይህ አንቀጽ በህገመንግስቱ ላይ መካተቱ በተግበር ያረጋገጠልን ነገር በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲነግስ በማድረግ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዜግነት በፍላጎት እንጂ በሃይል የሚጫን ነገር እንዳይሆን አድርጎታል።
ይህ አንቀጽ በአገራችን ዳግም ጭቆና እንዳያንሰራራ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዋስትና የሚሰጥ አንቀጽ መሆኑንም መዘንጋት የለበትም። አንቀጽ 39 ጭቆና ሊያመጣ የሚፈልግ አካልን እጁን እንዲሰበስብ ያደረገ አንቀጽ እንጂ አገሪቱን ወደመበታተን አላመራትም።
የህገመንግስታችን ውጤት ከሆኑት አንዱ የፌዴራል ስርዓታችን ነው። ይህ ስርዓት የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶቻችንን ከማጎልበት ባሻገር ህዝቦች በአገራችው ጉዳይ በያገባኛል እንዲወስኑ አስችሏቸዋል። ግንቦት ሃያ የጭቆና ቀንበር የተሰበረባት ብቻ ሳተሆን ያ ስርዓት ዳግም እንዳያንሰራራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበረበት መሆኑን የተበሰረባትም ናት።
ግንቦት ሃያ የአገራችንን ዘላቂ ሰላም የምናጠናክርበት ፈጣን የልማታችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን አጠናክረን በማስቀጠል አገራችንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን ቃል የምንገባበት ቀን ናት – ግንቦት ሃያ!
ግንቦት ሃያ የፌዴራል ስርዓቱ በህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የቻሉበት፣ መፈቃቀድ ላይ የተገነባ አንድነታቸውን መሰረት የተጣለበት ዕለት ናት። ከዚህም ባሻገር ግንቦት ሃያ በአገራችን የብሔር ጭቆና፣ አፈናና አድልዎ ዳግም ላይመለስ መቀበሩን ህዝቦች ያረጋገጡበት ዕለት ናት። የፌዴራል መንግስቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላቸውን እንዲያለሙ ሁኔታቸውን በማመቻቸቱ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን እድገት በሁሉም አካባቢ የተመጣጠነ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።
ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ከስምንተኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ጀምሮ እየተከበረ ያለው በዓልን ስንመለከት በቀድሞ ስርዓቶች ኋላቀር ተብለው ይጠሩ የነበሩ ማለትም ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ አካባቢዎች የአርብቶ አደር አካባቢዎች በመሆናቸው ባለፉት ስርዓቶች የተረሱ ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት ያልነበራቸው ነበሩ። ይሁንና ባለፉት 26 አመታት መንግስት ክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖር ጠንክሮ በመስራቱ በየትኛውም ኮርነር ያሉ የአገራችን ከተሞች የተመጣጠነ ልማት ማግኘት ችለዋል። እነዚህ አካባቢዎች በጣት ለሚቆጠሩ ለመስክ የሚወጡ ባለሙያዎች እንኳን የተሟላ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ማቅረብ የማይችሉ የነበሩ ከተሞች ዛሬ ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን የማስተናገድ አቅም ፈጥረዋል። ይህ ነው ለውጥ ማለት።
ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት መሰረተ ልማቶችን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍተሃዊ በሆነ መልኩ ማስፋፋት በመቻሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች ትላልቅ ኢቨንቶችን ማስተናገድ ጀምረዋል። በአገራችን እየተመዘገበ ካለው እድገት ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል መኖሩን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል የተመጣጠነ የከተሞች እድገት አንዱ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ ደግሞ በኢትዮጵያ ከተሞች እየታየ ያለው እድገት ነው። ዛሬ ለዘመናት ለውጥ ሳያሳዩ የነበሩ ከተሞች ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የጀመሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር በመቻላቸው የተመዘገበ ዕድገት ነው።
በለፉት 26 ዓመታት የአገራችን ህዝቦች በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተቀመጡ መብቶቻቸውን ተጠቅመው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያስቀመጡትን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ ተረባርበዋል። በዚህም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ችለዋል፣ ማንነታቸውን አውቀው የአገራቸውን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም አድርገዋል፣ በአገራችን ዘለቂ ሰላም ማስፈን በመቻላቸው ባለሁለት አሃዝ ዓለምን ያስደመመ ለ15 ዓመታት ተከታታይ እድገት ማስመዝገብ ችለዋል።
አገራችን እያስመዘገባች ያለችው በለሁለት አሃዝ እድገት የግንቦት ሃያ ውጤት ነው። በዕርስ በርስ ጦርነትና ረሃብ ትታወቅ የየነበረች አገር ባለፉት 26 ዓመታት በተመዘገበ ለውጥ ከአፍሪካ አልፋ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅናን ማትረፍ የቻለችው ግንቦት ሃያ በተጣለ መሰረት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በቀጣይም የፌዴራል ሥርዓቱን ማጎልበት ተገቢ ነው። የፌዴራል ስርዓቱ ስጋት የሆኑት ትምክህትና ጥበት መዋጋት የሁሉም ሃላፊነት መሆን ይገባዋል።
ብዝሃነት እንዲጎለብት ሲደረግ በሥርዓቱ ውስጥ በተሻለ ደረጃ ግልጽነትን ስለሚፈጥር ለጥበትና ትምክህት እንዲሁም ለፀረ ሠላም ኃይሎች የመደበቂያ ዋሻ የሆነው ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመናድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ብዝሃነት እንዲጎለብት በማድረግም የኃይማኖት አክራሪነት ቦታ እንዳያገኝ ያደርገዋል። በመሆኑም ለአንድነታችንና ለአብሮነታችን ጠንቅ የሆኑትን አክራሪነት፣ ጥበትና ትምክህትን በግንቦት ሃያ ድል በጋራ ልናወግዛቸው ይገባናል።
አገራችን ዘመናዊ ከሚባሉ ህገ-መንግስቶች ባለቤት እንድትሆን ያስቻላት ግንቦት ሃያ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። ሕገ-መንግሥቱ የአገራችን ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሠረት ጥሏል። ዛሬ በአገራችን በፖለቲካዊ አስተሳሰብ መደራጀት የተለመደ ተግባር ሆኗል። አገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን መከተል በመቻሏ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ። ሃሳብን የመግለፅ መብት በመረጋገጡ የግል ሚዲያ እየተስፋፋ ይገኛል። የተለያዩ ሃሳቦችም በነፃነት ይንሸራሸራሉ። ይህ ሁሉ የግንቦት ሃያ ድል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።
በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት እየተስተናገዱ ይገኛሉ። በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። ይህ በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስረት ተችሏል።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በአገራችን የታየው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና የህዝቦች እኩልነትና ነጻነት ባሻገር አገራችን እያስመዘገበች ያለችው ልማትና እድገት መሰረቱ ግንቦት ሃያ ናት። አገራችን በታሪኳ አከናውናው የማታውቃቸውን እጅግ ግዙፍ የሆኑ ባለ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መገንባት ችላለች። ለአብነት ያህል ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎችና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም በመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታ ወዘተ አገልግሎት ተጠቃሾች ናቸው።
ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት የከተማ ነዋሪዎችን ህይወት ለመለወጥ እንዲቻል የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተንቀሳቅሷል። በዚህም በርካታ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሆኑበትን የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን በመስፋፋት በርካታ ዜጎች ስራ እንዲፈጠሩላቸው በመሆኑ ገቢያቸው እንዲጨምር በመደረጉ የከተማ ነዋሪዎች ህይወት መለወጥ ችሏል። በዜጎች መካከል ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ በከፍተኛ ድጎማ የመኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በመገንባት በእጣ እያከፋፈለ ይገኛል። ይህም በርካታ የከተማ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለቸው ነዋሪዎች የቤት ባለቤት የሆኑበት ሁኔታን ማየት ይቻላል። በየትኛውም የአፍሪካ አገር ይህን ዓይነት ተግባር አልተከናወነም።
በማህበራዊ ዘርፍ በትምህርትና ጤናው ዘርፍም መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት በበርካታ አንጸባራቂ ድሎች የተሞሉ ናቸው። ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተዋል። የአገራችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች (በዕትዕ ሁለት በግንባታ ላይ የሚገኙትን አስር አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይጨምር) ከ36 በላይ ለማድረስ ተችሏል።
በአገራችን የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ እንዲሁም የተማሪዎች ቁጥርም ወደ 30 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው። ከሶስት ሰዎች አንዱ ተማሪ የሆነበት አገርን መፍጠር የተቻለው ግንቦት ሃያ ላይ በተጣለው መሰረት ሳቢያ ነው። አገራችን በጥቂት አመታት ውስጥ ምን ያህል የተማረ የሰው ሃይል ሊኖራት እንደሚችል መገመት የማያስቸግር አይመስለኝም። በጤናው ዘርፍም አገራችን ከፍተኛ ስኬት ያሳየችበት ዘርፍ ነው። በትምህርትና ጤናው ዘርፍ አገራችን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ቀድማ በማሳካት እንደአብነት የምትጠቀስ አገር መሆን ችላለች። ይህ ሁሉ ስኬት የግንቦት ሃያ እንደሆነ ማሳብ ተገቢ ነው።
የግንቦት ሃያ አምባገነን ስርዓት የተወገደባትና የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና የዕኩልነት ትግል ውጤት የታየባት ዕለት ናት። በመሆኑም ግንቦት ሃያ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት የተጣለበት ዕለት በመሆኗ ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ ሊያከብራትና ሊንከባከባት የምትገባ ህዝባዊ የድል ቀን ናት። ለአገራችን አንድነትና ለህዝቦች አብሮነት ጥንጣን የሆኑት አክራሪነት፣ ጥበትና ትምክህት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጠላት በመሆናቸው ሁላችንም በጋራ ልንዋጋቸው ይገባል።