Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መነሻውን ያላወቀ መድረሻውን

0 386

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መነሻውን ያላወቀ መድረሻውን አያውቅ!

አባ መላኩ

 

“መነሻውን ያላወቀ መድረሻውን አያውቅ” የሚል  ርዕስ ለዛሬ አተታዬ መነሻ እንድትሆነኝ የፈለኩት ኢትዮጵያ “በግንቦት ሃያ” ድል  ከየት ተነስታ የት እንደደረሰች አንዳንድ ሃሳቦችን ለማንሳት ታግዘኛለች በሚል ነው። ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በፊት  አገራችን አይኑን ታስሮ በገደል አፋፍ እንደቆመ ሰው  ተደርጋ  የምትወሰድ አገር ነበረች።  በአገሪቱ የድህነት መጠኑ እጅግ የከፋበት፣  ኢኮኖሚው ክፉኛ ያዘቀጠበት፣ ደም መፋሰሱ የከፋበት፣   የመበታተን አደጋው አስጊ የሆነበት በአጠቃላይ  ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት  ወቅት  ነበር።   ለ17 ዓመታት ለነጻነትና እኩልነት የተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ በርካታ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ የታጠቁ ሃይሎች ፍላጎታቸውን በሃይል ለማሳካተ ሲሯሯጡ የነበሩበት ወቅት ነበር። ይሁንና በወቅቱ ትልቅ ሃላፊነት የተጣለበት ኢህአዴግ የሁሉንም ሃይሎች ፍላጎት ማሳካት የሚያስችል አካሄድ መከተል በመቻሉ አገራችንን ከውድቀት ታድጓታል።  

 

ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ወዲህ የመጣውን  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ለውጦች ለመረዳት ቀደም ሲል የነበረውን ሁኔታ በትክክል መገንዘብን ይጠይቃል፡፡ አንዳንዶች የባለፉት ስርዓቶች ማለትም የአጼዎቹና የደርግ መንግስት  ሲነሱ አይወዱም።  ይሁንና እውነታው ግን መታወቅ አለበት። መነሻውን የማያውቅ መድረሻውን አያውቅም እንደሚባለው  ግንቦት 20  ከያት አንስታን የት እንዳደረሰችን ለማወቅ የቀድሞውን  መነሻ ማስታወስ ተገቢ ነው።  

 

የአጼዎቹ  ስርዓት የኢትዮጵያን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን ህዝብንም ጭምር እንደ ግል ንብረት ይቆጥር ስለነበር እንኳን ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ይቅርና ለሰብዓዊ መብቶችም ቁብ  የሚሰጥ ስርዓት አልነበሩም።  የደርግ መንግስትም ቢሆን ሶሻሊሊስታዊ ስርዓትን አስፈናለሁ በሚል ሽፋን የለየለት ፋሽስትና አምባገነን  መንግስት ነበር፡፡ ይህንን የተበላሸ ፖለቲካዊ ሁኔታ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መልኩ ለመቀየርና አማራጭ ሃሳብ ለህዝብ ለማቅረብ ትግል የጀመሩትን ወጣት ምሁራን በግልጽና በአደባባይ ከመጨፍጨፉም በላይ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር  በሚል  የጥፋት ፖሊሲው አገሪቱን ወደ ውድቀቷ ህዝቡን ወደከፋ ድህነት እንዲያመራ አድርጓታል። የደርግ መንግስት በተከተለው የተሳሳተ አካሄድ አገሪቱን ከገደል አፋፍ አቁሟት ነበር።   

 

ግንቦት ሃያ በአገራችን ታሪክ የበርካታ መልካም ነገሮች  መሰረት ናት።  የዛሬ 26 ዓመት ማለትም ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ መራሹ ሀይል አዲስ አበባን በመቆጣጠር  አምባገነኑን የደርግን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ከስልጣን ያስወገደበት ዕለት ናት።  በዚህም ሳቢያ ለ17 ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የተከፈለው እልህ አስጨራሽ   የዕርስ በርስ ጦርነት ያበቃበት ዕለት ናት – ግንቦት ሃያ። ደርግ በሃይል በትረ ስልጣኑን ሲለቅ በርካቶች የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ  እንደ ሶማሊያ፣ ዮጐዝላቪያና ላይበሪያ ትሆናለች በማለት ሲናገሩና ሲጽፉ ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ እንደተሟረተባት ሳይሆን በተቃራኒው  ለመሆን ያበቃት በወቅቱ ኢህአዴግ የተከተለው  ሁሉንም አካቶ መያዝ የሚያስችል  የሽግግር መንግስት  እንዲመሰረት  በማድረጉ ነው።

 

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ለኢትጵያና ለህዝቦቿ ከበርካታ ስቃይ  እፎይታን ያስገኘች፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረት የጣለችና ለብሔሮች፣ብሔረሰቦችና  ህዝቦች የነፃነትና የዕኩልነት መብት መረጋገጥ ፋና ወጊ የሆነች ዕለት በመሆኗ በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ህዝቦች ዘንድ በመልካምነት ስትዘከር፣ በገዥነት ስልጣናቸው በህዝቦች ጫንቃ ላይ ተቀምጠው ለነበሩት የባለፉት ስርዓት አቀንቃኞች  ደግሞ ገደቢስ ቀን ተደርጋ ትወሰዳለች። የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ሁሌም ሊቀድም ይገባልና ጥቂቶች ግንቦት ሃያን በመልካም ባይመለከቷትም በብዙዎች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ደምቃ የምትከበር ዕለት ለመሆን በቅታለች።

 

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም  በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ቀናት መካከል  በቀዳሚነት  የምትነሳ  ዕለት ናት። ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን ያረጋገጡበት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በሃይል ያስከበሩበት፣  የኢትዮጵያ አንድነት በህዝቦች መፈቃቀድ፣ በዕኩልነትና በነጻነት  በጽኑ መሰረት ላይ  የመሰረቱባት ዕለት ናት። ከግንቦት 20 1983 ዓ ም ማግስት በርካታ ለውጦች በአገራችን ተመዝግበዋል። እንደእኔ የመጀመሪያው የደርግ መንግስት ሲከተለው የነበረውን የዕዝ ኢኮኖሚ ስርዓት ሙሉ በሙሉ በመቀየር በነጻ ገበያ ስርዓት የሚመራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲተካ መደረጉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሀገሪቱ ቀደም ሲል በዘውዳዊና ፍጹም አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን በጠንካራ አህዳዊ ሥርዓት ስትመራ በመቆየቷ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ ባልተማከለ፣ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ በሆነ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት እንድትመራ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው  ነው፡፡

ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ይኸው ያልተማከለ፣ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ የሆነው አስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ በማድረግ አገሪቱ  ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አወቃቀርን ተከተለች፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና  ህዝቦች ራሣቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከመቻላቸውም በላይ በጋራ ጉዳዮችም ላይ እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበት የፌዴራል መንግስትም አዋቀሩ፡፡

 

ባለፉት 26 ዓመታት የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርአትን በመፍቀዱም ህዝቦች ይበጀኛል፣ ይወክለኛል የእኔ ነው የሚሉትን ተወካያቸውን በየአምስት ዓመት  በነጻነት መምርጥ ችለዋል። እስካሁን አምስት አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎችን በነጻነት አካሂደዋል። ህዝቦች  የተጎናጸፉት የፈለጉትን የመምረጥ  መብት ብቻ ሳይሆን  ውክልናውን በአግባብ አልተወጣም፣ አንፈልገውም ያሉትንም ተወካያቸውን በፈለጉበት ወቅት ማንሳት እንደሚችሉም በተግባር አረጋግጠዋል።

 

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ መብትንም ለዜጎች አጎናጽፏል።  ቅድመ ምርመራን ከማስቀረት ጀምሮ የፕሬስ ነጻነትን በግልጽ በማዋጁ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚስማማውን የፖለቲካ አስተሳስብ እንዲያራምድና የመሰለውንም ሀሳብ በነጻነት እንዲገልጽ ዕድል ተፈጥሮለታል።  ባለፉት 26 ዓመታት አንዳንዶች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ተጠቅመው አገርን ሊያፈርስ ህዝብን ሊያጫርስ የሚችል ተግባራትን ሲያከናውኑም  ታይተዋል። እነዚህ ሃይሎች የህግ የበላይነትን አይቀበሉም፣ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕኩልነት አያምኑም፣ እነዚህ ሃይሎች  አንድነት የሚሉት  የቀድሞ ስርዓቶች ያራምዱ የነበሩት የሃይል አንድነት እንጂ   በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገውን የአዲሲቷን ኢትዮጵያ አንድነት አይደለም።  በመሆኑም   በነጻ ፕሬስ ስም  በጥፋት ብዕራቸው አገራችንን ሊበታትኗት፣ ህዝቡን ሊያጫርሱት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። እንዲህ ያለን ቅጥ ያጣ  አካሄድን  ሃይ ማለት ፕሬስን መቃወም አይደለም። የህግ የበላይነት በየትኛውም ቦታና ጊዜ ማረጋገጥ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው።  

 

ባለፉት 26 ዓመታት  በአገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ረገድም ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ ከሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ወደ ሁሉም ነገር ወደ ልማት የሚል የፖሊሲ ለውጥ በመደረጉ በተለይም ደግሞ ባለፉት 15 ዓመታት እጅግ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ አገራችን አለምን ያስደመመ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ የዕድገት ምህዋር ውስጥ መግባት ችላለች። አገራችን በመሰረተ ልማት ግንባታም እጅግ ስኬታማ መሆን ችላለች።  የትምህርት ሽፋኑ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግና የጤና አገልግሎቱ በፍጥነት መስፋፋትም ሌላኛው በግልጽ የሚታይና በእጅ የሚጨበጥ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የወለደው ማህበራዊ ለውጥ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከ1995 ዓ.ም  በፊት የነበሩት ዓመታት በአገራችን የመንግስት ትኩረት   ሰላምና መረጋጋትን  በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈር ላይ የነበረ በመሆኑ እንዳሁኑ  ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበበት ወቅት አልነበረም።  ይሁንና አጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በአምስትና በስድስት ፐርሰንት እያደገ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው።  

 

መንግስት የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ  ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።  የመልካም አስተዳዳር ችግሮች በየትኛውም ዓለም ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች እንደሆኑ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በመነጋገርና በመወያያት እንጂ በአመጽና ነውጥ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት  በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት  በመልካም አስተዳደር እጦት የሚማረረውን የህብረተሰብ ክፍል ቅሬታ ለመፍታት  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት  መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ ነው። ይህ የመንግስት ጥረት ውጤታማ የሚሆነው በህዝብ ሲታጀብ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ለመልካም አስተዳዳር መስፈን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።  

 

ግንቦት ሃያ  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች  ዴሞክራሲያዊ ስርዓትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት  ለመገንባት፣ ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ ዘላቂ ሰላምን ለማርጋገጥና ህዝቡ በየደረጃው ዕኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሰረት የጣሉበት ዕለት ናት። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህልውና ዋስትና የሆነው የኢፌዴሪ   ህገ-መንግስትም  የግንቦት ሃያ ዋንኛ ፍሬ ነው።  በመሆኑም  ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ የእኔ የሚላት ቀን ናት።  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy