Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መናበብ ካለመቻል የሚመነጩ ችግሮቻችን

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መናበብ ካለመቻል የሚመነጩ ችግሮቻችን
ኢዛና ዘመንፈስ
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሠረተ ሃሳብ አነሳ ዘንድ ምክንያት የሆኑኝን ሁለት …. መረጃዎች ከሰሞኑ አግኝቻለሁ፡፡ እንግዲያውስ አንዱና ዋነኛው መነሻ ምክንያቴ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃ/ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሚያዝያ 11ቀን 2009ዓ.ም ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኖች የሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ፤ በተለይም በገዢው ፓርቲ አባል ድጅቶች አመራር መካከል እርስ በርስ የመሰጋጋት ወይም የመጣጠር ችግር ተፈጥሮ እንደነበር የገለፁበት አግባብ መሲሆን፤ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ በዚያው ሰሞን አየር ላይ ከዋለ አንድ የሬድ ውይይት የሰማሁት የአድማጭ አስተያየት ነው፡፡
ስለሆነም፤እነዚህ ሁለት ምክንያቶች እንደ ዋነኛ የመረጃ ግብዓት ወስጄ፤ ዕርስ በርስ መናበብ ካለመቻል የሚመነጩ ፈርጀ ብዙ የጋራ ችግሮቻችን ለማቃለል ይረዳል የምንለውን የመፍትሄ ሀሳብ መሰንዘር እንዳለብኝ አምናለሁና አሁን በቀጥታ ወደ ቀዳሚው ጉዳይ ልለፍ፡፡ ከዚህ ሁለቱን ነጥበች በቅደም ተከተል አንስቼ ከኔ የግል አስተያየት ጋር በሚጣጣም ምልኩ ለማቅረብ ያመቸኝ ዘንድም፤ ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃ/ማርያም ደሳለኝ፤ ሚያዝያ 11ቀን 2009ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው ለሀገር ውስጥ ጋዜተኞች የሰጡት መቀግለጫ ላይ፤ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራር አካል …. ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ስለመለሱበት ሀሳብ የሚያወሳውን ነጥብ አስቀድማሁ፡፡
በዚህ መሰረትም፤ እኔ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችንን ወቅታዊ መግለጫ በተሟላ መልኩ አንብቤ ለመረዳት የቻልኩት፤ ሚያዝያ 11ቀን 2009ዓ.ም የታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በኢህአዴግ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች መካከል መጠራጠር እንደነበር በይፋ አመኑ›› በሚል ርዕስ ከወጣው ፅሁፍ እንደሆነ ግንዛቤ ይወሰድልኝ፡፡ እናም ጋዜጣው የፖለቲካ አምዱ ላይ አትሞ ያወጣው የአቶ ሃይለ ማርያም ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ በእርግጥም የገዚው ፓርቲ አባል ድርጅቶች አመራር አካላት በመካከላቸው ንፋስ እንዲገባ የሚያደርግ አላስፈላጊ ዕርስ በርስ የመሰጋጋት ጥርጣሬ አድሮባቸው እንደነበርና ግን ደግሞ በጥልቅ ተሃድሶው መድረክ ችግሩ ተነስቶ ግለ ውይይት ስለተካሄደበት አሁን ጉዳዩ እንደማያሳስባቸው ነው የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር የተናገሩት፡፡
በተይም ደግሞ በብአዴንና በህውሐት መካከል አሳሳቢ አለመግባባት ያለ አስመስለው የሚያስወሩ ወገኖች ስለመኖራቸው የተጠየቁት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ‹‹በብአዴንና በህወሐት መካከል ብቻ አይደለም መጠራጠር ተፈጥሮ የነበረው ይህ ጥርጣሬ በኢህአዴግ እና ህወሐት መካከል፤በኢህአዴግ እና በብአዴን መካከል፤ እንዲሁም ደግሞ በኦህዴድና …….በብአዴን መካከል፤ እንዲሁም ደግሞ በኦህዴድና ….. መካከልም ተስተውሏል›› የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡
‹‹መጠኑ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶቻችን መካከል ተመሳሳይ አመካከት …………… ችግር ነበረ የሚል ነው በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማችን የጋራ መግባባት ላይ የደረሰበት ጉዳይ›› ሲሉ ያከሉት አቶ ሃ/ማርያም፤ እንደዚሀ አይነቱ ስህተት ለኢህአዴግ ወራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ታሪክ አዲስ ነገር ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ሲገልፁም ‹‹ ….. ትግሉ ዘመን ጀምሮ አልፎ አልፎ ያጋጠሙ መሰል ድክመቶች እንደነበሩና እንዲሁ በሰከነ ውይይት እንደተፈቱ የሚታወቅ ነው›› ብለዋል፡፡
በእርግጥም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንዳሉት፤ ለኢህአዴግ አመራር መሰል የአመለካከት መዋዠቅ የሚያስከትላቸውን የአመራር አካላት ድክመቶች በግልፅ ውይይትና ግምገማ ሂደት እንዲጠሩ እያደረጉ የእርምት እርምጃ የመውሰድ ድርጅታዊ የፖለቲካ ባህል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ግንባሩን በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ የተለየ ስፍራ እንዲሰጠው ከሚያደርጉት ጠቃሚና መዳበር የሚገባቸው የትግል እሴቶቹ መካከል አንዱ ይሔው የአመራሩን ድክመቶች በግልፅ የውይይት መድረክ እየፈተሹ ዕርስ በርስ የመተራረም ግምገማው እንደሆነም ደፍሮ መናገር ይቻላልና ነው እኔ ራሴም የእርሳቸውን ሃሳብ መደገፌ፡፡
በሌላ አነጋገር፤ ይልቁንም ደግሞ እንዲህ እደአሁኑ የግንባሩን አባል ድርጅቶች የአመራር አካላት እርስ በርስ መናበብ ካለመቻል የሚመነጭና መሠረታዊ የአቋም ልዩነት ሳይኖር የሚስተዋል የጥርጣሬ ስሜትን የሚያንፀባርቁበት አሉታዊ አዝማምያ ጎላ ብሎ ሲታይ፤ መሰል ወደ ውስጥ የመመልከቻ ድርጅታዊ መድረኮችን በመክፈት አላስፈላጊ ብዥታዎችን የማጥራትና የማስወገድ ጥረት ማድረግ፤ ኢህአዴግን ኢህአዴግ የሚያሰኘው ነባር የፖለቲካ ባህል ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም ማለታችን ነው፡፡ ይህን ስል ግን፤ ኢህአዴግ ወራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ከሌሎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ይልቅ የተሻለ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርጉት ጠቃሚ ድርጅታዊ እሴቶች፤ ሁሌም የግንባሩን ጠንካራ ጎን ጠብቆ ማስቀጠል የሚያገለግሉ ፍቱን መፍትሄዎች ይሆናሉ ለማለት እየቃጣኝ እንዳይመስልብኝ፡፡
ለኔ ለማለት የፈለኩት፤ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ ላይ እንደተገለፀው ሁሉ፤ ኢህአዴግ በረጅም የትግል ታሪኩ ከሚታወቅባቸውጠንካራ ጎኖቹ መካከል፤አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ነጥብ፤ ውስጣዊ ችግሮች ሲያጋጥሙት እንደየባህሪያቸው የሚወሰን ዴሞክራሲያዊ የአፈታት ስርዓትን በመከተል ረገድ የዳበረ ልምድ ያለው ስለመሆኑ ነው እንጂ፤ ግንባሩ …… የፀዳ ነው ለማለት እንደ ማይዳኝ ልብ ይባልልኝ፡፡ ደግሞስ ኢህአዴቹ ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ ለሚታወቁባቸው ጠቃሚ የፖለቲካዊ ባህል ዕሴቶች ተገቢውን ክብር አልያም ደግሞ ዋጋ እየሰጡ ቢሆን ኖሮ፤ እርስ በርስ መናበብ ካለመቻል የሚመነጩት ችግሮቻችን ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ ይመጡ ነበር እንዴ? ለዚህ ጥያቄ የእናንተን ምላሽ ለእናንተው ትቼ እኔ የራሴን አስተያየት በምክንያታዊ ማብራሪያ ለማስደገፍ እሞክራለሁ፡፡
ስለዚህም፤ እውነቱን መነጋገር ካለብን፤በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት ጭምር ታይቷል የተባለው አላስፈላጊ፤ ወይም ደግሞ ኢ ምክንያታዊ ዕርስ በርስ የመሰጋጋትን የጥርጣሬ ስሜት የማንፀባረቅ ስሜት፤ እንደ አንድ እቺን ሀገር የመምራት ታሪካዊ ሃላፊነት የመሸከም ብቃት አለው ተብሎ በህዝብ የተመረጠ የፖለቲካ ፓርቲ ዕርስ በርስ መናበብ ካለመቻል የመነጨ የአመለካከት ብዥታ እንጂ ሌላ መሰረታዊ የአቋም ልዩነት በመካከላቸው ስለተፈጠረ እንዳልሆነ ፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ በርካታ ጥንቃቄን የሚጠይቁና የነቃ ክትትል የሚያሻው የብዝሃነታችን ተጨባች መገለጫዎች በሚስተዋሉበት ነባራዊ እውነታ ውስጥ፤ እንኳስ መናበብ አለመቻል ታክሎበት እንዲያውም እንዲያው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንምና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ሲመጣ የሚስተዋለው የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፤ ባፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ሲገለፅ የሚስተዋበት በዚህ ወቅት፤ ሀገቷን የመምራት ታሪካዊ ሃላፊነት የተሸከሙት የመንግስት አካላት በመካከላቸው መኖር ስለሚገባው ዕርስ በርስ መናበብ የማል አስፈላጊነት ጉዳይ፤ የተሟላ የጋራ ግብዛቤ ሳይጨብጡ ቀርተው ሊከሰት የሚችል አደጋ ምንኛ አስከፊ ውጤት እደሚያስከትል መገመት መገመት የሚከብድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ሕገ መንስታዊ ስርዓቱን በአመፅ ተግባር ደርምሰው መንበረ ስልጣኑን በአቋራጭ መንገድ ለመቂናጠጥ የቋመጡ የቀለም አብዮት ናፋቂ የተቋውሞው ጎራ ፖለቲካ ሃይሎች፤ ከሀገርቤት እስከ ባህር ማዶ በተዘረጋ …….. ፈጠራ መረባቸው አማካኝነት የሚያዛምቱት መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ በሙሉ የገዢውን ፓርቲ አባል ድርጅቶች ዕርስ በርስ ለማጠላለፍ ሲባል የተቀነባበረ …. ሴራ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነ ይታወቃልና ነው፡፡
ስለዚህ፤ ምንም እንኳን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞነኛው መግለጫቸው ላይ ‹‹…መወሰድ ያለበት ጠቃሚ ቁም ነገር የሚመስለኝ የተፈጠሩ ችግሮቻችንን ሁሉ ለመፍታት የሚያስችል ሕጋዊ አግባብ ወይም ስርዓት መኖሩን መረዳት ነው እንጂ ችግሮቹ ለምን ተከሰቱ የሚል ጉዳይ አይደለም›› ያሉትን ቁልፍ ነጥብ እንደምጋራው ባያከራክርም፤ ግን ደግሞ መሰል ዕርስ በርስ መናበብ ካለመቻል የሚመነጪ ድክመት አቅልሎ መመልከት የሁዋላ ሁዋላ ለመቀልበስ ወደሚያዳግት ደረጃ አድገው ላለመገኘታቸው ዋስትና አይሆንምና ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› እንደሚመረጥም አለመዘንጋት ይበጃል ባይ ነኝ እኔ፡፡ ለማንኛውምግን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃ/ማርያም ደሳለኝ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሰጡት መግለጫ ላይ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ተፈጥሮ ስለነበረው ክፍተት በተናገሩት ዙሪያ ይህን ያህል ካልኩኝ ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው የፅሁፌ መነሻ ምክንያት ልለፍ፡፡
በዚህ መሰረትም፤ ሌላኛው መናበብ ካለመቻል የሚመነጩ ሀገር አቀፍ የጋራ ችግሮቻችን መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ስለሚሰማኝ የመንግስታዊ ሀብት ንብረት ብክነትን የሚመለከት ቅሬታቸውን ሲገልፁ የሚደመጡ ዜጎች ጥቂት እንዳልሆኑ የሚያወሳ ነው ሁለተኛው ነጥብ፡፡ ስለሆነም፤ ማክሰኞ ሚያዚያ ቀን 2009 ዓ.ም አየር በዋለ “ቆይታ ከሚሚ ስብሐቱ ጋር” የሚል ርዕስ ያለው የዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ ጣቢያ ፕሮግራም ስላስደመጠን የቀጥታ ስርጭት ውይይት አንስቼ እዚያ ላይ የተሳተፉ አድማጮች በተለይም የመንግስታዊ ሀብት ንብረት ብክነትን አስመልክተው የተናገሩትን ጠቃሚ ነጥብ ለማስታወስ እሞክራለሁና እነሆ አብረን እንየው፡፡
ስለዚህም፤ከላይ በተጠቀሰው ቀንና የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ሳምንታዊ ፕሮግራም ቀርበው፤ከጣቢያው አድማጮች ጋር በወቅታዊ የሀገራችን ችግሮች ዙሪያ ሀሳብ የተለዋወጡት የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ሚኒስቴሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ሲሆኑ፤ለእርሳቸው ከውውይቱ ተሳታፊዎች ዘንድ ተነስቶላቸው ከነበረው ጥያቄ ላይ በተለይ ሁለት ግለሰቦች ያቀረቡትን ማስታወስ ለኔ መጣጥፍ ርዕሰ ጉዳይ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡እናም ከዚያን ቀኑ አስተያየት ሰጭዎች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ በለው የተባሉ ሰው “እኔ አቶ ካሳን ልጠይቃቸው የምፈልገው ጉዳይ ምንም እንኳን በቀጥታ እርሳቸው የሚመሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመለከት ባይሆንም ግን ደግሞ እንደ አንድ የዚህ መንግስት ከፍተና ባለስልጣን ሊመልሱልኝ ይችላሉ የሚል እምነት ስላለኝ ነው” ሲሉ ጀምረው የሰነዘሩትን የሰላ ሂስ ምን ይመስል እንደነበር አንስተንብናስታውስ መልካም ሆኖ ይሰማኛል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ አቶ በለው የተባሉት የሬዲዮ ጣቢያው የቀጥታ ስርጭት ጥያቄና መልስ ተሳታፊ ግለሰብ ንግግራቸውን የቀጠሉበት አግባብ “ስለዚህም ክቡር ሚኒስቴሩን የምጠይቃቸውም የእናንተ ባለስልጣናት ለትንሽ ለትልቁ የጤና ችግር ሁሉ የውጭ ህክምና ያስፈልገናል እያሉ ከመንግስት ካዝና ላይ እየተነሳ በሚታሰብ የህዝብ ገንዘብ ዓለምን ዞረው ሲመለሱ ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡በዚህ መልኩ ወጭ የሚደረገውን በርካታ ገንዘብ ለማወራረድ ሲጠየቁ እንኳን ፈቃደኛ ሆነው እንደማይገኙም ዋናው ኦዲተር ጭምር ለፓርላማ የሚያቀርበው ዓመታዊ ሪፓርት ያረጋገጠው ነገር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እኛ እየተራብን የምንከፍለውን የታክስና ግብር እናንተ እንደተራ ነገር እየቆጠራችሁ በዘፈቀደ እንደምታባክኑት የሚያሳይ ማን አለብኝነት እንጂ ሌላ አይደለም” የሚል ጠጣር ቅሬታ ያዘለ ሀሳብ መሰንዘራቸውን አድምጫለሁና ነው፡፡
የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን “ቆይታ ከሚሚ ስብሐቱ ጋር” በተሰኘው የዛሚ ሬዲዮ ሳምንታዊ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ለአድማጮች የስልክ ጥያቄ ምላሽ የሰጡበትን ውይይት የተከታተላችሁ ወገኖች እንደምታስታውሱት፤እኚሁ አቶ በለው የተባሉ ሰው “የሚገርመኝ ነገር ደግሞ ኢህአዴግ ደርግን ለመውቀስ ሲሞክር መሰማቱ ነው፡፡ እንዴ! በደርግ ጊዜ እኮ እንኳን ሀገር ውስጥ መታከም እየተቻለ ከመንግስት ካዝና በሚመዘበር የህዝብ ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሄዱ የሚፈቀድላቸው ባለስልጣትን ልናይና እሁድ ቅዳሜን ስራ ስለሌለ ሁሉም የመንግስት መኪናዎች ቁልፋቸውን እያስረከቡ በአንድ የጥበቃ ማዕከል እንዲቆሙ የሚደረግበት አሰራር ነበር? ያን ማድረግ ያስፈለገውም ደግሞ በህዝብ ገንዘብ እየተገዛ የሚመጣው ነጃጅ ለባለስልጣናት የግል ጉዳይ ሶደሬና ላንጋኖ እየተሄደበት እንዳይባክን ሲባል ነው” ሲሉ ነበር ቅሬታቸውን አጠንክረው የገለፁት ፡፡
ከእርሳቸው ቀጥሎ በቀጥታ ስርጭቱ አየር ላይ ገብተው የስልክ ጥያቄያቸውን ለክብር ሚኒስቴሩ ሌላ አድማጭም እንዲሁ “ይቅርታ ይደረግልኝና እኔ ራሴም የአሁኑ ተናጋሪ ባቀረቡት ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ እስማማበታለሁ ሚሚ” ሲሉ ጀምረው የአቶ በለውን ትችት ለማዳበር እንደሞከሩ ትዝ ይለኛል፡፡እኚሁ የመዲናችን ነዋሪ ግለሰብ “ እንዲያውም የሌላ አይምሰልብኝ እንጂ አአንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ይልቅ ከደርግ ዘመን የማውቃቸው የኢ.ስ.ፓ. ካድሬዎች ለህዝብ ያስቡ ነበር ማለት ይቻላል” የሚል አስተያየት እንዳከሉም አድምጫለሁ፡፡
ስለዚህም እኔ በግሌ ሁለቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ግለሰቦች ኢህአዴግ መራሹን ፌደራላዊ የአፈና አገዛዝ ጋር ለማነፃፀር የሞከሩበትን አግባብ ባልቀበለውም፤አስተያየታቸው በከፊል እውነትነት እንዳለውና እርሱን በቀና መንፈስ ወስደን ልናርመው የሚገባን ስህተት ስለመኖሩ ግን አምናለሁ፡፡ይህን ስልም ደግሞ፤እውን ደርግ ከኢህአዴግ ይልቅ ለህዝብ ሀብት ንብረት የሚያስብና የሚጨነቅ መንግስት ነበርን?የሚለውን ማስፈራሪያ ወደጎን ትተን፤በዛሬዋ ፌደራላዊት፤ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ውስጥ መናበብ ካለመቻል የሚመነጩ ችግሮቻችን መገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱት አስተዳደራዊ ድክመቶች መካከል ምናልባትም ዋነኛው ጉዳይ፤የመንግስት ሀብት ንብረት ሲባክን የሚስተዋልበት ጥሬ ስለመሆኑ ግን የሚካድ አይደለም ማለቴ ነው፡፡
ይሄም ለማስተባበል የማያመች ሀገር አቀፋዊ የጋራ ድክመታችን አምኖ ለመቀበል የሚቸግር የመንግስት አካል ካለ ደግሞ፤በየተቋማቱ ቅጥር ግቢ እየዞረ ገና በቅጡ አገልግሎት መስጠት ሳይችሉ በየጥቃቅኑ ብልሽት ምክንያት እንደዘበት ቆመው የቀሩ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ፤ኮፒውተርና መሰል አላቂ እቃዎችን የምንይዝበት አጠቃላይ እውነታ ምንኛ ሃላፊነት የጎደለው እንደሆነ መመልከት የሚችል ይመስለኛ፡፡ከዚህ አኳያ የሚስተዋለውን ችግር ደረጃ በደረጃ ለማስቀረት የሚያስችል ትርጉም ያለው የተጠያቂነት አሰራር የማስፈን ጉዳይ ተገቢ ትኩረት እስካልተሰጠው፤የነ አቶ በለው ቅሬታ መላውን ህብረተሰብ የሚያሳምን ወደ መሆን ከፍ እያለ ላለመሄዱም ምንም ዓይነት ዋስትና አይኖረንም፡፡
ደግሞ እቺን ሀገር ስር ከሰደደው ድህነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ ያለው ፈርጀ ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ በምንገኝበት ወቅት ካለቺን ውስን ሀብት ንብረት መካከል አብዛኛው ላለአስፈላጊ ብክነት ሲዳረግ በቸልታ መመልከት ማለት፤የልማት ጉዟችንን የህልም ሩጫ ዓይነት እንዲሆን ሊያደርገው የሚችል አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ ይቀራልን? ስለዚህ እንደኔ እምነት ከሆነ በፁሁፌ ለማመላከት የተሞከሩትን መናበብ ካለመቻል የሚነጩ የጋራ ችግሮቻችንንና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ተያያዥ ባህሪ ያላቸው ድክመቶች ለማረም የሚያስችል የተጠያቂነት አሰራርን በሀገር አቀፍ ደረጃ የማስፈን አስፈላጊነት ፈፅሞ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው የሚለውን ነጥብ ልናሰምርበት ይገባል፡፡ በተረፈ ግን ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy