Artcles

መንገድና መንገድ !!

By Admin

May 08, 2017

መንገድና መንገድ  !!

         ይነበብ ይግለጡ

መንግስት በሀገራችን ቀድሞ የነበሩትን ብዙም የማያወላዱ መንገዶች ሙሉ በሙሉ በመቀየር አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እንዲስፋፉ ማድረጉ ሀገሪቱን የጀመረችውን ፈጣን እድገት ከማፋጠን አንጸር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ከመዲናችን አዲስ አበባ ጀምሮ በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል የነበረው መንገድ ጠባብና እንደልብ ለመንቀሳቀስ የማያስችል የነበረ ሲሆን ባለፉት በርካታ አመታት ለመንገድ ስራ መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የሀገሪቱ ዘመናዊ የመንገድ ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማደግ የቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሶአል፡፡

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የነበረው የጥርጊያ መንገድ በበርካታ አካባቢዎች በዘመናዊ አስፋልቶች የተሸፈነ ሲሆን አሁንም ብዙ መስራት ይቀረናል፡፡ በመንገድ ዘርፍ ሀገሪቱ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ዘመናዊና ምቹ አስፋልቶችን ሰርታለች፡፡ይህም ክልሎችን ከክልል በውስጥ ደግሞ አካባቢዎችን ከአካባቢዎች በጣም አጭር በሆነ ሰአትና ጉዞ እንዲገናኙ ለማድረግ አስችሎአል፡፡የአስፋልት መንገዶችን ብቻ ሳይሆን የባቡር መንገዶች የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ስራዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡

ለትምህርት ለጤና ለንግድ ግብይትና ልውውጥ መንገድ የሚያስገኘው ጠቀሜታ የላቀና የገዘፈ ነው፡፡ ቀድሞ በሁለትና ሶስት ቀናት በመኪና ጉዞ ይገባበት የነበረውን ርቀት ዛሬ በአንድ ቀን ማድረግ የተቻለው ምቹ መንገዶች በመሰራታችው ነው፡፡ ለሀገሪቱ ኢንቨስትመንትም ማደግ ያለው ድርሻ የላቀና ጎላ ነው፡፡ ያለመንገድ ልማት እድገት ስልጣኔ የለም፡፡ መንገድ የሀገርን ሕይወት በትልቁ የሚለውጥ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቀራርብ የሚያገናኝ ትልቅ ድልድይ ነው፡፡

ዛሬ በሀገራችን ውስጥ ከመቸውም ግዜ የላቀና የበለጠ የመንገድ ግንባታ ስራ ተሰርቶአል፡፡ በመሰራትም ላይ ይገኛል፡፡ሀገራችን ለመንገድ ስራ ያዋለችውና ያፈሰሰችው ሀብት በየትኛውም መስክ ከተደረጉት ወጪዎች ሁሉ ሊበልጥ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የመንገድ ስራ ወጪው የገዘፈና ወድ የሚሆነው በካሬሜትር ስለሚሰላ አንድ ኪሎሜትር አስፋልት ለመስራት በብዙ መቶ ሺዎች ብር ወይንም ከዚያ በላይ ሊጠይቅ ስለሚችል ነው፡፡የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ከመንገድ ስራው ጋር አብሮ ግምት ውስጥ ይገባል፡፡ ከመንገድ ስራ መስፋፋት ጋር በተለይ በአዲስ አበባ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ስንትና ስንት የመንግስትና የሕዝብ ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት የተሰራውን ዘመናዊ መንገድ በተለያዩ ግዜያት እየቆፈሩ አስፋልቱን እያፈረሱ ያሉት የመንገድ ስራ ክፍሎች ጉዳይ አነጋጋሪ  እየሆነ መጥቶል፡፡

አንዱ ሰርቶ አሳምሮ ይሄዳል ሌላው መጥቶ ያፈርሰዋል፡፡ በዛም ተባለ በዚህ የሚወጣው የሀገሪቱ ሀብትና ገንዘብ ነው፡፡እንደዚህ መቀለጃ መጫወቻ ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡ይሄንኑ ስራ የሚሰሩትም ተቋማት የመንግስት ናቸው፡፡ውኃ ክፍል መብራትኃይልና ቴሌኮሚኒኬሽን ተናበው መስራት አስቀድመው በጋራ ቁጭ ብለው ማቀድ የከተማዋን የ30 እና አርባ አመት የስርጭት ማስፋፋት ቀድመው በመስራት የሀገሪቱን ገንዘብ ከጥፋትና ከውድመት ሊታደጉት ይገባ ነበር፡፡

በረዥሙ ማቀድ ማስላት የውኃ ስርጭት መብራትና የቴሌ ስርጭት እያደገና እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት መስራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡በዚህ ረገድ ደግሞና ደጋግሞ ተሰርተው ያለቁትን መንገዶች በተለያዩ ግዜያት መልሶና መላልሶ መቆፈሩ በሀገር ሀብት በሰው ጉልበትም የመቀለድ ያህል ተደርጎ ነው በሕብረተሰቡ ዘንድ እየተወሰደ ያለው፡፡ይሄም ብቻ አይደለም የሚፈልጉትን ስራ ከጨረሱም በኃላ ቀድሞ እንደነበረው አስተካክለው ሰርተው አይሄዱም፡፡ እንደተበላሸ ሳይጠገን ይቀጥላል፡፡ይሄም ከክረምቱ መግባት ጋር ውሀ በማቆር ፍሳሽን በመዝጋት ወደ አስፋልቱ በመፍሰስ በጤና ላይ ችግሮችን ማስከተሉን ይቀጥላል፡፡

መንግስታዊ አካላቱ ተናበው ቢሰሩ ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር አይከሰትም ነበር፡፡አሁንም ይህ ችግር የከፋ ችግር ሆኖ ቀጥሎአል፡፡ የመንገዶቹ ባለቤት መንግስትና ሕዝብ ናቸው፡፡ለስራው ሂደት ደግሞ የሚመለከተው የመንገዱን ስራ የሚመራው ክፍል አለ፡፡ሊታሰብበት የሚገባው ያልተፈታ ችግር ነው፡፡

የሚፈሰው የመንግስትና የሕዝብ ገንዘብ ከድሀ ሀገር ካዝና የሚወጣ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ጨዋታ እንዳይሆን  ትኩረት ያሻዋል፡፡  

በሀገራችን የመንገድ ማስፋፋት ስራ ከፍተኛ ሀገራዊ ልማትና እድገትን የሚያስገኝ ሲሆን በቅርቡ ስምንት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የመንገዶች ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ስራ ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል፡፡468 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ሰባት የመንገድ ኘሮጀክቶችን ለመንገባትና ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ የኮንትራት ስምምነቶች መፈረማቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጾአል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ የሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆኑና በአራት ክልሎች የሚገነቡ ደረጃቸው የሚያድጉ መሆኑን የኮንትራት ስምምነት ከተፈረመባቸው መንገዶች ውስጥ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙትን የዳዬ – ጪሪ – ናንሰቦ፤ መነቤኛ – ፍቼ – ሻንቦ እና የጭኮ-ይርጋ ጨፌ እና በሶማሌ ክልል የሚገኘውን የጂጂጋ -ገለልሽ – ደገሕመዶ-ሰገግ መንገዶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ባለስልጣኑ ገልጾአል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚገኙት የሙከጡሪ – አለም ከተማ የመጀመሪያ ኮንትራት የሆነውን ሙከጡሪ – ኮከብ መስክ፣ የአለም ከተማ – ድጎሎ እና የድጎሎ – ከለላ የመንገድ ኘሮጀክቶችን በአስፋልት ደረጃ የመገንባትና የማሳደግ ሥራዎችም በስምምነቱ ውስጥ መካተታቸው ለረዥም ግዜ በበቂና ዘመናዊ የመንገድ እጦት ሲቸገር የነበረውን የአካባቢውን ነዋሪ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

የዘመናዊ መንገድ ስራ መስፋፋት የሀገር ኢኮኖሚ እድገት መሰረትም ነው፡፡በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰሩ ግለሰቦች ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያደርሱ ያስችላቸዋል፡፡ሌሎችም በዚሁ በመበረታታት በአካባቢው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተነሳሽነትን ያሳድጋል፡፡የጤና ፣ የትምህርት የማሕበራዊ አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን ያስችላል፡፡ለዜጎች ሰፊ የስራ መስክ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

የሚሰሩት አዳዲስ መንገዶች በፍጥነት አልቀው ወደስራ እንዲገቡ መንግስትና ሕዝብ የተቀናጀ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡አንዳንዶቹ መንገዶች ተጀምረው ለአመታት የማያልቁበት ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከሙስና ችግሮች ጋር የተቆራኙ ችግሮች ሲታዩባቸው የነበሩ መሆኑን ሕዝቡ ይናገራል፡፡

ስራውን መከታተልና ዳር ለማድረስ የሕዝቡም የመንግስትም የተቀናጀ አሰራር ሊኖር ይገባዋል፡፡ስራው ሲቆም ለምን ብሎ መጠየቅ ቶሎ መፍትሄ ማስገኘት ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

አዳዲስ መንገዶች የመስራት ነባር መንገዶችን የመጠገንና የማስፋፋት ስራ በሰፊው እየተካሄደ ሲሆን ክትትልና ቁጥጥርን የሚጠይቅ ነው፡፡ይሰራል ብቻ ሳይሆን ስራው ምን ላይ ደረሰ ምን ያህልስ ይቀረዋል ብሎ ማየት መጠየቅ ለምን ዘገየ ማለት ከኃላፊዎች የሚጠበቅ ግዴታና የሕዝብ አደራ ነው፡፡  ›

ከጥገና ጋር ተያይዞ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በገለጸው መሰረት የአባይ ድልድይ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱና በማርጀቱ እድሳት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ያስጠግነዋል፡፡ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ የሆነው የቻይናው ኩባንያ ሲሲሲሲ ስራውን እንዲሚያከናውን ታውቋል፡፡እድሳቱ በሶስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

የአባይ ወንዝ ድልድይ ለረዥም ዘመናት ያገለገለ ከመሆኑ የተነሳ ያልታሰበ ችግር ሊፈጥር ይችል የነበረ ሲሆን እንዲታደስ መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ዘለቄታ ያለው አዲስ ድልድይ ለመገንባት የመነሻ ጥናት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከአንድ ወር በኋላ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት የባሕርዳርን ከተማ የሚመጥንና የሚወክል ዘመናዊ ድልድይ ለማስገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ባለስልጣን መስሪያቤቱ መግለጹ አበረታች ውጤት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መንገዶችን የመጠገንና የማስፋፋት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአጠቃላይ በ5 ቢሊዮን ብር ወጪ አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን  ለማከናወን  የኮንትራት ስምምነቶችን ቀደም ብሎ ፈርሞአል፡፡አምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 357 ኪሎሜትር እርዝማኔ ያላቸው ሲሆኑ  መንገዶቹም የጭዳ -ሶዶ ሶስተኛ ኮንትራት ፣ የጨርቲ -ጎርቦክሳ- ጎሮዳሜ ፣ የፊቅ -ሀመሮ -ኢሚ ኮንትራት አንድ ፣የጊኒጪ-ካቺሴ -ጩሉቲ ኮንትራት አንድ እና የፓዊ መገንጠያ-ሕዳሴ ግድብ መሆናቸውን ገልጾአል፡፡

በዘንድሮው የበጀት ዓመት ባለሥልጣኑ ግንባታቸውን ለማስጀመር ካቀዳቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በአጠቃላይ በ13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወኑ 18 ፕሮጀክቶች ለአሸናፊ ድርጅቶች መሰጠታቸውን የባለስልጣኑ ዋናዳይሬክተር ማስታወቃቸው መንግስት በመንገድ ማስፋፋት ረገድ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሄደበትን ረዥም ርቀት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ከሚሰሩት መንገዶች ውስጥ ከዚህ ቀደም ምንም  የመሠረተ ልማት ባልነበረባቸው አከባቢዎች  በአስፓልት ደረጃ የሚገነቡም ይገኙባቸዋል፡፡