Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንጋው” አፉን እንደከፈተ ቀረ

0 372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“መንጋው” አፉን እንደከፈተ ቀረ♦…!
ዘአማን በላይ
ይህን ፅሑፍ የሚያነብ ማንም ሰው ርዕሱን እንደተመለከተ በቅድሚያ ወደ አዕምሮው የሚመጣው ነገር፤ ‘መንጋው ማን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይመስለኛል። አዎ! “መንጋው” በነጠላው አንድ፣ በድርብ ደግሞ የጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ነው። በአንድ ግለሰብነት፤ ለባዕዳን ተሰልፎና አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ፓውንዶችን በባንዳነት ተቀብሎ ዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም ለዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በተወዳደሩበት የመጨረሻ ዕለት በሚያስገርም ሁኔታ ድምፅ መስጫ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ላንቃው እስኪተረተር ድረስ ያላዘነው ዘላላም ተሰማን የመሰለ ግለሰብን ይወክላል። ነገሩ የሀገሬ አርሶ አደር “ውሻ በበላት ይጮሃል” እንደሚለው ዓይነት መሆኑ ነው። ግና የዚህ ባንዳ እና በትምክህተኝነት የተሰለፈ ሰው ከንቱ ጩኸት በጭንጫ ምድረ በዳ ላይ እንደተዘራ እህል የሚቆጠር ነው—አይበቅልምና። “መንጋው” ሌላኛው ትርጓሜ የጠባብና የትምክህት ቡድኖችን በሚያንቀሳቅሱ ጥቂት ግለሰቦችን የሚወክል ነው። እነዚህ ቡድኖችና በውስጣቸው የታቀፉት ጥቂት የዲያስፖራ አባላት በአሸባሪዎቹ ግንቦት ሰባት እንዲሁም ኦነግ ውስጥ የተሰገሰጉ፣ ለኤርትራና ለሌሎች የሀገራችን ጠላቶች ባንዳ ሆነው የተሰለፉ ናቸው። አስቂኙ ነገር፤ ከቡድኖቹ ውስጥ ግንቦት ሰባት የተሰኘውና በኤርትራ መንግስት አንዴ ‘ከእገሌ ጋር ተጣበቅ’፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እገሌ ከሚባለው ጋር ተለያይ’ እየተባለ የራሱን ቅርፅ ሳይዝ እየተሰፋ የሚቀደደው ባንዳ ኃይል የዶክተር ቴዎድሮስን የምረጡኝ ቅሰቀሳ ለማደናቀፍ መግለጫ ጭምር በማውጣት ያልቧጠጠው ነገር ባለመኖሩ ነው።
የአስቂኙ መግለጫ ጭብጥ “አፍሪካዊያን ለምን ለዶክተሩ ድምፅ ይሰጣሉ?” በማለት ዘረኛና ከአቅም በላይ ተንጠራርቶ የሀገራችንን መልካም ስምና የዶክተሩን የካበተ የዕውቀት ስብዕና ለማጠልሸት የተዘጋጀ የጭፍን ጥላቻ አባዜ ነው። ይህ አባዜም ድምፅ ሰጪዎቹ እዚህ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በማበብ ላይ መሆኑን ስለሚያውቁ እንዲሁም እንዲህ ዓይነቱ ጠባብና ዘረኛ አስተሳሰብ በቅኝ ገዥዎች ዘመን የቀረና አፍሪካዊያንም ይህንኑ የተዋጉ ስለሆኑ ጆሯቸውን የሚሰጡት አይደለም። ይልቁንም የተቃውሞውን ጀሌ ትዝብት ላይ የሚጥለው ነው።
ኢትዮጵያዊነትን በጥቅም ሸጦ በባዕዳን ጀሌነት የተንቀሳቀሰው “መንጋ” ተቃውሞ ከአፍሪካዊያንን የፓን አፍሪካኒዝም ህብረት እሳቤ እንዲሁም ለባዕዳን አድሮ ድምፅ የመስጠት መብታቸውን በገሃድ የተጋፋ በመሆኑ አፍሪካዊያንን የሚያሳንስ ብሎም ለነጮች የተንበረከከ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊ ለሚያስብ ሰው ትንሽነቱ ያሸማቅቃል። እውነቱን ለመናገር እኔ በ“መንጋው” ቦታ ሆኜ ላፍር ተገድጃለሁ። ርግጥ ይህ የ“መንጋው” የቁራ ጩኸት ተቃውሞ ከመሳለቂያነት ውጭ ያተረፈው ነገር የለም። የእኛው ጉድ “መንጋው” በቅድሚያ ኢትዮጵያዊነትን፣ ለጥቆም አፍሪካዊነትን ከፍ ሲልም ዶክተሩ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ተወካይ ሆነው ሲያበቁ፤ በባንዳዊ አስተሳሰብ ‘ዶክተር ቴዎድሮስ ለምን ይመረጣሉ?’ ብሎ የተነሳ አሳፋሪ ስብስብ ሆኖ መቀለጃ ሆኗል። የከፈተውን አፍ እንኳን ሳይዘጋ በዚያው በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ጎዳናዎች ላይ እንደከፈታቸው በመጣለበት እግሩ በቅሌት ተመልሷል።
የ“መንጋው” ዓላማ ትምክህት የወለደው “ሆድ አደርነት” ብሎም ፀረ-አፍሪካዊነት በመሆኑ ሊሳካ አልቻለም። እናም በግለሰብና በቡድን ተደራጅቶ ጄኔቫ ላይ አፉን እንደከፈተ ሊቀር ችሏል። ርግጥ እኔ ያለሁት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብት ጥረት በሚደረግባት፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ ዓይነት ምሁሮች በየዩኒቨርስቲው እየበቁ ባሉባት፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በይሁንታቸው ፌዴራላዊ ስርዓትን ገንብተው እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚገነቡባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ፤ በ“መንጋው” የተከፈተው አፍ ውስጥ ምን እንደገባበት ለማየት አልቻልኩም። ግና በቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ እንዳየሁት ከሆነ፤ የተከፈተው አፍ ሳይዘጋ ተከፍቶ ቀርቷል። ምናልባትም የጄኔቫ ዝንብ አሊያም በረዶ ገብቶበት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከዝንብ ማር መጠበቅ ስለማይቻል፤ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ባንዳዎች ማቅ ለብሰው፣ ማቅ መስለውና የሃፍረት ካባን ተከናንበው ወደ መጡበት ተመልሰዋል። አዎ! “መንጋው” አፉን እንደከፈተ ቀርቷል…!
ወትሮም ቢሆን ውሸት እንኳንስ በአስር ሺህዎች ፓውንድ ቀርቶ፤ በቢሊዮኖች ፓውንድም ቢደገፍ ያው ሐሰት ነውና ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር በቋሚነት የእውነትን አጥር ጥሶ ሊገባ አይችልም። እናም የ“መንጋው”ን አሳፋሪና የውርደት ማንነት ያወቁት የየሀገራቱ ድምፅ ሰጪዎች በተገላቢጦሽ ድምፃቸውን ለትናንቱ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ተወካይ፣ ለአሁኑ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም ሰጥተዋል። ባንዳነትንም እንደምን እንደሚፀየፉት አሳይተዋል። ዶክተሩ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በርግጥም “ድሉ የእኛ ነው” እንዳሉትም፤ በከፍተኛ የድምፅ ብልጫ የምርጫው አሸናፊ መሆን ችለዋል። ይህ ለ“መንጋው” አሳፋሪ ሽንፈት ብቻ ሳይሆን፤ የሚያራምደው አስተሳሰብ ከአዲሷ ኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ምን ያህል የዘቀጠ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ “መንጋው” የከፈተውን አፍ እንዳይዘጋ ያደረገው፤ ዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም በተወዳደሩበት 70ኛው የዓለም የጤና ጉባዔ በተካሄዱት የሶስት ዙር ፉክክሮች፤ በመጀመሪያው ዙር 95 ድምፅ አግኝተው ፓኪስታናዊቷን ዶክተር ሳኒያ ኒሺታር ለሁለተኛው ዙር እንዳያልፉ በማድረግ እንዲሁም በቀሪዎቹ ዙሮች ተቀናቃኛቸው የነበሩትን እንግሊዛዊውን ዶክተር ዴቪድ ናባሮን 133 ለ 50 በሆነ ሰፊ የድምፅ ልዩነት በመዘረር የድርጅቱ መሪ እንዲሆኑ መቻላቸው ነው። እናም ይህ ሃቅ “መንጋው” እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ ከማድረግ ባሻገር፤ በድንጋጤ አፉን ከፍቶ እንዲቀር አድርጎታል።
ሌላኛው “መንጋው”ን አፉን አስከፍቶ ያስቀረው ጉዳይ፤ በአሉባልታ ያሰራጨው የፈጠራ ወሬ ውሃ የበላው ስለሆነ ነው። “መንጋው” በተቃራኒው እንደሚያወራው ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ልማትን የሚያፋጥን፣ ሰብዓዊ መብትን የሚያከብር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚተጋ እንዲሁም የህዝቦች እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያከበረ መንግስት መኖሩን ዓለም እውቅና እንደሰጠው የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በእኔ እምነት ዶክተር ቴዎድሮስ በምርጫው ያሸነፉት ሀገራችን በእርሳቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ወቅት በዘርፉ ላስመዘገበችው ውጤት ሽልማት ነው።
ርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ በቀየሳቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካኝነት ሀገራችን ውስጥ የእናቶችንና የህፃናት ሞትን እንዲሁም የወባ፣ የቲቢና የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታዎች ስርጭት እንዲቀንሱ በማድረግ ብሎም የልጅነት ልምሻ በሽታን በመከላከል ዓለም የሚያውቀው ስኬታማ ተግባሮች ተከናውነዋል። በዘርፉም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምዕተ-ዓመቱን የልማት ግቦች አስቀድማ ማሳካት ችላለች። ዶክተር ቴዎድሮስ ደግሞ እነዚህ ውጤቶች እንዲገኙ አመራር በመስጠት ለውጥ ያመጡ ምሁር ናቸው።
በዚህ ብቃታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደማጭነትን ማግኘት የቻሉና የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ምርጥ ልጅ ናቸው። የዶክተር ቴዎድሮስ አቅም የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ህዝቦችና የዓለም አቅም ነው። በእኔ እምነት ዶክተር ቴዎድሮስ የመመረጣቸው ምስጢር፤ ውስብስብ የጤና ችግር የነበረባት ኢትዮጵያን በመንግስት ልማታዊ ፖሊሲዎች አማካኝነት ተመርኩዘው ውጤት ማምጣት የቻሉ የስራ መሪ በመሆናቸው፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቢሆኑ ያላቸውን ተሞክሮ በመጠቀም የዓለምን ችግር ይፈታሉ አሊያም እንዲፈቱ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚል ትክክለኛ እሳቤ ነው።
ዳሩ ግን “መንጋው” በግለሰብና በቡድን ተደራጅቶ ጄኔቫ በሚገኘው አዳራሽ ፊት ለፊት አፉን የከፈተው ሌላው ቀርቶ በጤናው ዘርፍ ብቻ እነዚህን ዓለም ምስክርነቱን የሰጠባቸውን ለውጦች ያስመዘገበችውንና የአፍሪካዊያን ተምሳሌት በሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዲሁም ስራውን በመሩት ባለ ክህሎቱ ዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም ላይ መሆኑን እንኳን በቅጡ ቆም ብሎ ሊያጤነው አልፈቀደም። ይህ በመሆኑም በጭፍን፣ በጠባብነትና በትምክህት አስተሳሰብ እንዲሁም ክፋትና ምቀኝነትን ከባንዳነት ጋር ወገቡ ላይ ታጥቆ ማላዘኑ መልሶ ዋጋ ያስከፈለው ራሱን ነው— “የቅሌት ቀን አይመሽም” እንዲሉ አበው፤ “የመንጋው” አፍ እንደከፈተ ቀርቷልና!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy