Artcles

መከላከያ—የ“ትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫ

By Admin

May 26, 2017

መከላከያ—የ“ትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫ

                                                 ዘአማን በላይ

የዘንድሮው ግንቦት 20 የድል በዓል ለ26ኛ ጊዜ “የህዝቦች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት እየገነባች ያለች ሀገር—ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል። በዚህ መሪ ቃል ውስጥ በዋነኛነት ‘የህዝቦች እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ፌዴራላዊ ሥርዓት እና ኢትዮጵያ’ የተሰኙ ቁልፍ ቃላቶች አሉ። እነዚህ ቃላቶች አዲሲቷ ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት በተጓዘችበት የአስተማማኝ ሰላም፣ የፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጎዞዎች ማሳያዎች ይመስሉኛል።

ርግጥም ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም እስከ ህዳር 28 ቀን 1987 ዓ.ም ድረስ ለአራት ዓመታት ስራ ላይ ከነበረው የሽግግር መንግስቱ ቻርተር እንዲሁም መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መክረውበትና ዘክረውበት አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ቃል ኪዳን ያሰሩበት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እውን ከሆነበት ከህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ፤ መንግስትና ህዝብ ባከናወኑት ጠንካራ ርብርብ በመሪ ቃሉ ላይ የተጠቀሱት ቁልፍ ቃላት እውን ሆነዋል።

አዎ! በተለይም በህገ መንግስቱ አማካኝነት እውን የሆነው ፌዴራላዊ ስርዓት ገቢራዊ ከሆነበት ካለፉት 22 ዓመታት ወዲህ የሀገራችን ህዝቦች አንዱ ከሌላው የበላይም ይሁን የበታች ሳይሆን በውድ የህዝብ ልጆች መስዕዋትነት ያገኛቸውን መብቶች ሁሉ በእኩልነት እያጣጣመ ዛሬ ላይ ደርሷል። ይህም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በእኩልነት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ ተችሏል። እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋም በግንቦት 20 ምክንያት እውን በሆነው ህገ መንግስት ውስጥ በተደነገጉ መሰረታዊ መብቶች አማካኝነት የተገኙ የዕድገት ውጤቶች በየደረጃው በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ሆኗል። ይህም የሀገራችን ህዝቦች ይበጀናል ብለው በጋራ ያቋቋሙት ፌዴራላዊ ስርዓት ትሩፋት ነው።

ታዲያ ስለ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ትሩፋቶች ስናነሳ፤ የህዝቦች ሁለንተናዊ መብቶችና ፍትሐዊ ተጠቃሚነቶች እንዲረጋገጡ ከህዝቡና ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በህዝባዊነት፣ በጀግንነትና በዓላማ ፅናት እየተወጣ የሚገኘው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አብሮ ሊታወስ የሚገባ ይመስለኛል።  በአንድ ሀገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ከሌለ፣ ስለ ፈጣንና ተከታታይ ልማት ብሎም ዘላቂነት ስላለው ዕድገት ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታም ማሰብ አይቻልም።

እናም በእኔ እምነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት ለተገኘው አስተማማኝ ሰላም በሽግግር መንግስቱ ወቅት የኢህአዴግ ሰራዊት፤ ከህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ከተመሰረተበት ከህዳር 1987 ዓ.ም በኋላ በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 87 በተቀመጡት አምስት መርሆዎች ተመርኩዞ እንዲሁም ነባሩን የኢህአዴግ ሰራዊት በእርሾነት ያካተተና የሁሉንም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦን የያዘ የመከላከያ ኃይል በ1988 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 27/88 እንደ አዲስ እንዲደራጅ የተደረገው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በህዝቡ የማይነጥፍ ድጋፍ እየታገዘ ውጤታማና አኩሪ ተግባራትን አከናውኗል። ከአፍሪካዊያን ህዝቦች ባገኘው ህዝባዊ አመኔታም ከራሱ ሀገር አልፎ የጎረቤቶቹ ሰላም ጠባቂና ተንከባካቢ ሊሆንም ችሏል።

በዚህ አጭር ፅሑፍ ላይ የሰራዊቱን በህዝባዊ ወገንተኝነትና በጀግንነት እንዲሁም በፅናትና በዲሲፕሊን በሀገር ውስጥና በውጭ ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። የተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይም የሰራዊቱ “የትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫ መሆኑን ማሳየት ስለሆነ፤ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 87 ከተደነገጉት መርሆዎች ውስጥ ንዑስ አንቀፅ አንድን ብቻ በመመልከት የግሌን ዕይታ ለአንባቢያን ለማብራራት እሞክራለሁ። በዚህ ንዑስ አንቀፅ “የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል” የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል። ይህ ድንጋጌ በሰራዊቱ ውስጥ እየተሰራበት መሆኑን ከሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ እምነት በመነሳት መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል።

አንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም እነርሱ ተፈቃቅደው በመሰረቱት ህገ መንግስት ከተሰጠው ተልዕኮዎች ውስጥ አንዱ፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማናቸውም የውስጥና የውጭ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጥቃት መከላከል ነው። ይህ ተልዕኮ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ማስከበር ብቻ ሳይሆን፤ ሰራዊቱ ራሱ ማክበር እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው።

በዚህ ረገድ ላለፉት ዓመታት መከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን ከማክበር በዘለለ፤ በህገ መንግስቱ ላይ ፅኑ እምነት ይዟል። ለዚህም ከራሱ ዴሞክራያዊ እሴቶች ውሰጥ “ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር” የሚለውን እሴት ስንመለከት፤ መከላከያ ሰራዊቱ ከራሱ ህይወት፣ መብትና ጥቅም ይልቅ ለህዝብ ፍላጎት፣ መብትና ጥቅም የቆመ እንዲሁም ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅምና ዳር ድንበር መከበር መስዕዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ ኃይል መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

በመሆኑም ሰራዊቱ ህገ መንግስቱ በሀገራችን ህዝቦች መስዋዕትነት የተገኘና ህዝቡም ለመከላከያ ተግባሩን ዘርዝሮ እንደሰጠው የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን፤ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎቶችን ለማክበር የገዛ ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተሰለፈ ኃይል ነው። ለህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ህይወቱን ለመስጠት የተሰለፈ ኃይል ደግሞ በምንም ዓይነት ስሌት ህገ መንግስቱን አያከብርም ተብሎ ሊታሰብ አይችልም።

እናም የህዝቦች ፍላጎት የሆነውና በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገገው የተዋፅኦ ጉዳይ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በቁርጠኝነት እየተሰራበት ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። በዚህም ዛሬ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ገብቶ የሰራዊቱን ስብጥር ለመመልከት የሚሻ ማንኛውም ሰው፤ “ትንሿን ኢትዮጵያ”ን ማየቱ አይቀርም። ህብረ-ብሔራዊነት ምን ማለት እንደሆነም ይገነዘባል። ስብጥሩ ደማቅ ህብርን የሚፈጥርና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ነፀብራቅ መሆኑን ካለ አስረጅ መረዳቱ አይቀርም።

ይህ ህብረ-ብሔራዊ ሰራዊት በአንድ ላይ የሚኖር፣ በእኩልነት መርህ የሚመራ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት በተቋሙ ውስጥ በሚገኙ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች አቅሙን በየጊዜው የሚያጎለብት እንዲሁም በጀትን አብቃቅቶ በመጠቀም የሀገሪቱ ዕድገት በሚፈቅደው መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆን ነው። ታዲያ ይህን እውነታ የሚገነዘብ ማንኛውም ሰው፤ የዚህ ለህዝብ የወገነ፣ ጀግና የሆነ፣ ከብረት የጠነከረ ህገ መንግስታዊ እምነት ያለውና በዲሲፕሊን የታነፀ እንዲሁም በወታደራዊ ሳይንስ እውቀቱን እያጎለበተ ያለ ሰራዊት አባል መሆን የሚመኝ ይመስለኛል—ከብሔራዊ ሚዛናዊ ተዋፅኦው ትግበራ ባሻገር ማለቴ ነው።   

እናም መከላከያ እንደ ተቋም ላለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት እየፈጠረ ያለው ሚዛናዊ ተዋፅኦን የመፍጠር አመርቂ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በእኔ እምነት የውትድርና ሙያ በግለሰብ ደረጃ በልምድ የካበተ ክህሎትንና የጊዜ ቆይታን የሚጠይቅ በመሆኑ ባጠረ ጊዜ ውስጥ በሁሉም እርከኖች ሚዛናዊ ተዋፅኦን የመፍጠር ጉዳይ ያለ አንዳች እንከን ምሉዕ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። በመጀመሪያ ደረጃ የውትድርና ስራ ዳግም ሊገኝ የማይችለውን የሰውን ህይወት መምራት በመሆኑ፤ የማዕረግ አሰጣጡ እንደ ሌሎች የስራ ዘርፎች በሹመት ሊከናወን የሚችል አይመስለኝም።

እኔ በግሌ እንደሚመስለኝ ከሆነ ስራው ዘመናዊ የውትድርና ሳይንስን ዕውቀት የሚጠይቅ በመሆኑም አንድን ሲቪል ያለ አንዳች የውትድርና ክህሎት ሻለቃ ወይም ኮሎኔል በማድረግ ሰራዊትን እንዲመራ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። ምንም እንኳን ስለ ውትድርና ሙያ እውቀት ባይኖረኝም፤ እንዲያው ከራሴ እሳቤ ተነስቼ ሁኔታውን ስመለከተው ይህ ቢደረግ በሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም ላይ የራሱን ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ ሊቀር የሚችል አይመስለኝም። ታዲያ ይህን ሃቅ ለመረዳት ብዙም ምርምር የሚጠይቅ አይደለም—በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ሊፈጥር የሚችለው አደጋ ግልፅ ነውና። እናም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህን መሰል ችግሮችን ተቋቁመው የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መከላከያን ዛሬ ለደረሰበት የብሔር ተዋፅኦ ቁመና ማብቃታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል እላለሁ።

ርግጥ ይህ ውጤት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም። የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ተብሎም የተፈፀመ አይደለም—ተቋሙ፣ በየደረጃው የሚገኙት አመራሮቹና አባላቱ በህገ መንግስቱ ላይ ያላቸው የፀና አቋምና ታዛዥነት የፈጠረው ነውና። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ሰራዊቱ የሚከተላቸው እንደ “ምንጊዜም የተሟላ ስብዕና” እና “ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ” የተሰኙ እሴቶች መገለጫ ይመስለኛል። እናም በዚህ ሰራዊት ህገ መንግስታዊ እምነትና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሁላችንም ኩራት ሊሰማን ይገባል እላለሁ።    

ከተዋፅኦ አኳያ በሁለተኛ ደረጃነት ሊነሳ የሚገባው ነገር፤ በመከላከያ ውስጥ የሚሰጥ የማዕረግ ዕድገት የጊዜ ቆይታን መሰረት የማድረጉ ጉዳይ ይመስለኛል። አንድ የሰራዊት አባል ከመሰረታዊ ወታደርነት ቀጥሎ ያሉትን ማዕረጎች የሚያገኘው በተቋሙ ውስጥ ባለው የጊዜ ቆይታ ነው። ከወታደርነት ማዕረግ ተነስቶ፤ መካከለኛውን የመስመራዊ መኮንነትን አልፎ ወደ ክፍተኛ መኮንንነት ለመሸጋገር ብሎም የጄኔራል መኮንንነት የተለያዩ የእርከን ደረጃዎች ለመድረስ ዓመታትን ማለፍ የግድ ይለዋል።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ የሆነበት ምክንያት፤ በአንድ ሰራዊት ውስጥ የቆይታ ጊዜ፤ የውትድርና ልምድን፣ ዕውቀትን፣ የውጊያ ክህሎትን፣ ሰራዊት የማደራጀት የመምራት ብቃትን እንዲሁም ስነ ልቦናዊና ሞራላዊ ዝግጁነትን ከፍ የሚያደርግ ነው። ርግጥ እንኳንስ ለህዝብና ለሀገር ሲባል የህይወት መስዋዕትነትን መክፈልን በሚጠይቀው በውትድርና ሙያ ውስጥ ቀርቶ፤ ይህን መሰሉ ግዳጅ በሌለባቸው የሲቪል ሙያዎች ውስጥም ቢሆን ከቆይታ የሚገኝ ሁለንተናዊ የካበተ ልምድ መኖሩ የሚያጠያይቅ አይደለም። ዕውነታው ወደ መከላከያ ሲመነዘር ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ ፅሑፍ አንባቢ የሚሰወር አይመስለኝም።

ያም ሆኖ ባለፉት ተቋሙና በየደረጃው የሚገኙት አመራሮቹ ህገ መንግስቱን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። በጎረቤቶቹ የሚታመን፣ ማንኛውንም ሀገራዊ ተልዕኮ በአነስተኛ ኪሳራ በላቀ ደረጃ መፈፀም የሚችል ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ ሰራዊት መፍጠር ችለዋል። ይህም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ውክልና የሚንፀባረቅበት እየሆነ ነው። ይህ በተቋሙ የሚደረግ ጥረት ወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል—እስካሁን የተከናወኑት ተግባሮች መጪውን ሁኔታ የሚያመላክቱ ናቸውና።