Artcles

መገናኛ ብዙሃን ልሳነ-ህዝብ ሊሆኑ ይገባል!

By Admin

May 07, 2017

መገናኛ ብዙሃን ልሳነ-ህዝብ ሊሆኑ ይገባል!  /ቶሎሳ ኡርጌሳ/

                 በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚገኝ መገናኛ ብዙሃን የሀገሩ ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ትስስር አላቸው፡፡ ባለቤትነታቸውና ሚናቸውም የሚወሰነው በሥርዓቱ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የአንድ ሀገር መገናኛ ብዙሃን የሥርዓቱ ነጸብራቅ ናቸው ማለት ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችንን የቅርብ ጊዜ ትውስታን ስንመለከት፤ ሁለት የተለያዩ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ሥርዓቶችንና የመገናኛ ብዙሃን ሚናን እናገኛለን፡፡ የደርግና የኢፌዴሪ መንግሥትን፡፡  እንደሚታወቀው ወታደራዊው መንግስት ከሚከተለው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ሥርዓት አኳያ ሃሳብንና አመለካከትን በነጻነት የመግለጽ መብት ተገድቦ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡

በዘመነ ደርግ የመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤትነትም በመንግስት ብቻ ከመያዙ ባሻገር፤ የቅድመ ምርመራ ህግም ዋነኛው የማፈኛ ዘዴ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን ሚና በዋነኛው የሀገራዊው ድህነትንና ኋላቀርነት የመቅረፍና ለህዝብ የዴሞክራሲ መብቶች መከበር የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ በሥርዓቱ ህልውና ቀጣይነት ላይ ሚያተኩር የፕሮፓጋንዳ ሥራ ተጠምዶ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የደርግ መንግስትን መገርሰስ ተከትሎ የተፈጠረው የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ሥርዓት ነፀብራቅ የሆነ መገናኛ ብዙሃን አሰራር መዘርጋት ተችሏል፡፡ በዚህም ለዘመናት የተሻገረው የፕሬስ ነጻነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፡፡ የቅድመ ምርመራ አሰራርም አክትሟል፡፡ ሀገሪቱ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት አቅጣጫን በመከተሏ በመንግስት ብቻ ታጥረው ከቆዩ ሚዲያዎች ይልቅ በብዙ እጥፍ የሚበልጡ የግሉ የህትመት ሚዲያ ውጤቶችን መመልከት ተችሏል፡፡ በዚህም ዜጎች አመለካከታቸውንና ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ተከብሮ በሂደት እየጎለበተ መጥቷል፡፡ እነዚህ ሁለት አብነቶች መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካል ኢኮኖሚው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው እንድንገነዘብ የሚያደርጉን ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙሃንን የአሰራር ፍልስፍና የሚያመላክቱ ሁለት አስተሳሰቦች ይስተዋላሉ፡፡ የእነዚህ አስተሳሰብ ምንጭ ደግሞ ፖለቲካል- ኢኮኖሚው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የመጀመሪያው አስተሳሰብ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞነት ሙያ ዋነኛ ተግባር ዜጎች በነጻነት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ የሚያስችል መረጃ ማቅረብ ነው የሚል የሊበራል ፖለቲካ ኢኮኖሚ አቀንቃኞች አቋም ነው፡፡ ይህም መገናኛ ብዙሃንን ከፖለቲካል- ኢኮኖሚው የተለየ ህልውና እንዳላቸው የማስመሰል ጥረት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እሳቤው የመገናኛ ብዙሃኑ ተግባር የዜጎችን መብት በማስከበር ብቻ የተወሰነ ሊሆን ይገባል የሚል ምልከታ ውጤት ስለሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዜጎች በመገናኛ ብዙሃኑ በየዕለቱ የሚያገኙት መረጃ እነርሱ የሚፈልጉትና በተግባርም ለነጻነታቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት የሚያስችል መረጃ ማቅረብ አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ በጥቅሉ ሲታይ መገናኛ ብዙሃን ተግባርና ሚና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፖለቲካል- ኢኮኖሚው ነፀብራቅ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህም ባሻገር መገናኛ ብዙሃኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚው የበላይ አካል የሚቆጣጠራቸው በመሆናቸው በኢኮኖሚ የበላይነትና በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዕልና መካከል ያለው ቀጥተኛ ትስስር የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካል- ኢኮኖሚው ግንኙነትም ጠንካራ ትስስር ያለው ይሆናል፡፡ የኒዮ- ሊበራል ሥርዓት የዘረጉ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ንብረትነታቸው የግሉ ባለሀብት በመሆኑ፤ ተቋማቱ በመረጃ ሽያጭ የሚተዳደሩና እንደ ንግድ ተቋማት የሚታዩ ናቸው፡፡ ተግባራቸውና የአሰራር ፍልስፍናቸው የመንግስትን የሥራ ሂደት መቆጣጠር ብቻ ነው፡፡

ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን የተቀናጀ ባለቤትነት ሞዴል በመከተል በህዝብ፣ በግልና በማህበረሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የመኖር አስፈላጊነትን አቋም የሚገልጹ ወገኖች ምልከታ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የዜጎች የመረጃ ልውውጥና የክርክር መድረክነት የሚያገለግል፣ በህዝብና በመንግስታት እንዲሁም በንግድ ተቋማት መካከል ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ በዕውቀት ላይ በተመሰረተ የሃሳብ ክርክር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማጎልበት መሆን ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ የህዝቡ ባህል፣ ልምድና እሴት መገለጫና ማሳደጊያ መድረክ የሆነ፣ የመንግስት ሥራን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚያሳድግ፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን የሚያጋልጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠንና ውጤታማነቱን ማረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና መሆን እንዳለበትም ያስረዳል፡፡

ታዲያ ይህ እሳቤ የመገናኛ ብዙሃን የልማት አቅጣጫዎች መገናኛ ብዙሃን በባለቤትነትም ሆነ በሚያቀርቡት የመረጃ ይዘት ብዝሃነትን ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው የሚያመላክት አቅጣጫ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም ከዚህ ሃቅ የምንረዳው ነገር ቢኖር መገናኛ ብዙሃን የህዝቡ ልሳን መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህም የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን በተለይም ተጠሪነታቸው ለአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ጥቅም መስራት እንዳለባቸው የሚያሳየን ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን መንግስት የልማታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓትን በመከተል ላይ የሚገኝና ለተከታታይ 15 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ውጤታማነቱን ማስመስከር የቻለ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከነበረችበት የድህነትና የኋላቀርነት አረንቋ ለማውጣት የተከተለው የልማታዊ አስተሳሰብና ፍልስፍና የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አማራጭን ለመከተል ያካሄደው ጥረት ውጤት መሆኑ አይታበይም፡፡ ይህ ደግሞ ማጠንጠኛው የህዝብ ጥቅም ነው፡፡ እናም መገናኛ ብዙሃኑ በሙያ ተክነው የህዝብን ጥቅም ተቀዳሚ ሊያደርጉ ይገባል፡፡  በተለይም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የህዝቡን ድምፅ ሳያሰሙ በራሳቸው ፍላጎት ውስጥ የሚዳክሩ፡፡ ከሆነ እዚህ አገር ውስጥ በድህነት ላይ የተጀመረን ህዝባዊ ዘመቻን ሊደግፉ አይችሉም፡፡ ህዝቡ አምኖ እውን እንዲሆን ያደረገውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማገዝ ይከብዳቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው የየትኛውም ሀገር ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ልማትን ማፋጠንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባት አቅጣጫን የሚከተል ነው፡፡ ለዚህም ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህ እውነታም በዘፈቀደና በአሉባልታ  እንደሚወራው ሳይሆን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታት ለፕሬስ ነፃነትን ያላቸው ቦታ ከፍተኛ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፤ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት የሚከተል፣ የመገናኛ ብዙሃኑ ሚና ደግሞ ለልማቱ መፋጠንና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ዕድልን መፍጠር ችሏል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ የሚጠበቅባቸውን የህዝብ አገልጋይነት ሚናን በተገቢው መንገድ ባይወጡም፡፡

እንደሚታወቀው በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ የፕሬስ ነፃነትን አስመልክቶ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል፤ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል የሚል ግልፅ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከምትከተለው የፈጣን ልማትን የማረጋገጥ ጥረትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መፋጠን የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ነው፡፡ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ልማትን ማረጋገጥ አገራዊ ህልውናን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዘመናት የህዝብ ጥያቄ የሆነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማፋጠንም ከልማቱ ጋር አብሮ የሚታይ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የአገራችን የመገናኛ ብዙሃን ሚናና የአሰራር ፍልስፍና ከነባራዊው አገራዊ የለውጥ ፍላጎታችንና በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት የመገንባት ዓላማ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ለማሳካት ድርሻቸው ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ዛሬ በከፍተኛ ዕድገት ላይ የሚገኙ የኤሺያና የላቲን አሜሪካ ሀገሮች ለውጥ በማስመዝገብ ረገድ የቀረፁት የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ሚና አስተዋጽኦ የላቀ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የእነዚህ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን በመንግስት፣ በህዝብና በግል ባለቤትነት ስር ቢሆንም ሚናቸው ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የመገናኛ ብዙሃኑ ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን የማሳካት አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት የበኩላቸውን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳን የሊበራል ሥርዓቶች የመገናኛ ብዙሃን እንደ አራተኛው የመንግስት አካል ተደርገው የሚታዩ ቢሆኑም፤ በእኔ እምነት ግን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ጠቃሚ ነው ብሎ ለመቀበል ይቸግረኛል። ምክንያቱም ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ዕውነታዎች በመነሳት መገናኛ ብዙሃን የስርዓቱ ነፀብራቅ እንጂ አራተኛው የመንግስት አካል ተደርገው መወሰድ ይገባቸዋል ብዬ ስለማላምን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን ከምትከተለው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር ተያይዞ የመገናኛ ብዙሃን የተቀናጀ ባለቤትነት ሞዴል በመከተል፤ በህዝብ፣ በግልና በማህበረሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን የሶስቱ የመንግስት አካላት ደጋፊዎች እንጂ ውሳኔ ሰጪ ሆነው እንዲደራጁ ስላልተደረገ ነው፡፡

እናም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ በተቀመጡት መሰረታዊ ድንጋጌዎች መሰረት መገናኛ ብዙሃን ተግባራቸውን በሚገባ መወጣት ያለባቸው ይመስለኛል። የስርዓቱ ነፀብራቅ በመሆን ህዝቡ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትንና ህዝቡ ህዳሴውን ለማሳለጥ እያከናወናቸው የሚገኘውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን በማሳለጥ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ይህን ተግባር እንዲወጡ በመንግሥት ተደራጅተው ተጠሪነታቸው ለገለልተኛ አካል የሆኑ የብዙሃን መገናኛዎች ባለሙያቸው በሙያቸው እንዲደረጁ፣ ካላስፈላጊ ውሰጣዊ አተካራ እንሲወጡ፣ መጎልበት የሚገባቸውን አገራዊ ጉዳዩችን እንዲያበረታቱ፣ ችግሮችን በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘው እንዲያጋልጡ ልሳነ- ህዝብ መሆን የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። በህዝብ ተቋቁመው ለህዝብ ልሳን መሆን የማይችሉ የብዙሃን መገናኛ ታርመው ወደ ህዝብ አገልጋይነታቸው ጎራ ሊቀላቀሉ ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን ከመገናኛ ብዙሃኑ ጋር ቀጥተኛና የጎንዮሽ ግንኙነት ያላቸው አካላት እንዲሁም ሙያውን ለማገዝ የተቋቋሙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አገር በቀል የትምህርትና የምርምር ተቋማት ብሎም ሌሎች አካላት ድጋፍ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።