Artcles

መፈናጠሪያ ገበታ ላይ ወጥተናል

By Admin

May 06, 2017

መፈናጠሪያ ገበታ ላይ ወጥተናል/ብ. ነጋሽ/

የተባበሩት መንግስታት የሰበአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል። የዋና ኮሚሽነሩ ጉብኝት በኢትዮጵያ መንግስት በቀረበ ጥያቄ የተከናወነ ነው። ዓላማውም ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ መገንዘብ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ነው። ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር፣ ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳና ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረዋል።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን ከዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያና በመንግስታቱ ድርጅት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።  ኮሚሽነር ዘይድ ራድ ሃሰን ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚያከናውነው የሠብዓዊ መብት ጥበቃ  አንዷ አጋር መሆኗን ገልጸዋል።  የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን መስራች እንደመሆኗ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ዓለም አቀፍ ህጎች ተቀብላ እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ጋር በነበራቸውም ቆይታ፣ በሰብዓዊ መብቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች አከባበር፤ በተቋማት ግንባታና ማጠናከር ዙሪያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን  ጋር በጋራ የምታከናውናቸው ተግባራት አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ገልጸዋል። በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ፣ በተቋማት ግንባታና ጥንካሬን የተመለከቱ ዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ከአፈ ጉባኤ አባዱላ ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በምን አይነት መነገድ እንደሚያከናውን ጠይቀዋል። አፈ ጉባዔ አባዱላም የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ በምክር ቤቱ ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቶት በተቀናጀ መንገድ የሚተገበር ዓብይ አጀንዳ መሆኑን ገልጸውላቸዋል። ምክር ቤቱ ለዜጎች ህይወት መሻሻል፣ ህገመንግስታዊ መብት መረጋገጥና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎችን ማሟላት የሚያስችል የአሰራርና የክትትል ስርዓት መዘርጋቱንም አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት የዜጎች በሠላም የመኖር መብት እንዳይጣስ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሠላም ማስፈን መቻሉንም ገልጸዋል። አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ባለችበት ጊዜም የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ምክር ቤቱ በየጊዜው  በመገምገም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰድ ማድረጉንም ገልጸዋል።  

የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጋር ተወያይተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት ጉዳዮች ጉድለቶች መኖራቸውን ገልጸውላቸዋል። የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለሠብዓዊ መብት ትልቅ ሥፍራ መስጠቱን የገለጹት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ ሆኖም አተገባበር ላይ የሚታዩ ጉድለቶች የሠብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያን ሠብዓዊ መብት ኮሚሽንን አቅምና ገለልተኝነት ለማጠናከር ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ኮሚሽነር ዘይድ ራድ በበኩላቸው የሚስተዋሉት ችግሮች የሚፈቱት በኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልፀዋል።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሶስት ቀናት ጉብኝት ማጠናቀቂያ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና  መረጋጋት እንዲሁም ለስደተኞች የምታደርገውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር ማካሄድ የጀመረውን ውይይት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል። የበጎ አድራጎትና የጸረ ሽብርተኝነት አዋጆች የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን እንዳይውሉ ጥንቃቄ መድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ አንዳንድ አከባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ሊበረታታ የሚገባው መሆኑንም ገልጸዋል። የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኢትዮጵያ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ተግባራዊ ለማደረግ በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የሁለተኛው የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀግብር ስኬታማነት ድጋፍ  እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን በኢትዮጵያ ተገኝተው በተለይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ከመንግስት ውጭ ባሉ አካላት ዘንድ ያለውን እይታ መገንዘብ ያስችላቸዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረማርያም፣ ከኢፌዴሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገማዳ ጋር ያደረጉት ውይይት ደግሞ መንግስት ህገመንግስቱን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነትና በዚህ ሂደት የሚገጥሙትን ፈተኛዎች ምንነትና ምንጭ መረዳት ያስችላቸዋል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ የተለያየ ፍላጎትና አተያይ ያላቸው አካላት ያላቸውን አቋም ሚዛናዊ በሆነ አኳኋን መመልከት ያስችላቸዋል ተብሎ ይገመታል።

እንዳጋጣሚ ሆኖ ዋና ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አልዊ  ሁሴን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሁለተኛው የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር በይፋ ስራ ላይ በዋል በጀመረበት ሰሞን መሆኑም ስለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች ያላቸውን እይታ ሚዛናዊ ሊያደርገው ይችላል።

የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብሩ መሰታዊ ሰብአዊ መብቶችን፣ ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶችን፣  የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መብቶችን አካቶ የያዘ ሰነድ ነው። ሰነዱ የእያንዳንዱ መብት አጠባባቅ ሳይሸራረፍና ሳይዘለል ተግባራዊ መሆን እንዲችል ለሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ተጨባጭ ሃላፊነቶችን ዘርዝሮ ይሰጣል። የአፈጻጸም ችግር ሲኖር ድክመት የታየበትን አካል ለይቶ ማወቅና ተጠያቂ ማድረግ፣ የአፈጻጻም ችግሮችን በመለየት ተግባራዊ የሚሆነበትን አቅም ማጠናከር ያስችላል። ይህም በሂደት አጠቃላይ የሃገሪቱን ሰብአዊ መብት አያያዝ ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ያግዛል።

የድርጊት መርሃ ግብሩ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን ምንነት በስፋትና በጥልቀት መረዳት ያስችላል። በተደጋጋሚ በተጨባጭ እንደታየው ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ነን በሚሉ አካላት የሚነሳው ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ዴሞክራሲ በሀዝቡም፣ በመንግስትም፣ በተቃዋሚ የፖሊካ ፓርቲዎችና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት ላይ በሚመጣ የአመለካከት ለውጥ የሚገነባና ምሉዕ ለመሆን ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በተለይ ጅምር በሆነበት ደረጃ ላይ ችግሮች ይታዩበታል። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሃገራት የሚያጋጥም ነው። እናም የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ከዴሞክራሲው እድገት ጋር ምሉዕ እየሆኑ ከሚሄዱት ከዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች አኳያ ብቻ በመመልከት የተዛባ እይታ የፈጠረበት ሁኔታ አለ። የድርጊት መርሃ ግብሩ ይህን የተዛባ እይታም ያስተካክላል። የድርጊት መርሃ ግብሩ ይፋ በተደረገበት ስርአት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርረያም ባደረጉት ንግግር ይህን በግልጽ አስቀምጠውታል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስት የድርጊት መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው የተለመደ አሰራር ስለሆነ ወይም የለጋሽ ድርጅቶችን ቀልብ ለማማለል አይደለም። ሰነዱ የተዘጋጀው የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጉዳይ የሃገሪቱ ህልውና መሰረቶች መሆናቸውን በአግባቡ በመገንዘብ፣ ከልብ በመቀበልና በማመን ነው ብለዋል። አያይዘውም የሰብአዊ መብት አያያዛችንም ሆነ የዴሞክራሲ ስርአታችን ታዳጊና በሽግግር ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ፣ ልማታችንንና ሰላማችንን የማይፈልጉ ወገኖች በሚሉት ልክና መጠንም ባይሆን ጉድለቶች አሉበት ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዴሞክራሲ ስርዓት እየዳበረ እንዲሄድና ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ለማድረግ መንግስት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው፣ ሆኖም ግን አሁንም ገና በጅምር ደረጃ ላይ የሚገኘው የሃገሪቱ የዴሞክራሲ ስርአት ከጉድለት የፀዳ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በህግ አስከባሪዎች የግንዛቤ እጥረትና የብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን እንዲሁም ከሌሎች ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ጋር የተያያዙ የዴሞክራሲያዊ ነጻነቶችንና የሰብአዊ መብቶቸን በማስከበርና በማክበር ሂደት ላይ ችግሮች እድሚታዩም አስታውቀዋል። ይህንን መንግስት ራሱ በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ተመልክቶ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን መቀበሉን፣ ይህንን ለማቃለል በመስራት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል። የሁለተኛው የብሄራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብርም የሰብአዊ መብቶች አያያዞችና የዴሞክራሲ ስርዓትን በተቀናጀ መልኩ በተለያዩ ተቋማት ለመተግበር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሁለተኛው የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ትግበራ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፐሮግራም (ቪኦኤ) ያነጋገራቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢተዮጵያ ዋና አስተባባሪ፣ የተመድ የልማት ፕሮግራም እንዲሁም የሰብአዊ ጉዳዮች ዋና ተጠሪ ሚ/ሥ አሁና ኢዛኩ አዛኩኑዋ አኑቺ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ ማብበራሪያ ሰጥተዋል። ሴተየዋ በሰጡት አሰተያየት “ስለሰብአዊ መብቶች ስንነጋገር ስለማይነጣጠሉ ሁሉን አቀፍ መብቶች የምንነጋገር መሆኑን ማስተዋል አለብን። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መበቶች ረገድ መልካም ውጤቶች አስመዝግባለች። የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡ ለዘለኣለም ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት ከፍተኛ ሃብት አፍስሶ ያገኘው ውጤት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከቀዳሚ ሃገራት አንዱ ያደርጋታል። ኢትዮጵያ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ካሳኩ ሃገራት አንዷ መሆኗን ስንናገር በኩራት ነው። ወደፖለቲካዊና የዜግነት መብቶች ስንመለስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም እንደገለጹት ፈተናዎች አሉ። ፖለቲካዊ መደረኩን ለተሳትፎ ክፍት ማድረግ፣ የፖለቲካ ባህሉን ማጥለቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ገና በማደግ ላይ የሚገኝ ህጻን ነው። በለውጥ ሂደት ላይ ነው የሚገኘው ብለዋል።

እነዚህ ከላይ የተገለጹ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ በተለያየ አካላት የተገለጹ እውነታዎች የሃገሪቱ አጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ መልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ በዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ግን አሁንም ክፍተት መኖሩንና ክፍተቱም ዴሞክራሲው ለጋ ከመሆኑ የመነጨ መሆኑን ያመለክታሉ። መንግስት በተለይ በቅርቡ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጋር የጀመረው ውይይት ክፍተት የሚታይበትን የዴሞክራሲ መብት በተማላ ሁኔታ የሚከበርበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያለው ፍላጎት ቁርጠኝነት ያሳያል። እናም በዚህ ረገድ በቅርቡ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የገመታል።

የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ ለኢትዮጵያ የአንድ ሰሞን ጉዳይ አይደለም። በህገመንግስት ላይ የሰፈረ ጉዳይ ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንድ ሶስተኛ መሰረታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና ነጻነቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው። እነዚህ ድንጋጌዎች በህገመንግስቱ ምዕራፍ 3 ክፍል 1 እና ሁለት ላይ ከአንቀጽ 14 እስከ 44 በሰፈሩት ድንጋጌዎች የተገለጹ ናቸው። ኢትዮጵያ የፈረመችባቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በህገመንግስቱ ላይ ከሰፈሩት የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መልክ መከበር እንዳለባቸው ህገመንግስቱ ይደነግጋል። ህገመንግስቱ የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን አፈጻጸምና አተረጓጎም በሚመለከተው አንቀጽ 13 ላይ፤

 

 

ተብሎ ተደንግጓል።

ሰሞኑን ወደትግብራ ምዕራፍ የገባው ሁለተኛው የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር በህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩ ሰብአዊ መበቶች፣ ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች እንዲሁም የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት መብቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ተግባራዊ የሚሆኑበት መሳሪያ ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት መብቶችን በማረጋጋጥ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊጠቀሰ የሚችል ድንቅ ስኬት አስመዝግባለች። የብሄር ብሄረሰቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰንና ተያያዥ ፖለቲካዊ ነጻነቶችን በማረጋጋጥ ረገድም ድንቅ ውጤት ተመዝግቧል። እርግጥ አንዳንድ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችንና ዴሞክራሲያዊ ነጻነቶች አከባበር ላይ ክፍተቶች ይታያሉ። ኢትዮጵያ አሁን እነዚህን ክፍተቶች ማስተካከል ወደሚያስችል ደረጃ የሚያሸጋግር መፈናጠሪያ ገበታ ላይ ትግኛለች። ሁለተኛውን የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብርና ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሲቪክ ማህበራት ጋር የተጀመረውን ድርድርና ውይይት ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ፤ በአማራና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቀስቅሶ ከነበረው ሁከት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በገለልተኛነት በመመርመር ይፋ የተደረገው ሪፖርትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።