Artcles

ሚዲያ እና ሽብርተኝነት

By Admin

May 23, 2017

ሚዲያ እና ሽብርተኝነት

ሰለሞን ሽፈራው

ዓለም አቀፋዊ የሽብርተኛነት እንቅስቃሴ በመገናኛ ብዙሃን የሙያ ዘርፍ ላይ የማይናቅ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥም ደግሞ ጉዳዩ እውነት እንዳለው በርካታ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ማስታወስ እይከብድም፡፡ ከዚህ አኳያ አብነት አድርገን ብናወሳው እውነታውን በተሻለ መልኩ ያሳያል የምለውም ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንድ ዓለም አቀፋዊ የሥርጭት ሽፋን እንዳለው በሚነገርለት የፈረንሳይ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ላይ አይ ኤስ የተባለው ሽብር ቡድን የፈፀመው እጅጉን አሰቃቂ ጥቃት ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም በፈረንሳውያኑ የአንድ በካርቶን ስዕል የተደገፈ ትችቶችን በማተም ዓለም አቀፍ ዝናን ስለማትረፉ በሚነገርለት ታዋቂ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አባላት ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት፤ እነርሱን ለመግደል ብቻ ስለተፈለገ ብቻ የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ አይታሰብምና ነው፡፡ ይልቅስ አሰቃቂው ግድያ ጽንፈኝነት የተጠናወተውን ሃማኖታዊ እሳቤ ለየራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሊያደርጉት ሲሞክሩ የሚስተዋሉትን አንደ አይ.ኤስ. ዓይነቶቹን የሽብር ቡድኖች የሚቃወም ጠንካራ ዜና መዘገብን ጨምሮ ዕኩይ ተግባራቸውን በማያሻማ መልኩ አምርረው የሚያወግዙ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ሁሉ “አጉል ድፍረታቸውን” እንዲያቆሙ ለማድረግ ሲባል የተወሰደ የመቀጣጫ እርምጃ ነው ተብሎ ይታመናል በፈረንሳውያኑ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አባላት ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ፡፡ እኔ ይህን የምለው ደግሞ በወቅቱ መላው የዓለማችን ማህበረሰብ አስረግጦ የተነጋገረበትና የጋራ ግንዛቤ የተወሰደበትም ጭምር ስለነበረ እንጂ እንዲያው ከራሴ መላምት በመነሳት ብቻ አይደለም፡፡

ለነገሩ ያን ያህል ሩቅ መሄድ ሳይጠበቅብን እዚሁ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ውስጥ ሽብርተኛው የአልሸባብ ቡድን እርሱን ተቃውመው የሚጽፉ የሚዲያ አውታሮች እንዳይኖሩ ለማድረግ ሲል በርካታ ሶማሊያውያን ጋዜጠኞችን ለአሰቃቂ ግድያና የአካል ጉዳት የዳረገበትን ተደጋጋሚ ጥቃት ማስተወስ ይበቃል፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ፈረንሳይ ውስጥ የተፈፀመውን የነጭ ጋዜጠኞች ግድያ ያህል ዓለም አቀፋዊ መነጋገሪያ የሆነበት አጋጣሚ ባይኖርም፤ በየወቅቱ የአልሸባብ ሽብርተኛ ቡድን አባላት ተመሳሳይ ጥቃት እየፈፀሙባቸው ለአሰቃቂ አማሟትና እንዲሁም ደግሞ ለፈርጀ ብዙ የአካል ጉዳት የተዳረጉ ሶማሊያውያን የሚዲያ ባለሙያዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላልና ነው እንደ አንድ የጎረቤት አገር ሰው ልመሰክር መሞከሬ፡፡

ለማንኛው ግን የዚህ መጣጥፍ ዋነኛ ዓላማ ለመሆኑ ከላይ ለመንደርደሪያ ያህል የተወሳውን ዓለም አቀፋዊ ርዕሰ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ አውነታ አምጥተን ለማየትብንሞክር የምናገኘው ምላሽ ምን ሊመስል ይችላል? በሚለው ነጥብ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብ ማንሳት ነው፡፡ ስለሆነም አሁን በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፌ የዘመናችንን ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ አንቅልፍ የነሳብርቱ የጋራ ደህንነት ስጋት እያስከተለ ያለው ሽብርተኝነት በኛ አገር የሚዲያ ሙያ ዘርፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ አጽዕኖ ለመመልከት የሚረዳ ትዝብቴን ለማቅረብ እሞክራለሁና አብረን እንቀጥል፡፡ ……

እንግዲያውስ ረቡእ ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “መንግስት የሚያስተላልፋቸውን መመሪያዎች ለኦ.ነ.ግ ያቀብል ነበር የተባለ የወረዳ ስራ አስፈፃሚ ተከሰሰ” በሚል ርዕስ የቀረበውን ዜና ለዚህ የዛሬው ፅሑፌ ማጠንጠኛ ለሆነው መሰረተ ሃሳብ ማዳበሪያነት የሚጠቅም ጉዳይ ሆኖ ስላገኘሁት እርሱን ነው በቅድሚያ የማነሳው፡፡ እናም ከሪፖርተር ጋዜጣ ዝርዝር ዘገባ መረዳት እንደሚቻለው አየለ በየነ የተባለ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የወረዳ 10 ስራ አስፈፃሚ የነበረ ግለሰብ ከሌሎች ሰባት ግብረ አበሮቹ ጋር በህቡዕ እየተመሳጠረ የመንግስትን ሚስጢሮች ለኦ.ነ.ግ ሊቀመንበር ለሽብርተኛው ዳውድ ኢብሳ የማቀበል ተግባር ሲፈጸም ተደርሶበት በሕግ ቁጥጥር ስር ከመዋሉም ባሻገር፤ ተከሳሹ የወረዳ ተሿሚ የሀገራችንን እውነተኛ ጋዜጠኖች የሽብር ቡድኖቹ “ዝም የሚያሰኝ እርምጃ እንዲወስዱባቸው” የሚያሳስብ ዝርዝር ሪፖርት እንዳቀረበም ጭምር የሚያረጋግጥ የጽሑፍ ማስረጃ ተገኝቶበታል፡፡

ከዚሁ የኦ.ህ.ዴ.ድ /ኢህአዴግን ማሊያ ለብሶ እንዲጫወት ሲባል ሽብርተኛው የኦ.ነ.ግ አመራር አካል አስርጎ ሳያስገባው እንዳልቀረ ከሚጠረጠር የወረዳ ስራ አስፈፃሚ ጋር “እጅና ጓንት” ሆነው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ተደርሶባቸው አብረውት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ የተከሰሱት ሌሎች ሰባት ግለሰቦችም ስማቸው በሪፖርተር ጋዜጣው ሰሞነኛ ዜና ላይ ተዘርዝሯል፡፡ በዚህ መሰረትም አቶ አየለ በየነን ጨምሮ መልካሙ ክንፈ፣ ቦንሳ በየነ፣ ይማም መሐመድ፣ ለሜሳ ግዛቸው፣ ኩመራ ጥላሁን፣ መያድ አያናና ሙሉ ዳርጌ የሚባሉ ግለሰቦች የኦ.ህ.ዴ.ድ /ኢህአዴግን ማሊያ ለብሰው ለሽብርተኛው ኦ.ነ.ግ ሲጫወቱ እንደነበር ተደርሶባቸው እንደተከሰሱ ነው ጋዜጣው በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ችሎት ፊት ተገኝቶ ከዘገበው ዜና የተረዳሁት ጉዳይ፡፡

እናም እነዚሁ የኦ.ነ.ግ ሰርጎ ገቦች ይልቁንም ደግሞ “የወረዳ ሥራ አስፈፃሚ” ተብየው ግለሰብ ስልጣኑን ተተግኖ የሚሰጣቸውን የሕጋዊነት ሽፋን እየተጠቀሙ ለሽብርተኛ ቡድኖች ይጠቅማል የሚሉትን የመንግስት ደካማ ጎን አነፍንፈው የሚለቃቅሙትን መረጃ ሁሉ ራሱ አቶ አየለ ባዘጋጀላቸው ሚስጢራዊ የኢሜይል አድራሻ አማካኝነት ለሽብር ቡድኑ ቁንጮ ለአቶ ዳውድ ኢብሳ ከመላክ ቦዝነው እንደማያውቁ ረቡዕ ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ከሳሽ አቃቤ ሕግን በምንጭነት ጠቅሶ የዘገበው ዜና ያትታል፡፡ በተለይም የወረዳ ስራ አስፈፃነትን መንግስታዊ ስልጣን የመጨበጥ ዕድል የገጠመው አቶ አየለ በየነ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ካቢኔ አባል መሆኑን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኦ.ነ.ግ ሽብርተኛ አመራር የሰጠውን ድብቅ ተልዕኮ ለማሳካት የሞከረበት አግባብ የሚዲያ ዘርፉ ላይ ያነጣጠረ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠርን እንደዋነኛ “የትግል ስልት” መወሰዱን የሚያረጋግጥ ነው ቢባል ትክክል ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም የወረዳ ስራ አስፈፃሚ የነበረው ግለሰብ “የኦ.ነ.ግን ዓላማ የሚያሰናክል ተጽዕኖ ፈጣሪ ዘገባ እያቀረቡ ስላስቸገሩን አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል” ከሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር ስም ዝርዝራቸውን ለሽብር ቡድኑ ቁንጮ ለአቶ ዳውድ ኢብሳ እንዲተላለፍ አድርጓል የተባለው በተለይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን እንደሆነ ዘገባው ያመለክታልና ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በሌሎች ሀገር ውስጥ ሚዲያ ተቋማት የሚሰራ ጋዜጠኛ ኦ.ነ.ግን አምርሮ የሚነቅፍ ተጽዕኖ ፈጣ ሃሳብ የማስተላለፍ አቅምና ድፍረት ያለው ሆኖ አስከተገኘ የሽብር ቡድኑ ጥቃት ኢላማ ከመሆን ያመልጣል ማለት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡

ይልቅስ ጉዳዩን ልብ ብሎ ላስተዋለው ሰው፤ በመላው የሀገራችን የመዝናኛ ብዘሃን ተቋማት ውስጥ ሰፍኖ የሚታየው የፍርሃት ስሜት ምንጩ እነ ኦ.ነ.ግ እና እነ ግንቦት ሰባት አስርገው የሚያሰርጓቸው ጀሌዎች እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ላይ መፍጠር የያዙት ስነ ልቦናዊ ሽብር ስለመሆኑ ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ደግሞስ ቡድኖቹ የኢፌድሪ መንግስት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆት ያተረፈበትን የጸረ ሽብርተኝነት ሕግ ህዝቡ እንዲቃወመው ለማድረግ ባለመ ሴራ ምን ያህል ያለ የሌለ አቅማቸውን አስተባብረው ሲረባረቡ እንደቆዩ ይዘነጋል እንዴ? እኔ በግሌ ጽንፈኛ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ሀገራችን ኢትዮጵያ ለምታካሄደው የፀረ ሽብር ትግል እንደሚሰጡት ግምት የሚያስገርመኝ ጉዳይ የለም ማለት እችላለሁ፡፡

እንኳንስ በትጥቅ ትግል ስም አስመራ ከከተሙ ዓመታትን ያስቆጠሩት የኦ.ነ.ግ እና የግንቦት ሰባት መሪዎች፤ አዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጠው ኢህአዴግን በመቃወም የሚታወቁት ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ መንግስትን ራሱን በአሸባሪነት ፈርጀው በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ጭምር ሲወነጅሉት የሚደመጡ ናቸው እኮ ወገኖቼ!? ለአብነት ያህልም ዶክተር መረራ ጉዲና የዛሬ ዓመት ገደማ ከአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ራሱ አሸባሪ ሆኖ ሳለ ሽብርተኝነትን ይታገላል ብሎ ማመን አላዋቂነት ነው” ሲሉ መደመጣቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡

ሌላው የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩም እንዲሁ አባል በነበሩበት የቀድሞው ፓርላማ መድረክ ፊት ተቀምጠው “የፀረ ሽብርተኛነት ሕጉ ራሱ ህዝብን የሚያሸብር ሆኖ ስለተገኘ ሊሰረዝ ይገባል” እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጣቸው የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ የግሉፕሬስ ሚዲያ ይህንኑ የጽንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቋም በመደገፍ የጸረ ሽብርተኝነት ሕጉን ተቀባይነት ለማሳጣት ያለመ ፕሮፓጋንዳዊ ዘመቻውን እንደጉድ አጧጡፎት እንደነበርም የሚካድ አይሆንም፡፡ እናም ከዚያ ሁሉ የጽንፈኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እነርሱ የሚቀርቡትን ውንጀላ ያለአንዳች ማጣራት እንደወረደ ተቀብለው በመደገፍ የሚታወቁት የግሉፕሬስ ሚዲያዎች የተቀናጀ የጸረ ሽብር ሕጉን አምርሮ የማጥላላት ዘመቻ በኋላም ነው፤ ሽብርተኝነት በሀገራችን የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ላይ ስነ ልቦናዊ ተጽዕኖውን ማሳደር መቻሉ መንጸባረቅ የጀመረው፡፡ አንዳንድ አድር ባይ የመንግስታዊ ሚዲያ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ፤ የዘርፉ ባለሙያ (ጋዜጠኛ) የተቃውሞው ጎራ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች “የጸረ ሽብር ሕጉ በሕወሃት የበላይነት የሚመራው የወያኔ ኢህአዴግ አገዛዝ በ1997ቱ ምርጫ ከመደንገጡ የተነሳ የሚፈራቸውን ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አፍኖ ለመያዝ ሲል ብቻ ያወጣው አንጂ ሽብርተኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያህልም አሳሳቢ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም” ሲሉ የሚያሰሙትን ቅሬታ አምኖ የተቀበለ የሚያስመስልበትን ወላዋይ አቋም የሚያሳይበት እውነታ ሰፍኖ መስተዋሉ የሚስተባበል ጉዳይ አይደለም፡፡

ስለዚህም እንደኔ እንደኔ፤  በተለምዶ “የመንግስት” ተብለው የሚጠሩትንና ግን ደግሞ ንብረትነታቸው የህዝቡ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ አጠቃላይ እውነታ በሚመጥን ሀገር አቀፋዊ ቅኝነት ላይ የተመሰረተ አስተማማኝ ቁመና እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ፤ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ካሉት ፈርጀ ብዙ ምክንያች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው፤ የሙያ ዘርፉ የስነልቦናዊ ሽበራ ሰለባ እንዲሆን የሚሹት ጽንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈጽሙት ስውር ተጽእኖ የሚፈጠርበት ደባ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ አስተያየቴ ተራ መላምት እንዳልሆነም ደግሞ፤ በተለይም ከላይ የተመለከተው የሽብርተኛው ኦ.ነ.ግ ጉዳይ አስፈፃሚዎች የኢህአዴግን ማሊያ በመልበስ ጭምር ሲጫወቱ የተገኙበት የክህደት ተግባር የተሻለ ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡

ይህን እንድል የሚያስገድደኝ ዋነኛ ምክንያትም፤ አንድ የወረዳ ስራ አስፈፃሚ ግለሰብ ከሰባት ግብረ አበሮቹ ጋር ተከሶ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ስለቀረበበት የአቃቤ ሕግ ዝርዝር ማስረጃ በሚያትተው የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና፤ ሌሎች በመንግስታዊ ተቋማትና እንዲሁም ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎችም፤ ሽብርተኛው የኦ.ነ.ግ ቡድን ህቡዕ እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው ህዋሶች ስር እየታቀፉ ስርዓቱን በተደራጀ መልኩ የማዳከም ተግባር እንዲፈጽሙ ከቡድኑ ቁንጮ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ የተላለፈ የጽሑፍ መመሪያ መገኘቱን አክሎ ያመለክታልና ነው፡፡ ስለሆነም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጨባጭ ድርጊታቸውን አገናዝቦ በሽብርተኝነት የፈረጃቸውን እንደ ኦ.ነ.ግ እና ግንት ሰባት ዓይነቶቹን ጽንፈኛ ቡድኖች በአመጽ ተግባር ወደ ስልጣን ለማምጣት ሲባል የሚፈጸም ፈርጀ ብዙ ደባ፤ በተለይም የሀገር ውስጡን ሚዲያ የስነ ልቦናዊ ሽበራ ሰለባ አድርጎታል ብለን ብናጠቃልል ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡

ስለዚህም አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ጎላ ባለ መልኩ እየተስተዋለ ያለውን ጋዜጠኝነትን እንደ አደገኛ የሙያ ዘርፍ የመቁጠር አዝማሚያ ከምን እንደሚመነጭ ለማወቅ ሲሞክር፤ የፈረደበትን መንግስት ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከላይ ለአብነት ያህል የተወሳውን ዓይነት የሽብር ቡድኖች ስውር ተጽእኖም ግምት ውስጥ ማስገባት መቻል ፍርዳችንን ሚዛናዊ ያደርገዋል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ አኳያ የሚስተዋለውን የዘርፉ ውስብስብ ችግር ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት መርምሮ የመፍታት አስፈላጊነት ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ሀገራዊ የጋራ መግባባትን የሚጠይቅ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው የሚለው ቁልፍ ነጥብ ላይ አስምሬበት እነሆ ለዛሬ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ መዓሰላማት!