Artcles

ሥርዓቱ የፈጠረው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት

By Admin

May 23, 2017

ሥርዓቱ የፈጠረው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት

                               ዳዊት ምትኩ

ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ከሀገሪቱ ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ ሆነዋል። በእነዚህ ጊዜያት በርካታ ፍሬያማ ውጤቶችን ተቋድሰዋል። ውጤቶቹም በሁሉም መስኮች በክልሎች ውስጥ ተመጣጣኝ ዕድገት መፍጠር የቻሉና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው። ለዚህ የተጠቃሚነት አዲስ ምዕራፍ መከፈት ትልቁ መሰረት መንግስትና ገዥው ፓርቲ የተከተሏቸው ሁሉን አቀፍ መንገዶች፣ በተለይም በህገ መንግስት ላይ ህዝባዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ድንጋጌዎች እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ ሰነዶች መሆናቸው ግልፅ ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ከመሆኑ ሌላ በህገ መንግሥቱ ውስጥ በሰፈሩት ድንጋጌዎች ላይ አገራዊ መግባባቱ እየዳበረ መምጣት፣ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ አስችሏታል።

ህገ መንግሥቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የመቀየስ ኃላፊነት ወድቆበታል።

በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትም እንዲሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል። በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል። ትናንት ከ500 ሺህ ብር በላይ ሃብት እንዳይዝ ገደብ ተጥሎበት የነበረ ኢትዮጵያዊ፤ ዛሬ ላይ የሚሊዮኖች ጌታ እንዲሆን አስችሎታል። ሚሊዮኖችን የባለ ሚሊዮንነት ራዕይን እንዲሰንቁ አድርጓል።

ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። ይህም በመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል። በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝ}ቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል።

በዚህ መሠረትም የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል።

የግንቦት ትሩፋቶች የሆኑት የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው። የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።

የክልሎችን እኩል የመልማት እድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወሳኝ መሆኑን የህገ መንግሥቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ህገ መንግሥቱ ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል። የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑ ተደንግጓል።

እንደሚታወቀው የልማት አጀንዳ ለአገራችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ “የሞት ሽረት” ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ርብርብ እያደረገ ነው። ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን በመንደፍ “የሞት ሽረቱን” ጉዳይ ወደ መሬት አውርዶ እየሰራ ነው።

በዚህም አብዛኛውን ህዝብ መሰረት ያደረገ ዕቅድ ነድፎ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ላይ ይገኛል። በሀገራችን በተዘረጋውና በተመረጡ ጉዳዩች የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓትም፤ የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ አገሪቱን ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጎ እየሰራ ነው።

ገበያ መሩን የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ተከትሎ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሥራ ሥምሪት ፖሊሲዎች ተነድፈው በሥራ ላይ ውለው ውጤት እያስገኙ ነው። እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የሚያሳዩ የውጭ ባለሃብቶች በምን ዓይነት የስኬት መንገድ ላይ እየተረማመድን መሆኑን ጠቋሚዎች ይመስሉኛል።

እርግጥ በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ ውስጥ የመንግሥት ዋና ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት ነው። መሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሃብት ልማት ማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ዕውን ሆነዋል። በአንፃሩም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ተግባራትን እንዲከናወኑ እየተደረጉ ነው።

እርግጥ ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት፤ ፈጣን፣ ዘላቂና ሰፊ መሠረት ያለው እድገት የማምጣት አቅም የሌለውና ብቻ አይደለም። ከዚህ በላይ የህዝብና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ጎራ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግ ይታመናል። እናም በልማቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮት ለመፍታት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው። በምጣኔ ሃብት ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ ህዝቡ እንደመሆኑ መጠን፤ የሚደረገው የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ውጤት ማምጣቱ አይቀርም። ምክንያቱም ህዝብ የተሳተፈበት ማንኛውም ጉዳይ ከግብ ይደርሳል። በዚህም በቀጣዩቹ ጊዜያት ካለፉት 26 ዓመታት በላይ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ሥር የታቀፈው ሁሉም የሀገራችን ህዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱ መዳበሩ አይቀርም።