Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ራዕይ 2020››

0 436

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹ራዕይ 2020››

/ስሜነህ /በበጀት  አመቱ  ዘጠኝ   ወራት    ከቡና ፣ከቅመማ ቅመምና   ከሻይ  ቅጠል  ምርቶች  148 ሺ 227 ነጥብ  2  ቶን ተልኮ  560 ሚሊዮን  ዶላር  ማግኘት  መቻሉን  የኢትዮጵያ   ቡናና  ሻይ  ልማትና   ግብይት   ባለስልጣን ሰሞኑን አስታውቆ ነበር፡፡  ባለስልጣኑ  17 ሺ 354 ነጥብ 72  ቶን  በመላክ  649 ሚሊየን   ዶላር  ለማግኝት አቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ካቀደው  በመጠን 85.55  በመቶው ከገቢ ደግሞ 86.3 በመቶውን  ማሳካት  ችሏል፡፡ አፈጻጸሙ   ከባለፈው  አመት   ተመሳሳይ  ወቅት   ጋር   ሲነጻጸር   በመጠን  4.5%  በገቢ 15%  ጭማሪ   ማሳየቱም  ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ  ቡና  መዳረሻ  ሀገራት  59  ሲሆኑ   ሳውዳአረቢያ 17.72 % ጀርመን  17.41፣ ጃፓን 10.25፣  ቤልጂየም 8.44%ና አሜሪካ 7.62%  በመያዝ  ቀዳሚውን  ቦታ  የያዙ ናቸው፡፡ ይህን መነሻ አድርገን የሃገራችንን የወጪ ንግድ አፈጻጸምና ተግዳሮቶች እንቅስቃሴዎች ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንጻር እንፈትሽ።

ንግድ በአንድ ሃገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ስትራቴጂው እንደ አገራችን ባሉ ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በመናድ በምትኩ የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን መገንባት ታሳቢ ያደረገ ነው። የሚቀየሰው ስትራቴጂ በአገሪቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችልና ህዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆን እንዳለበት ታምኖበት ተግባራዊ ተደርጓል። በተጨማሪም በከተሞች ለዴሞክራሲ ማበብ የሚበጅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታን የሚፈጥር መሆን ያለበት መሆኑን በማመን  በሁለቱም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተለፋ ነው።

በሀገራችን የንግድ ሥራ አጀማመር የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ቢሆንም ንግድ እንደ ሙያ ሥራ ተቆጥሮ በህግ እንዲመራ የተደረገው በ1952 ዓ.ም የወጣውን የንግድ ህግ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላም ቢሆን ዘርፉ ትኩረት ባለማግኘቱ እና የደርግ መንግሥትም በዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረጉ ምክንያት የሸቀጦች ነፃ ዝውውርና የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴም በካፒታል ጣሪያ ተገድበው በመቆየታቸው የንግድ ዘርፍ በውድድር ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ ሚናውን በተገቢው መጫወት የተሳነው ዘርፍ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ኢህአዴግ ሃገሪቱን መምራት ከጀመረበትና ከሽግግር መንግሥት ምሥረታ ማግስት ጀምሮ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ  ተደርጓል፡፡ ገበያው በፍላጎትና በአቅርቦት የሚመራ እና የሸቀጦች ዝውውርና የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴም በካፒታል ጣሪያ ያለመገደባቸው ፣ ልዩ ትኩረት የማይሹ የመንግስት የልማት ድርጀቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዞር  እና ሃገራዊ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ ኢኮኖሚያችንን ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለማስተሳሰር የተወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም ኋላ ቀር አሠራሮችን በማሻሻል የተቀላጠፈና ውጤታማ አገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ፈጣንና ቀጣይነትያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብና ህዝቡንም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን አስቸሏል፡፡

 

የግሉ ዘርፍ የኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈሩ ተደርጓል፡፡ በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ የመወዳደር አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች በመደረጋቸው በርካታ አስመጪዎችና ላኪዎች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ሀብት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ ለልማቱ የሚያስፈልገውን ሀብት በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት አስችሏል፡፡  

የንግድ አሠራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሸቀጦችና የጉልበት ነፃ ዝውውር እንዲኖርና የሸቀጦች ዋጋ በአቅርቦትና ፍላጎት ህግጋት መሠረት በውድድር እንዲመራ በመደረጉና የመንግስት ሚናም ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ በርካታ ለውጦች እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የገበያ ጉደለት በሚያጋጥምበት ወቅት በተመረጠ አግባብ እና ለተወሰኑ ጊዜያት በመግባት ጉድለቶችን የመሙላት ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ መሰረታዊ ሸቀጦችን በድጎማ ለህብረተሰቡ በማቅረብና በማሰራጨት እንዲሁም በጅምላ ንግድ ስርአቱ ውስጥ የሚታየውን የገበያ ክፍተት ለመሸፈን የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅት ወይም አለ በጅምላን በማቋቋም ዋጋን በማረጋገት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

 

የንግድ ግንኙትንና ድርድርን በማጠናከር ገበያ በማፈላለግ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት፤ የሥራ ማስኬጃ ችግርን ለማቃለል የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፤ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ፤ የቫውቸር ሥርዓት የመዘርጋት፣ የማይቀረጥ የዕቃ ማከማቻ መጋዘንና የተመላሽ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓቶች መተግበር፤ የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል እቃዎችና ግብአቶች ያለቅድመ ሁኔታ የሚገቡበትን መንገድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መሬት  የሚያገኙበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም የወጪ ንግድ ዘርፉ ወጥ በሆነ አቋም ላይ የማይገኝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በማሽቆልቆል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን እዚህ ጋር በማያያዝ እንመልከት።

በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ሳይል ቀርቷል፡፡ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በሰባት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በጠቅላላው 1.423 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ግን በሰባት ወራት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ከታቀደውም ሆነ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው።  

በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት 2.488 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም የተመዘገበው 1.423 (57.19 በመቶ) ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል፤ የሚለው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፣ በተያዘው ዕቅድ አኳያ የ50 በመቶ በታች ቅናሽ ካስመዘገቡት የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ዓሣ፣ ሰም፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ፣ ወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ የሥጋ ተረፈ ምርትና ብረታ ብረትም ከግማሽ በላይ ቅናሽ ያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ዋና ዋና ከሚባሉት የወጪ ንግድ ሸቀጦች መካከል ቡና ቀዳሚው ነው፡፡ በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 360.8 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ይጠበቅ ከነበረው የገቢ መጠን አኳያ ማከናወን የተቻለው ከዕቅዱ 4.2 በመቶ ብቻ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከታየው ይልቅ ዘንድሮ የ14.67 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ጭማሪ ቢመዘገብም፣ በመጠን ግን ለአራት ሺሕ ቶን የቀረበ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡ዘንድሮ ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን 96.6 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ዓምና በሰባት ወራት ውስጥ የቀረበው የቡና መጠን ግን ከ100 ሺሕ ቶን በላይ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡

‹‹በዚህ ወርና በአጠቃላይ በሰባት ወራት በመጠንና በገቢ የቀነሰበት ምክንያት በቡና አብቃይ ክልሎች በቂ የቡና ምርት እንዳለ ቢታወቅም፣ ይህንን ሁኔታ ገዢዎች በመረዳት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋጋ በታች እየሸጡ በመሆኑ በዋጋ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቂ ኮንትራት አልተገባም፣ ገዢዎች ምክንያት እየፈጠሩ የሚላክላቸውን ናሙና ውድቅ በማድረግ L/C ከፍቶ ለመላክ በማዘግየታቸው ነው፤›› በማለት ቡና የታሰበውን ያህል ውጤታማ ያልሆነው የውጭ ገዢዎች የሚሰጡት ዋጋ ከአገር ውስጥ የምርት ገበያ ዋጋ አንሶ መገኘቱ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየወጡ እንደሚገኙ ከተገለጹ ምርቶች መካከል ወርቅ ይገኝበታል፡፡ የወርቅ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከመኖሩ ባሻገር ዘመናዊ አምራቾችም ቢሆኑ በዕቅዳቸው መሠረት አከታትለው መላክ ባለመቻላቸው ምክንያት ዝቅተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደቻለ ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከወርቅ ይጠበቅ ከነበረው ገቢ የ26 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ የ111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተመዝግቧል፡፡

የወጪ ንግዱ ዘርፍ እንዲህ ባለው ደረጃ እየተንሸራተተ መምጣቱ አገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት እያባባሰው መምጣቱን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚጠቅሰው፣ አገሪቱ የከረንት አካውንት ጉድለት 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) የ10 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት በአማካይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ዓምና የነበረው የንግድ ሚዛን ጉድለት ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም የንግድ አሠራር መለኪዎችን ለማሻሻል የዓለም ባንክ ሞዴል ያደረጋትን ሩዋንዳ ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል።

ከሚያዝያ 19 ቀን እስከ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በዘለቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሩዋንዳ ጉብኝት ወቅት  ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው የገለጹበት መስክ አንዱ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በተለይ በንግድ አሠራር ሒደት የሚታዩ እንቅፋቶችን በመቀነስ፣ የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ለንግድና ኢንቨስትመንት ቀልጣፋ አሠራርን በሚለካው ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራም መተግበር መጀመሯን አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የንግድ አሠራር ሪፎርም ሩዋንዳን ተምሳሌት እንደምታደርግም ማሳወቃቸው የተሻለ ተሞክሮ ስላላት ነው፡፡ በአፍሪካ እያስመዘገበች ከምትገኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ባላት ምቹነት ሩዋንዳ በዓለም ባንክ መለኪያ ጥሩ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ የሩዋንዳን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መስህብ እንዲኖራት ለማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሪፎርም ሥራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ሩዋንዳን ውጤታማ ካደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመማር መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ማረጋገጣቸው ተገቢ ነው፡፡

የዓለም ባንክ በዋና ዋና መመዘኛ መስፈርትነት የሚጠቅሳቸው የሚከተሉት አሥር መለኪያዎች ናቸው፡፡ የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ የግንባታ ፈቃድ በቀላሉ ለማግኘት መቻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት፣ ንብረት ማስመዝገብ፣ ብድር በቀላሉ ማግኘት መቻል፣ ለአነስተኛ ኢንቨስተሮች ከለላ መስጠት፣ ታክስ መክፈል፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማካሄድ፣ የውል ስምምነቶችን መተግበር እንዲሁም የኪሳራ እወጃን ያለ ውጣ ውረድ መፍታት የሚሉት ዋና ዋና መለኪያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ 190 ያህል አገሮች በማካተት ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ በአራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከዓለም 50 አገሮች ምርጧ አገር እንድትሆን የሚያስችል ‹‹ራዕይ 2020›› የተባለ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ይኼ እንዲሳካም በየአመቱ የ40 ከመቶ ለውጥ ማስመዝገብን መሠረት ያደረገ ውጤት እንዲመዘገብና የአገሪቱ አጠቃላይ ውጤትም አሁን ካለበት 159ኛ ወደ 34ኛ እንዲመጣ ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡

እንዲህ ያሉ ትልልቅ ለውጦችን ለማስመዝገብ ምሳሌ እንደምትሆን የተጠቀሰችው ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ይልቅ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ትገኛለች፡፡ እንዲህ ያሉ ልምድ ልውውጦች በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ለማካሄድ የተቋቋመ ቋሚ የጋራ ኮሚሽን ተሰይሟል፡፡ 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy