NEWS

ሳውዲ አረቢያ ህጋዊ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን ትቀበላለች

By Admin

May 30, 2017

ሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን በህጋዊ መንገድ እንደምትቀበል የሀገሪቱ ሰራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትር አሊ አል ግሃፊስ ተናገሩ፡፡

ለዚህ ያመች ዘንድም ከኢትዮጵያው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር አብዱልፈታህ አብዱላሂ ሀሰን ጋር ስምምነት  ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ ህግ መሰረት የተሰጣቸውን ስራ በአግባቡ ለማከናወን የሚያስል የተሟላ ጤና እና እውቀት ያላቸውን እንዲሁም ከወንጀል ነጻ የሆኑ  ሰራተኞችን ብቻ ለመላክ ከስምምነት ላይ ደርሷ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰራተኞቹ በሀገር ውስጥ አስፈላጊውን ስልጠና መስጠትና የሳውዲ አረቢያን የሥራ ባህርይ፣ ባህልና ህግ  የማስገንዘብ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ከማጠናከሩም በላይ የሰራተኞችንና የአሰሪዎችን መብቶች ለማስከበርና የአሰሪና ሰራተኛ ውሉን ተፈጻሚነትም ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ የሰራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የሰራተኛ ምልመላውንም ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ድርጅቶች አማካኝነት ብቻ ለማከናወን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራተኛቹ ወደ ስራ ከመሰማራታቸው በፊት የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ለማስገንዘብ  የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የኤፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር አረጋግጠዋል፡፡

በአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች በኩል የሚቀርቡ ሰነዶችን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ስምምነቱ በስራ ውሉ መሰረት አሰሪዎቹ ለሰራተኞቹ በሚከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች አማካኝነት ደመወዛቸውን ወደየሀገራቸው ለማስተላለፍ እንደሚያስችላቸውም የሀገሪቱ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡