Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሽብርተኝነትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ምን አገናኛቸው?

0 372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሽብርተኝነትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ምን አገናኛቸው?   /ዘአማን በላይ/                                               

          ዛሬ የዓለማችን ስጋት ከሆኑት ውስጥ ሽብርተኝነት አንዱ ነው፡፡ ይህ የንፁሃን ዜጎችን ህይወት በጠራራ ፀሐይ የሚቀጥፍ ዘግናኝ ተግባር፤ ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ሃብታምና ድሃ፣ የተማረና ያልተማረ፣ የበለፀገና ያልበለፀገ ሀገር አይለይም፡፡ ሁሉንም በደፈናው የሚያጠቃ የጭካኔ ተግባር ነው። ዛሬ ላይ ሽብርተኞች የሌሉበትን የዓለማችን ክፍል ማለም የቅንጦት ያህል እየተቆጠረ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህ እኩይ ሴራ ከዓለማችን ልዕለ ሃያሏ ሀገረ- አሜሪካ እስከ ካናዳ፣ ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሶማሊያ እስከ ኬንያ፣ ከኡጋንዳ እስከ ማሊና ኢትዮጵያ እንዲሁም እስከ ሌሎች ሀገሮች ድረስ በድንበር ተሻጋሪነት የዘለቀ ተግባር ሆኗል፡፡

በየትኛውም ስፍራና በማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ጥፋትን በማስከተል ላይ ያለውን ይህን እኩይ ሴራ “ሽብርተኝነት ምንድነው?” በማለት የሚሰጠው ትርጓሜ እንደየ አተረጓጎሙ የተለያየ ቢሆንም፤ “ሽብርተኝነት አንድን ዓላማ ለማስፈፀም ድርጊቱን የሚያዩትና በሚሰሙት ወገኖች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ታስቦ የሚደረግ እንዲሁም አብሮ በመዶለት የሚከናወን ህገ ወጥ ተግባር ነው” የሚለው አጠቃላይ ብያኔ ግን ሁሉንም የዓለማችንን ሀገሮች የሚያስማማቸው ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው ሽብርተኝነት በዓለማችን ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ተከትሎ የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ ርዕሰ ሆኗል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሽብርተኝነትን ለመከላከል ብሎም ምንጩን ለማድረቅ የሚካሄደው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን ከተግባሩ ተለዋዋጭ ባህሪ የተነሳ ችግሩን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም፡፡

ርግጥ ሽብርተኝነት በልማትና በሰላም ላይ የሚያንዣብብ አደጋ በንፁሃን ዜጎች ህይወት ጥፋት ላይ የሚያነጣጥር የፈሪ ዱላ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ የጅምላ ጥፋትን የሚያስከትለው ይህ ሴራ፤ ምንም እንኳን የትኛውንም ሀገር ለጥፋት የመዳረግ ብቃት ያለው ቢሆንም፤ ችግሩ የሚከፋው ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ደፋ ቀና እያሉ በሚገኙ ሀገሮች ላይ መሆኑ የአሳሳቢነቱን ደርዝ ከፍ ያደርገዋል፡፡

በተለይም ድህነት የደቆሰው የአፍሪካ ቀንድ ለዚህ ችግር የተጋለጠና የሽብር ጥቃት ስለባ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በርግጥ ችግሩን ከቀጣናው ሀገራት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በሁለት ክፍሎ ማየት ጠቃሚነቱ የጎላ ነው። በምስራቅ አፍሪካ በአንድ በኩል የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሻበሪነትን በማስፋፋት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሀገሮችን እናገኛለን፡፡

በቀጣናው ሀገራት ላይ የሚደርሰውን የሽብርተኝነትን ጥቃት በማቀነባበር፣ በመደገፍ፣ በማስፋፋትና በማሰማራት በኩል ኤርትራና ሶማሊያ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ የጥቃቱ ሰለባዎች በመሆን ላይ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያም ከድህነትና ኋላቀርነት የመውጣት ዓላማን አንግበው ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ለሚገኙት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ በተለይም ለፈጣን ልማት ቀጣይነት በመረባረብ ላይ የምትገኘው ሀገራችን ሽብርተኝነት በተለያዩ ጊዜያት ተፈታትኗታል— ሊያንበረክካት ባይችልም፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው ደግሞ ለተግባሩ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የማይፈጥሩት ህዝባችንና መንግስት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑ እሙን ነው፡፡

በርግጥ ሀገራችን የሽብር ጥቃት ሰለባ መሆን ከጀመረች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ብቻ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ አሸባሪዎች በተካሄዱ የሽበር ጥቃቶች የአያሌ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፤ በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል፡፡ ከቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ እስከ ቅርብ ጊዜው በኤርትራ መንግስት አሰማሪነት በሀገራችን የጠረፍ ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለው የሽብር አደጋ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካው የአልቃዒዳ ክንፍ የሆነው አልሸባብ ጀሌዎቹን በመመልመልና በማሰልጠን ባይሳካለትም ለመፈፀም የሚሞክረው የግብረ-ሽበራ ተግባር በማሳያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በማደግ ላይ የሚገኝ ህዝብ የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስራዎችን ከግቡ ለማድረስ ስላምና መረጋጋት ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ሰላም ከሌለ፤ ስለ ልማትም ሆነ ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መናገር ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም በዚያች ሀገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ካልተረጋገጠ፤ ሊመጣ የሚችል ዕድገትም ይሁን ስር እንዲሰድ የሚፈለግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊታሰብ ስለማይችል ነው፡፡

ታዲያ ሀገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ በሀገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን የመፍጠር ጉዳይ በይደር የሚተው አይደለም፡፡ ምከንያቱም ለኢትዮጵያ ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ፤ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር የግድ ይላታል፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በሽርብተኝነት ዙሪያ የሚያጠነጥን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅን አውጥታለች—ሌሎች ሀገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚያደርጉት፡፡

አዋጁ የወጣበት ዋነኛው ምክንያት ህዝቦች በሰላም፣ በነጻነትና በተረጋጋ ሁኔታ ያላቸው ህገ- መንግስታዊ መብት ከመሸርሸር አደጋ እንዲጠበቅ እንዲሁም ሽብርተኝነት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ፀር በመሆኑ የህግ አግባብን ተከትሎ ተግባሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በማለም ነው፡፡ ይሁንና አንዳንድ ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራሎችና የሀገር ውስጥ ጀሌዎቻቸው አዋጁን ለመቃወም ሲሉ የሽብርተኝነትን ተግባር ሃሳብን ከመግለፅ ህገ መንግስታዊ መብት ጋር የግድ ሊያቆራኙት ይከጅላሉ።  

ይህ እሳቤ በየትኛውም ምድራዊ መስፈርት ትክክል ሊሆን አይችልም። መግደልና ነፃነት በምንም ዓይነት ስሌት አንድ ሊሆኑ አይችሉም። የዜጎችን ህይወት በጠራራ ፀሐይ የሚቀጥፍና አንጡራ ሃብታቸውን የሚያወድምን እኩይ ሴራ፤ መልሶ የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብት ከሆነው ሃሳብን ከመግለፅ መብት ጋር ማቆራኘት ተገቢ ሊሆን ይችልም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ዜጎችን ለመግደል የሚደረግ ሴራና ዱለታ ከህዝቦች መብት ጋር እኩል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችልበት መሰረት የለም። እናም መቼምና የትም ቢሆን የሽብርተኝነት ዘግናኝ ሴራና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚገናኙበት መስመር የለም።

እንደሚታወቀው ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 29 ላይ በሚገባ ተገልጿል። በድንጋጌው መሰረትም ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን ሃሳብ የመያዝና በነፃነት የመግለፅ የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይሁንና የትኛውም ዜጋ ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ሽፋን፤ የሀገሪቱን ህገ መንግስትና እርሱን ተከትለው የወጡ አዋጆችን ተፃርሮ መቆም አይችልም። ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራሎች አንድ ሰው ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛ አሊያም ዳኛ ወይም ተኳሽ፣ ቀዳሽ አለያም ሯጭ መራሽ ቢሆንም ከሀገሪቱ ህግ ውጭ በመሆን በማን አለብኝነት ከተንቀሳቀሰ የህግ ተጠያቂ እንደሚሆን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። በእነሱም ሀገር ውስጥ ቢሆን የህግ የበላይነትን ማስከበር ለነገ የሚተውት ጉዳይ አይደለምና።

እዚህ ላይ ሁለት ሃቆችን ላንሳ—ተጠርጣሪው ዶክተር መረራ ጉዲናንና ፍርደኛው “ጋዜጠኛ” እስክንድር ነጋን የተመለከተ። ተጠርጣሪው ዶክተር መረራ የአውሮፓ ህብረት ባደረገላቸው ግብዣ ወደ እዚያው ማቅናታቸው ይታወቃል። ማንም ሰው ወደ ፈለገበት ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት ስላለው በእርሳቸው ጉዞ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ሊኖር አይችልም። ችግሩ ግን ሰውዬው ወደ አውሮፓ ሄደው ያከናወኑት ጉዳይ ነው። አንደኛ ከአሸባሪው ግንቦት ሰባት መሪ ጋር መገናኘታቸውና መዶለታቸው በሀገሪቱ ህጎች የሚያስጠይቃቸው መሆኑ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡትን ክልከላዎች ተላልፈው መገኘታቸው ነው። ቀደም ሲል እንዳልኩት ማንኛውም ግለሰብ የሀገሪቱን ህጎች እስከተላለፈ ድረስ ተጠያቂ ይሆናል። እናም ዶክተሩ ተጠያቂ የሆኑት እንደ ፖለቲከኛ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገፁ ሳይሆን፤ የሀገሪቱን ህጎች በመተላለፋቸው ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ የዶክተሩ ጉዳይ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከዚህ በላይ መሄድ ባይቻልም፤ መጨረሻውን በውሳኔ አሰጣጡ ላይ የምንመለከተው ይሆናል።

ፅንፈኛ ኒዮ ሊበራሎች ሰሞኑን ‘ሃሳቡን በነፃነት በመግለፁ ለእስር ተዳረገ’ እየተባለ ሽልማት….ምንትስ ተሰጠው የሚባለው “ጋዜጠኛ” እስክንድር ነጋ ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይደለም። አቶ እስክንድር በተለያዩ ወቅቶች ሆን ብለው የሀገሪቱን ህጎች በመፃረር አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች የሰጧቸውን ‘ተልዕኮ’ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጉዳዩን የመረመረው ፍርድ ቤት በሰውና በሰነድ ማስረጃ አረጋግጦ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በእስራት እንዲቀጡና ከማህበራዊ መብቶቻቸው እንዲታገዱ ብይን ሰጥቷል። ይህም አቶ እስክንድር ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ አሊያም ጋዜጠኛ” ስለነበሩ ውሳኔ የተሰጣቸው ሳይሆን፤ እንደ ፀረ-ሽብርተኝነት ዓይነት የሀገሪቱን ህጎች ተላልፈው በመገኘታቸው ነው። ይህም ብይንም በምንም ዓይነት የሂሳብ ቀመር ሃሳብን ከመግለፅ ጋር የሚገናኝ አይደለም።

ከእነዚህ ሁለት አብነቶች መገንዘብ የሚቻለው ነገር ቢኖር፤ ግለሰቦች ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ስለሆኑ ያንን “ሙያቸውን” በታዛነት በመጠቀም እንዳሻቸው ሊሆኑ እንደሚፈልጉ ነው። ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደሆነ መጠን፤ ለሌላው ዜጋ ያልተሰጠ ህግን የመፃረር መብት ተለይቶ ለእነዚህ ግለሰቦች ሊሰጥ አይችልም። ሲጀመር በህግና በስርዓት በሚመራ ሀገር ውስጥ ህግን በማን አለብኝነት ተፃርሮ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት መሞከር የሚፈቀድ ጉዳይ አይደለም። ይህን የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት ግለሰቦችን በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ሲያደርግ ጉዳዩን በመጠምዘዝ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም። በእኔ እምነት ፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራሎች የፀረ-ሽብርተኝነት ዓይነት ህጎችን ከዜጎች የማይገሰሱ መብቶች ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት ያላቸውን ንቀትና መብቱ አፍሪካ ውሰጥ በጭንብልነት እንዲያገለግል ምን ያህል ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመላክት ነው። እናም ከዚህ ፍላጎታቸው በመነሳት ‘ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ታሰሩ’ የሚባሉት ግለሰቦች የፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች መሆናቸውን ለመገመት የሚከብድ አይመስለኝም።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy