Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሽብርተኝነት ሲባል…

0 560

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሽብርተኝነት ሲባል…

                                               ታዬ ከበደ

ሽብርተኞች ሃይማኖትንና ፖለቲካን ከለላ በማድረግ ዓላማቸውን በኃይል ለማስፈን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዒላማዎቻቸው ንፁኃን ዜጎች ናቸው፡፡ የሶማሊያው አልሸባብ፣ የናይጄሪያው ቦኮ ሐራም፣ የአፍጋኒስታኑ ታሊባን፣ ከየመን እስከ ኢራቅ የሚንቀሳቀሰው አልቃዒዳ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ በመንሰራፋት ላይ ያለው ኢስላሚክ ስቴት የሚፈጽሙዋቸው የሽብር ድርጊቶች በሙሉ በንፁኃን ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸው አይዘነጋም።

የተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ይዘው የተነሱ የሽብር ቡድኖች ሃይማኖትን ከለላ ቢያደርጉም፣ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ በሚጽሙት ጭፍጨፋ ዋነኛ ተግባራቸው መሆኑ በገሃድ እየታየ ነው። አሸባሪዎቹ ንፁኃንን ዒላማ ማድረጋቸውና አውዳሚነታቸው መለያቸው ከሆነ ሰነባብቷል። የሽብርተኝነት ተግባር አጽናፍና ዳርቻ የሌለው ነው። በየትኛውም ጊዜና ቦታ በማንኛውም ግለሰብ ላይ ጥቃት ሊፈፀም ይችላል።

የሽብርተኝነት አደጋ የትም ሀገር ውስጥ እንዳለው ሁሉ፤ እኛም ሀገር ውስጥ ሊኖር አይችልም ብሎ መደምደም አይቻልም። በተለያዩ ወቅቶች ፍርድ ቤት የሚቀርቡና የእነ ኦነግን፣ ግንቦት ሰባትንና ኦብነግን የመሳሰሉ አሸባሪዎችንና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ዓላማ አንግበው በሰላም ወዳዶቹ ህዝባችንና በፀጥታ ሃይሎች ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በዋቢነት ማንሳት ይቻላል። እናም ጉዳዩን ከቀጠናውና ከሀገራችን አኳያ መመልከቱ ለአንባቢያን ግንዛቤ የሚሰጥ ነው።

እርግጥ ሽብርተኝነት በልማትና በሰላም ላይ የሚያንዣብብ አደጋ በንፁሃን ዜጎች ህይወት ጥፋት ላይ የሚያነጣጥር የፈሪ ዱላ ነው፡፡ ታዲያ የጅምላ ጥፋትን የሚያስከትለው ይህ የጥፋት መንገድ ምንም እንኳን የትኛውንም ሀገር ለችግር የመዳረግ ብቃት ያለው ቢሆንም፤ ችግሩ የሚከፋው ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ደፋ ቀና እያሉ በሚገኙ ሀገሮች ላይ መሆኑ የሚያሳስብ አድርጎታል። እንደሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ለዚህ ችግር የተጋለጠና የሽብር ጥቃት ስለባ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል።

በእርግጥ ችግሩን ከቀጠናው አገራት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በሁለት ክፍሎ ማየት ጠቃሚነት የጎላ ነው። በምስራቅ አፍሪካ በአንድ በኩል የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሻበሪነትን በማስፋፋት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሀገሮችን እናገኛለን፡፡

ከዚህ አኳያም ከድህነትና ኋላቀርነት የመውጣት ዓላማን አንግበው ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ለሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ በተለይም ለፈጣን ልማት ቀጣይነት በመረባረብ ላይ የምትገኘው ሀገራችን ሽብርተኝነት በተለያዩ ጊዜያት ተፈታትኗታል። ሊያንበረክካት ግን አልቻለም፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው ደግሞ ለተግባሩ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የማይፈጥሩት ህዝባችንና መንግስት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑ እሙን ነው።

ኢትዮጵያም የሽብር ጥቃት ሰለባ መሆን ከጀመረች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ብቻ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ አሸባሪዎች በተካሄዱ የሽበር ጥቃቶች የአያሌ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፤ በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል።

በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ሽብርተኝነት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው በኤርትራ መንግስት የሚደገፉ፣ የሽብር ተግባሩን ለማሳካት የሚሰማሩ ብሎም የተላላኪነት ሚናቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ አሸባሪዎችና ፀረ-ሠላም ኃይሎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የምስራቅ አፍሪካው የአል ቃዒዳ ክንፍ የሆነው አል ሸባብ በሀገራችን ላይ የደቀነው ግልፅና ድርስ የሽብር አደጋ ነው።

አሸባሪዎችንና ፀረ ሰላም ሃይሎችን የማደራጀት፣ የማሰልጠን፣ የማስታጠቅና የማሰማራት አባዜ የተጠናወተው የኤርትራ መንግስት፤ በተለይም ራሳቸውን ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና ኦብነግ እያሉ የሚጠሩ አሸባሪ ቡድኖችን ወደ ሀገራችን አሰርጎ በማስገባት የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቶችን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ ዛሬም ድረስ ከድርጊቱ አልተቆጠበም።

በሀገራችን ላይ ከተቃጡት የሽብር ጥቃቶች መካከል፣ በመዲናችን አዲስ አበባ በትግራይ ሆቴል፣ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላየ የደረሰውን የሽብር ድርጊት የፈጸመው የአስመራው መንግስት ተላላኪው ኦነግን እናገኛለን፡፡ አሸባሪው ኦነግ በፈሪ ዱላው የንጹሃን ዜጎችን ህይወት የመቅጠፍ እኩይ ተግባር በዚህ ብቻ ሳይወሰን፤ በባቡር ትራንስፖርት፣ የተለያዩ መሰረተ ልማት ተቋማትን በማውደም ጭምር ድብቅ አጀንዳውን ለማስፈጸም፣ በዜጎች ላይ ፍርሃትና ውዠንብር ለማንገስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ ስኬቱ ያልተሳካና የማይሳካ ቢሆንበትም።

ሽብርተኛው ኦነግ የታጠቀ ኃይሉን አሰርጎ በማስገባት ሀገራችን ከድህትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ትግል ለማኮላሸት የተለያየ ጥረት ቢያደርግም፤ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ወድመት የሚያስከትሉ ጥቃቶች ለመሰንዘር ያካሄዳቸው ሙከራዎቹ ግን ለፍሬ ሳይበቁ ተጨናግፈዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርተው ዓላማቸውን ሳያሳኩ በሠላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጥረት ለፍርድ ከቀረቡ የአሸባሪው ቡድን አባላት አማካኝነት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

ሻዕቢያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የማደናቀፍ ተልዕኮን ለጋሻ ጃግሬውና እራሱን ግንቦት ሰባት ብሎ ለሚጠራው አሸባሪ ቡድን የሰጠው፡፡ ታዲያ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ልማትና ሠላም የቆመ ሃይል በማስመሰል በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚደሰኩረው አሸባሪው ግንቦት ሰባት፤ ተለዕኮውን ለመቀበል ጥቂት እንኳን አላቅማማም። ይህም ሀገራዊ ባንዳነቱን ያረጋገጠ ክስተት ሆኖ አልፏል። ያም ሆኖ ‘ኢሳት’ በተሰኘው የውሸት ማቀነባበሪያ ቴሌቪዥኑ ላይ ከመለፍለፍ በስተቀር ያገኘው አንዳችም ውጤት የለም።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልማትን ለማደናቀፍ የተላላኪነቱን ሚና ከተረከቡት መካከል አሸባሪው ኦብነግ ይጠቀሳል። ኦብነግ ከሻዕቢያና ከሌሎች የሀገራችንን ልማት ከማይሹ ሀገሮች ተልዕኮን እየተቀበለ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልማትን የማደናቀፍ ስራን አንግቦ የአፍራሽነት ሚናውን ሲወጣ ቆይቷል። ይህ የሽብር ቡድን  በጅግጅጋ ከተማ በአንድ ሆቴል ላይ ባደረሰው የሽብር ጥቃት የበርካታ ዜጎች ህይወትን ቀጥፏል። በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ላይ ያደረሰው የሽብር ጥቃትም ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበር ከሀገራችን ህዝብ የሚሰወር አይደለም።

የክልሉ ህዝብ የዘመናት የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ በመንግስትና በክልሉ መንግስት አማካኝነት ሲካሄዱ በነበሩት የመሰረተ ልማት ተቋማት ላይ ጋሬጣ ከመሆን አልፎ ፤የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያካሂድ ተስተውሏል፡፡ የክልሉ ህዝብ በህገ መንግስቱ የተጎናጸፈውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በመግፈፍ የራሱን ፍላጎት ለመጫን በርካታ ጥረቶችን አካሂዷል። ታዲያ እነዚህ ጥረቶቹ ከንቱ ከመሆናቸውም በላይ ዛሬ ላይ የሽብር ቡድኑ ትርጉም ወደ ሌለው ደረጃ ደርሷል።

እንደሚታወቀው መንግስት የፀረ ሽብር ህግን አፅድቋል። የፀረ ሽብር ህጉ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘበ ወቅታዊነቱን የጠበቀ፣ ለሀገራዊው ልማት፣ አስተማማኝ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቀጣይነት ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ምክንያቱም ድህነትና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የሠላምንና ልማትን ማረጋገጥ እጅጉን ቁልፍ ተግባር በመሆኑ ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ የሀገራችን ዕድገት በመፋጠን ላይ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን የግድ ይላል፡፡ የአስተማማኝ ሠላም መስፈን ሽብርተኝነትን መዋጋት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እናም ሸብርተኝነትን ከሩቅ ማስቀረት የሚችል ህግ መኖሩ ወሳኝ ነው፡፡

በተለይም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት፣ ለስልጣን መቆናጠጫነት ተግባር ከመረጡ ሃይሎች ባሻገር፤ ዓላማቸውን ለማሳካት የተለያዩ ፀረ ህገ መንግስታዊ ስልቶችን ለመጠቀም ሞክረው ያልተሳካላቸውና በተስፋ መቁረጥ የሚወራጩት አሸባሪ ቡድኖችም እየተስተዋሉ ነው።

እናም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ሰላም የማተራመስ ዓላማ ኢንግቦ ሲንቀሳቀስ የቆየው የኤርትራ መንግስት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ተቃዋሚ ሃይሎችን በማስታጠቅና በማሰማራት ሀገራዊ ልማታችንን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ከማድረጉ በተጨማሪ ሀገራችን ለሽብር ጥቃት ዳርጓት ቆይቷል። እንደ ኤርትራ መንግስት ሁሉ ሶማሊያም ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተለይም ለሀገራችን የሽብር ጥቃት ተጋላጭነት የበኩሏን ድርሻ ስታበረክት የቆየች ሀገር ናት፡፡ የሀገሪቱን መንግስት መውደቅ ተከትሎ የበርካታ አሸባሪ ቡድኖችን ቀልብ የሳበችው ሶማሊያ፤ በመንግስት አልባነቷ የአሸባሪዎች መናኸሪያ በመሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች የሽብር ተጠቂነትና ተጋላጭነት አይነተኛ መንስዔ ሆና ስታገለግል ቆይታለች፡፡ አሸባሪዎቹ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የሽብር ኢላማቸው በማድረግ ባደረሱት ጥቃትም በተለያዩ የቀንዱ አገራት ውስጥ ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል፡፡ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም አስከትለዋል፡፡

ምንም እንኳን አልሸባብ አላማውን ማሳካት የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ ሀገራችን ወስጥ እጅግ የጠበበ ቢሆንም፣ በየትኛውም ሀገር ሊከሰት እንደሚችለው ሁሉ ሀገራችን ውስጥም የሽብር ተግባር አይከሰትም ማለት አይቻልም። ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን በሚሉ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ወይም በሌሎች አካላት ሊከሰት ይችላል። መንግስት ችግሩን ለመቋቋምና ተግባሩን ለመዋጋት እስከዛሬ ድረስ ብርቱ ጥረት አድርጓል፤ ከህዝቡ ጋር በመሆን። ይህ ጥረቱ በሁሉም ዜጎች ይበልጥ ሊደገፍ ይገባል። መንግስት ያለ ዜጎች ድጋፍ ሊያደርገው የሚችላቸው ጉዳዮች እጅግ ጥቂት ናቸው። እናም ሽብርተኝነትን ለመከላከል ዋናው ስራ ያለው በእያንዳንዱ ዜጋ መዳፍ ውስጥ መሆኑን በመገንዘብ፤ ዜጎች የበኩላቸውን እገዛ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy