Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀላል ይሆናል

0 354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀላል ይሆናል/ዮናስ/

ብሄራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የትግበራ ምእራፍ የተሰኘውንና ለአለምአቀፋዊና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ተገዢ መሆኑ የተነገረለትን የመጀመሪያውን ሰነድ ሃገራችን ይፋ ካደረገች እነሆ ሁለት አመታት አልፈዋል። ሁለተኛው ብሔራዊ መርሐ ግብር ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ሆኗል፡፡

በመርህ ደረጃ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች ተፈጥሮአዊና በሕይወት መኖር ተነጥለው የማይታዩ ተደርገው የሚወሰዱ ነበሩ፡፡ ዜጎችን በማስተማርና ንቃተ ህሊናቸውን ከፍ ያለ እንዲሆን በማድረግ አንዳንድ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዚህም ከፍ ባለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል። ኮሚሽኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችን ጨምሮ አንዳንድ ወሳኝ ክስተቶችን በመፈተሽ፣ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች እንዲሰባሰቡና የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎችን ከመስራትም አልፎ  ጥፋት ፈጻሚዎች እንዲቀጡ ሽንጡን ገትሮ በመሞገትም ላይ ይገኛል፡፡  

ባለፉት 22 ዓመታት በኢትዮጵያ የተተገበረውና በፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥርዓት አወቃቀር ላይ የተመሠረተው ሕገ መንግሥት ይዘት፣ አንድ ሦስተኛው በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚያነጣጥር መሆኑ ይታወቃል፡፡ይህ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀደቀውና የቬና ዲክላሬሽን እየተባለ የሚጠራውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በመቀበል ለተግባራዊነቱ ቃል የገባው ሕገ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን አካቷል፡፡ ከመሠረታዊ የሰው ልጆች መብት ጀምሮ እስከ ፖለቲካና ሲቪል መብቶች ይገኙበታል፡፡ በዚህም መሠረት በተለይ የሰው ልጅ መሠረታዊ በህይወት የመኖር፣ የመበልፀግ፣ ሐሳቡን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና የመቃወም መብቶችን አጠቃልሎ ይዟል፡፡

በየአራት ዓመቱ በመደበኛነት ለተመድ የሚቀርበው የሰብዓዊ መብት የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረክ ለአንዳንድ አገሮች ምክረ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም ባቀረበችው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ከተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አንዱ ብሔራዊ ሰነድ ማዘጋጀት ነበር፡፡ በተለይ የፖለቲካና የሲቪል መብት አያያዝን እንዲያሻሽል ምክረ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት የድርጊት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት የተሰጠው ምክረ ሐሳብ ላይ ተመስርቶ እየሰራ ለመሆኑ እኒህ የድርጊት መርሃ ግብር ሰነዶች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት መንግሥት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አቀናጅቶ በማከናወን ፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ግንዛቤ ከፍ ለማድረግና የሰብዓዊ መብት ጥቃቶችን ለመከላከል ያለመ እንደሆነ በራሱ በሰነዱ ሰፍሯል፡፡ የመጀመሪያው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር መጠናቀቅ ላይ የተከሰተውን አመፅ ተከትሎ የደረሰውን የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት መርምሮ፣ መነሻው በአብዛኛው የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት መሆኑን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የገለጸው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተግባር ከአንደኛው የድርጊት መርሐ ግብር ዓላማ ተፈጻሚ ከመሆን ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። ሁለተኛው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ይፋ በሆነበት ወቅትም፣ የአስተባባሪው ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያው መርሐ ግብር ከሞላ ጎደል ግቡን የመታ እንደነበር ያቀረበው ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ እንደ መጀመሪያው ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ሁሉ ሁለተኛው መርሐ ግብርም ይፋ የሆነው፣ በጣም ትልቅ ትኩረት በተሰጠውና በርካታ እንግዶች ታዳሚ በሆኑበት ሰፊ መድረክ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በይፋ መከፈቱን  ማብሰራቸው ለጉዳዩ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመላክት ነው፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠናቅሮ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው ይኸው ዕቅድ፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻልና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት እንደ አንድ መሣሪያ የሚያገለግል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ መርሐ ግብሩ ሁለተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አድርጎ የተነሳ መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው ለሕዝቡ የመልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ትርጉም ያለው ምላሽ ይሆናል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል በመንግስትም በኩል ተቀባይነትን ያገኘው አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ መርሃ ግብሩ በዝርዝር ያልተመለከተ መሆኑ ነው፡፡  

በድርጊት መርሐ ግብሩ ሥር አራት ዋና ዋና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች በቀዳሚነት፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የባህል መብቶች፣ በመብት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በአካባቢ ደኅንነትና የመልማት መብት ሥር በርካታ የሰብዓዊ መብት ዝርዝሮች ሰፍረዋል፡፡

የሕግ የበላይነት ማለት በሕጉ መሠረት ብቻ ኃላፊነትን መወጣት ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በመጨፍለቅ ያደረሱት ጉዳት ምን ያህል ሃገራችንን ለአደጋ  አጋልጠዋት የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ይህ መርሃ ግብር ሆን ተብሎ እየታለፉ አገርን ችግር ውስጥ የሚከቱ አሰራሮችን አደብ  የሚያስገዛ ይሆናል፡፡  

ተግባራዊነቱን በተመለከተ ደግሞ አስፈጻሚውን መንግሥት፣ ሹማምንቱን፣ ፖለቲከኞችንና ሠራተኛውን ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ እያንዳንዱ ተቋም በሕግ ተደንግጎ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ ሲደረግ፣ አሠራሩ ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነቱም በዚያው ልክ ይታያል፡፡ አመራሩም ሆነ ፈጻሚው በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ከሰራ መርሃ ግብሩን በመሬት ላይ ማውረድ ቀላል ይሆናል። አለበለዚያ ግን የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ ሌብነት ይንሰራፋል፡፡ የአገር ሀብት ይባክናል፡፡ ፍትሕ ይታጣል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሰላም ይደፈርሳል፡፡ የአገር ገጽታ ይበላሻል፡፡ ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሁሉንም ለማቅለል የሚጠበቀው ቀላል ነገር ሁሉም የየድርሻውን መወጣት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy