Artcles

ቆም ብሎ ማሰብ ከወጣቶቻችን ይጠበቃል

By Admin

May 22, 2017

ቆም ብሎ ማሰብ ከወጣቶቻችን ይጠበቃል

ስሜነህ

በየሃገራቱ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል የወጣቶች ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ከእለት እለትም እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ከየሃገራቱ ለሚደረጉ ስደቶችም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በሃገራቸው ያለን ጦርነት በመሸሽ፣ መታሰርና መገደልን መፍራትን ጨምሮ የተሻለ ኑሮ ፍለጋና ስራ አጥነት እንዲሁም ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች ታዲያ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከላይ ከተመለከቱት ቢያንስ በአንደኛው ምክንያት በየብስ ሲጓዙም በተዘጉ ድንበሮች ምክንያት ሕይወታቸውን በረሃ ላይ ያጣሉ፡፡ ሆኖም ስደተኞች እንዳይገቡ በማለት አገራት ድንበሮቻቸውን መዝጋት ቢጀምሩም፣ የስደተኞችን ፍሰት መከላከል አልተቻለም፡፡ ይልቁንም ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ስደት ተበራክቷል፤ የስደተኞች ቁጥርም አሻቅቧል፡፡  

የስደተኞች ጉዳይ ከሚመለከታቸው ተቋማት መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ነው። ኤጀንሲው በየአመቱ በሚያከብራቸው የዓለም ስደተኞች ቀን ላይ ይፋ የሚያደርጋቸው ሪፖርቶች የሚያመለክቱትም ከሃገራቸው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር 65.3 ሚሊዮን መድረሱን ነው፡፡

ኤጀንሲው ከመንግሥታትና ከአጋር ድርጅቶች የተገኙ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ በ2015 ማብቂያ ላይ ይፋ ያደረገው ጥናት 65.3 ሚሊዮን ሰዎች መሰደዳቸውን ሲያመላክት፣ ከ12 ወራት በፊት ከነበረው 59.5 ሚሊዮን ስደተኞች ጋር ሲነጻጸር የ5.8 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም በስደተኞች ታሪክ ትልቁ ቁጥር ሲሆን ይህ ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ የሚመጣ እንደሆነም የየአመቱን ቀመር ያሰላው ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

የኤጀንሲው ዓላማዎች  ከሆኑት ውስጥ ዋነኛው ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ ወይም በሄዱበት ሃገር የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖራቸው ማስቻል ቢሆንም ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ያደረገው እና በማድረግ ላይ የሚገኘው ጥረት ተሳክቶ የማያውቅ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል። እንደ ኤጀንሲው የአሰሳ ጥናት ከሆነ በ2014 በዓለም ከሚገኙ ስደተኞች አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ ወደአገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በሰው አገር ያሉትም ቢሆኑ ሥራ በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት ያላቸው ዕድል አናሳ ሲሆን፣ የሥራ ፈቃድ ለማግኘትም ይቸገራሉ።

ብዙዎች ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ የመሰደድ ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የተሻለ የገቢ ምንጭና ኑሮ በመሻት ቢሆንም እዚህ ላይ ሕገወጥ ደላሎችና በሰው ንግድ የተሰማሩ አዘዋዋሪዎች የማይጨበጥ ተስፋ በመስጠት የሚጫወቱት ሚና ግን ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።እነዚህ ሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች የፋይናንስ አቅማቸው እጅግ የፈረጠመ፣ ከሃገር ሃገር የተዘረጋ ሰንሰለታቸውና መዋቅራቸው የተወሳሰበና የረቀቀ ስለመሆኑም የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡  

ከነዚህ መካከል ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ይፋ ያደርገው ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ እነዚህ ከተለያዩ አገሮች በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ተፅዕኖ የሚሰደዱ ሰዎች ተስፋ ወደ ሚያደርጉት ሃገር ለመድረስ፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ35 እስከ 40 ሺሕ ዶላር ለእነዚህ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ይከፍላሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያንን የሚጨምር ሲሆን፣ አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ እንኳን ብናሰላው በአማካይ ከ800 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደ ማለት ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ለከባድ ድብደባና አስገድዶ መደፈር፣ እንዲሁም በቃላት ለመግለጽ ለሚከብድና ለሚዘገንን ኢሰብዓዊ አያያዝ ተጋልጠዋል፡፡ የተጠየቁት ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በተለይም አፍሪካውያን ስደተኞች ምን እንደሚሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሊቢያ ምድር ያሉበትን ሁኔታና የደረሰባቸውን ግፍ ማስታወስ በቂ ነው  ፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ እነዚህ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሊቢያ ውስጥ በአዘዋዋሪዎች እጅ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች፣ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ገበያ ላይ እንደ ዕቃ ይሸጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜድትራንያን ባህር አቋርጠው ለመድረስ በተለያዩ ማጎሪያዎችና እስር ቤቶች ያለ ምግብና መፀዳጃ ታሽገው በእነዚህ አዘዋዋሪዎች እጅ እንደሚገኙ የገለጸው ድርጅቱ፣ ሜድትራንያን ባህር ለማቋረጥ በቂ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉና ከትውልድ አገራቸው ተነስተው አስቸጋሪውን የሰሃራ በረሃ ሲያቋርጡ ገንዘባቸውን አሟጠው ለደላሎቹ የከፈሉ ናቸው፡፡ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ እነዚህ ስደተኞች ገበያ ላይ ከአንድ ደላላ ወደ ሌላው እያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 500 ዶላር ይሸጣሉ፣ አልያም ይገዛሉ፡፡

እነዚህ ገበያ ላይ እንደ ዕቃ የሚሸጡት ስደተኞች ለቀጣይና መቋሚያ የሌለው የገንዘብ ክፍያና አስገዳጅ የጉልበት ሥራ የሚዳረጉ ሲሆን፣ ሴቶቹ ደግሞ በተለያዩ የጎሳ መሪዎችና ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተገደው ይደፈራሉ፡፡በእኛ ሃገር ስደተኞችም ላይ እየተፈጸመ ያለው ተመሳሳይ ወንጀል እንደሆነ ባለፈው አመት ላይ በሊቢያ ምድር ከደረሰባቸው ዘግናኝ አደጋ በላይ ዋቢ መጥቀስ አስፈላጊ አይሆንም ። አስፈላጊ የሚሆነው የችግሩ ምንጭን መፈተሹ እና ምንጩን የሚያደርቅ መፍትሄ መሻት ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ የሃገራችን ወጣቶች ያላቸውን ጥሪትና ገንዘብ ከፍለው ወደዚህ የገሃነም ምድር እየተጓዙ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙዎቹ በንዴትና በፀፀት ስሜት ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ በከባድ የሥነ አዕምሮ ጭንቀት ለእብደት ይዳረጋሉ፡፡እነዚህ ሕገወጥ ደላሎች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ኤርትራውያን ስደተኞች በሚኖሩባቸው ካምፕ ሳይቀር በመግባት የወንጀል ድርጊታቸውን እያከናወኑ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የድርጊቱ ስላባ የሆኑ ሰዎችም የደረሰባቸውም ለተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎች ምስክርነት እየሰጡ ነው ፡፡ ከእነዚህ የስደተኞች ካምፕ በሕገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ አውሮፓ ለመሻገር በከባድ የጭነት መኪና ተሳፍረው ሱዳን ውስጥ ሲጓዙ የነበሩ ከ60 በላይ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ አልቀዋል፡፡

ይህ ዘግናኝና አስከፊ አደጋ ማጋጠሙ እንደተነገረ ከቀናት በኋላ ደግሞ 26 ሕገወጥ ስደተኞችን ጭኖ ወደ ሱዳን በሌሊት ሲጓዝ የነበረ የጭነት መኪና ሁመራ አካባቢ እንደደረሰ ገደል ውስጥ ገብቶ አንድ ሰው ወዲያውኑ ሲሞት፣ የተቀሩት በከባድ ቆስለው ወደ ሽሬና መቀሌ ዓይደር ሆስፒታል ተወስደው የነበረ መሆኑም ይታወሳል፡፡ ይህ የሚነግረን ሀቅ ቢኖር ብዙዎች ጥረውና ግረው መለወጥ እየቻሉ በማይጨበጥ የደላሎች ተስፋ ተታለው ለከፋ አደጋ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ነው፡፡

በእርግጥ በዚህ የሕገወጥ ደላሎች  ሰዎችን የማዘዋወር የሰንሰለት ድርጊት ምክንያት እያለቀ ያለው ወጣት እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ፣ ድርጊቱ የተወሳሰበ በመሆኑ በቀላሉ መከላከል የሚቻል አይደለም፡፡ የመንግሥት፣  የቤተሰብ፣ የሕዝብ የተለያየ በዚህ ጉዳይ የተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው ሥራ ይጠይቃል፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ በጽንፈኛው ‘አይኤስአይኤስ’ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ጊዜያዊ አጀንዳና ቁጣ ፈጥሮ ተወራበት፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ቢያንስ የሳምንት መነጋገሪያ አጀንዳቸው ሆኖ ስለሕገወጥ ስደትና ደላሎች ብዙ ተባለ፡፡ ሕገወጥ ስደት የሚያስከትለው አደጋና ችግር በየመንገዱ ሳይቀር የሃገር  አጀንዳ የነበረው ቢበዛ ለአንድ ወር ነው።

የዜጎች በሕገወጥ መንገድ መሰደድና የደላሎች ወንጀል ግን በሳምንት የወሬ ጋጋታና ቁጣ የሚቆም አልሆነም፡፡ አደጋውና ውስብስብነቱ ገዝፎ የብዙ ቤተሰቦችን ሕይወትና ኑሮ እያናጋ፣ የብዙ ወጣቶች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበታል፡፡  

የተለያዩ አገሮች ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለስደት እንዲዳረጉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሰፊ ጥናት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን እያንዳንዱን ቤተሰብ ያንኳኳ ነው፡፡ ብዙዎችን ለአሰቃቂ ሞትና እልቂት የዳረገ አሳዛኝ የዘመኑ ክስተት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች አብዛኛዎቹ በደላሎች አማካይነት እንደሆነ ከስደተኞች አንደበት በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለከቱት በሞያሌ አድርገው ኬንያ በመግባት ታንዛኒያ፣ ማላዊና ዚምባቡዌን አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሙሉ በሙሉ በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት ነው። በእነዚህ ደላሎችም ሆነ በጉዞው አስቸጋሪነት ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸውና አብዛኛዎቹም ኮንቴይነር ውስጥ ታሽገው እንደሚያልቁ ጥናቶቹ ያመለክታሉ፡፡ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሕገወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጡ ስደተኞች በእያንዳንዱ ሰው ለደላሎች እስከ 80 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈል በአንደኛው ጥናት የተመለከተ ሲሆን፤ሕገወጥ ደላሎች ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ፣ ስደተኞቹ የኬንያን ድንበር ሲያቋርጡ በኬንያ ፀጥታ ኃይሎች ከተያዙ “የአገር ድንበር በመድፈር” ወንጀል ተከሰው ለእስር እንደሚዳረጉ ተጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ደላሎች ግን ወንጀል በመሥራት ያገኙትን ገንዘብ ይዘው በመሄድ ስለታሰሩ ስደተኞች ምንም ደንታ እንደሌላቸው ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ለኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ስደት የደላሎች ሚና የጎላ ሲሆን፣ ኬንያ ውስጥ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የኬንያ ደላሎች እንደሚበዙና ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ደላሎች ስማቸውን እየቀያየሩ ይህንኑ ወንጀል እንደሚሠሩ ከስደት ተመላሽ የሆኑ ዜጎቻችን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኖች በተደጋጋሚ ሲገልጹ አድምጠናል አይተናል፡፡

ሌላው እና ዓለም አቀፍ ሥጋትና ጭንቀት እየፈጠረ የሚገኘው በሊቢያ በኩል በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚደረገው ሕገወጥ ስደት ነው፡፡ የዚህን የስደት ጉዞ ለየት የሚያደርገው በተለይ ከምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካ በከፍተኛ ሐሩርና በረሃ በደላሎች እየተመሩ፣ ከ10 እስከ 20 ቀናት የእግር ጉዞ ማድረጋቸውና ብዙዎቹ ያሰቡትንና ያለሙትን ሳያገኙ በየበረሃው ማለቃቸው ነው፡፡የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያሰራጩት ከሆነ በዚህኛው የስደት መንገድ ያለው ሰብዓዊ ዕልቂት የሴቶች መደፈርና የሰዎች የኩላሊት ንግድ እጅግ በጣም ዘግናኝና አስከፊ ነው፡፡

በዚሁ በሊቢያ በኩል አውሮፓ ለመድረስ ለሚደረገው ሕገወጥ ስደት እያንዳንዱ ስደተኛ ለሕገወጥ ደላሎች እስከ 200 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈልም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ዕድለኛ ሆነው ከሞት አፋፍ ወይም ከአንበሳ መንጋጋ የማምለጥ ያህል በሕይወት ከተረፉ ነው፡፡ ብዙዎቹ  ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን ገንዘብ ለሕገወጥ ደላሎች አስረክበው ሀሩር እንደ እሳት በሚለበልበው የሊቢያ በረሃ ወድቀው ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ በዚህም ቤተሰቦቻቸውን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡

አውሮፓ የደረሱትም ቢሆኑ እንዳሰቡትና እንዳለሙት ሳይሆን በመቅረቱ፣ ገሚሶቹ በንዴትና ብስጭት በገዛ ራሳቸው ሕይወታቸው ሲያጠፉ ቀሪዎቹ ደግሞ ከገቡበት ድብርትና ጭንቀት ለመላቀቅ የአልኮልና የዕፅ ሱሰኞች መሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የሚያወጣው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለዚህ ተጋላጭ የሆነው አብዛኛው የሃገራችን የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የሌለው መሆኑ አንደኛው ምክንያት መሆኑን የተገነዘበው መንግስት አሁን ወጣቶች በሃገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚችሉበትን እድል ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ በአገራችን የተስፋፋው የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆኖ ከቆየ በኋላ የወላጆቹን ልማዳዊ የግብርና ስራ ሊቀጥልበት የማይፈልግ እየሆነ መምጣቱም የገጠሩ ወጣት ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች እና  ከላይ ወደተመለከቱ ሃገራት በህገወጥ መንገድ የሚሰደድ መሆኑንም ተገንዝቦ እዚሁ መስራት የሚችሉባቸው ፓኬጆችን ቀርጾ ውጤታማ በሆነ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።

ወጣቱ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው እና በዚህም ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ ከሆነ ለህገወጥ ደላሎችና ስደት ሰለባ መሆኑ የማይቀር መሆኑን የተገነዘበው መንግስት ከመቼውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ እያደረገ መሆኑንም ወጣቶች ሊያጤኑ ይገባል፡፡በጥቅሉ ወጣቶች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ በመሆን ከላይ ለተመለከቱ አስከፊ አደጋዎች ተጋላጭ እየሆኑ የሚገኙት ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ተጠቃሚነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች መሆኑን የተገነዘበው መንግስት ራሱን ወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት የሚቻልባቸው እድሎችን አመቻችቷልና ቆም ብሎ ማሰብ ከወጣቶቻችን ይጠበቃል ።