Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህገ መንግስቱ ያገኘናቸው ድሎች

0 247

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህገ መንግስቱ ያገኘናቸው ድሎች

                                                          ታዬ ከበደ

የአገራችን ህገ መንግሥት አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል፡፡ ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር የመቀየስ ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል፡፡ መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበት በህዳር ወር 1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ መንግሥት ያረጋግጣል፡፡

ህገ መንግሥቱ ሁሉም ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህም ጋር በደርግ ሥርዓት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ የናደ ሆኗል፡፡ በዚህም ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተከብሮለታል፡፡

ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል፡፡ በመሬት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በጽኑ መሠረት ላይ ጥሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል፡፡ እኚህ ሁሉ የግንቦት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ህዝቦች ለነጻነት ባደረጓቸው ትግሎች አምባገነኑን ሥርዓት ላይመለስ ገርስሰውታል፡፡ 26 ዓመታት ሊቆጠሩም ቀናት ቀርተውታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት መላ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስኮች አያሌ ድሎችን አስመዝግዋል፡፡ የድል ፍሬዎቹንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡

በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል፡፡ ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል፡፡

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል፡፡ ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝ}ቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል፡፡

የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ፡፡

የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም የክልሎችን እኩል የመልማት እድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ህገ መንግስቱ ላይ የተደነገገው የመልማት መብት እውን እንዲሆን መንግሥት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውሰን ሀብትን መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ ተግባራት ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የሕዝብ ተሳትፎን በማጐልበት እና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት እድገትና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ህገ መንግሥቱ በሚደነግገው ፍትሀዊና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገው ልማት መሠረት በመንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት የአገሪቱን በአጠቃላይ፤ በገጠር የሚኖረውን እጅግ በርካታ ሕዝብ በተለይ የሚጠቅም ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ስትራቴጂው ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ፣ ሕዝቡ ከልማቱ በላቀ ደረጃ እንዲጠቀም  ለማድረግ፣ ኢትዮጵያን ከተመጽዋችነት ለማዳን እና በአገሪቱ የዳበረ የነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡

በዚህ መሠረት የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን በመከተል ግብርና ዋና የኢኮኖሚ እድገት ምንጭ ሆኖ የኢንዱስትሪ ልማቱ እንዲፋጠን ስትራቴጂው ከኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችና ማህበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ትምህርት፣ ጤናና ውኃ እንዲሁም ከከተማ ልማት ጋር ትስስርና ተመጋጋቢነት ባለው አግባባ ተፈፃሚ በመሆን ላይ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ በግብርና የሚተዳዳረውን ኅብረተሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡

በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሚመራው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሳትፎና ከተጠቃሚነት አንፃር መንግሥት በዋነኛነት ለጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል፡፡ ውጤትም እያገኘበት ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ በአገሪቱ የተሟላ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ አድርጓል፡፡ በህገ መንግስሥቱ አውቅና ያገኙ የስብዓዊና የዴሞክራሲያዊ ውጤቶች የተሟላ ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ዝግጁነት እንዳለው የሚያረጋግጡ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የክልሎች ህገ መንግሥት የፌዴራልና የክልሎች ፖሊሲዎችና ህጐች በህገ መንግሥቱ የተመለከቱ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ውጤቶችና ነፃነቶች መርሆዎች መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም ህገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ህግ እና የሌሎች ህጐች ህጋዊነት መሠረት ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ሁኔታም ሀገራችን ውስጥ ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል እንዲሆንና ከህግ በላይ እንዳይሆን አድርጓል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy