Artcles

በመስዋዕትነት የተሰበረው የሳንሱር ቀንበር

By Admin

May 21, 2017

በመስዋዕትነት የተሰበረው የሳንሱር ቀንበር

ኢብሳ ነመራ

የአሁኗ ኢትዮጵያ ትውልድ የማያውቀውን አንድ ጉዳይ በማስታወስ ልጀምር። ድሮ – ከሃያ ስድስት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፣ በድብቅ የሚነበቡ መጻህፍትና ሌሎች ጽሁፎች ነበሩ። አንዳንዶቹ መጽሃፍት በተዓምር አይመሬውን የማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴር የሳንሱር መቀስና እገዳ አልፈው ከታተሙ በኋላ እንዳይሰራጩ የተከለከሉ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ በውጭ ሃገር ቋንቋ የተጻፉ በሌላ ሃገር የታተሙ ናቸው። ጽሁፎቹ ደግሞ በድብቅ የሚታተሙና ውስጥ ለውስጥ የሚሰራጩ ናቸው።

የሳንሱርን አጥር ሾልከው ከታተሙትና ከተከለከሉት መሃከል በዘውዳዊው ስርአት ታትሞ የነበረውን የአቤ ጉበኛ አልወለድም ልቦለድ መጸሃፍ አስታውሳለሁ። በዚያን ጊዜ ለአቅመ ንባብ ባልበቃም፣ በኋላ መጽሃፉ እንዳይሰራጭ ታግዶ እንደነበረ ሲወራ ሰምቻለሁ። መጽሃፉንም ለማንበብ በቅቻለሁ። አልወለድም የስርአት ለውጥ ሲመጣ በድጋሚ ባይታተምም የስርጭት ገደቡ ግን ተነስቶ የነበረ ይመስለኛል። ታዲያ አልወለድም በግልጽ የዘውዳዊውን ሥርአት የሚያወግዝ ነገር አልነበረውም። መጽሃፉ የታገደው ደራሲው ይሄን ሲል ይህን ለማለት አስቦ ነው በሚል የሳንሱር አድራጊዎቹ ሰሜታዊ ትንታኔ ነው። ልብ በሉ የሳንሱር አጥርን መሻገር አቅቷቸው በታይፕ እንደተጻፉ በደራሲው ሳጥን ውስጥ የቀሩ እጅግ በርካቶች ናቸው። ደራሲያኑ የሚከተለውን በመፍራት ቀደሞውኑም ለሳንሱር ያላቀረቧቸውም እንዲሁ በርካቶች ናቸው።

በወታደራዊው ደርግ ስርአት የሳንሱርን አጥር ዘለው መታተም ቢችሉም የስርጭት እገዳን መሻገር ካቃታቸው መሃከል የአሁኑ ትውልድም የሚያውቀውን የበአሉ ግርማ ኦሮማይ ልቦለድ መጸሃፍ አስታውሳለሁ። ይህ መጸሃፍ በታተመበት 1975 ማገባደጃ ወደሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት የተሸጋገርኩበት ዘመን ሰለነበረ ብዙ ነገሮችን አስታውሳለሁ። በወቅቱ ታላላቆቼ 10 ብር ሰጥተው መጽሃፉን ፈልጌ እንድገዛ ልከውኝ ነበር። እነርሱ መታገዱን በጭምጭምታ ሰምተዋል፣ እኔ ደግሞ ይህን አልሰማሁም። ደራሲውን አውቀዋለሁ። ምናልባት አንድ ወይም ሁለት መጸሃፎቹን ሳላነብ የቀረሁም አይመስለኝም። ታዲያ በተላኩት መሰረት መርካቶ መጸሃፍ ተራ ሄጄ መጠየቅ ጀመረኩ። ያጋጠመኝ ነገር ከጠበኩት የተለየ ነበር። አብዛኞቹ መጻህፍት ሻጮች በጥርጣሬ ተመልክተው የጠየኩት መጸሃፍ እንደሌለ ሲነግሩኝ፤ ሌሎቹ ደግሞ ቆጣ ብለው “የለም!” የሉኛል።

ነገሩ ግራ አጋባኝ። መርካቶ ከ3ኛ ክፍል ጀምሬ የተማርኩበት፣ ትምህርት ቤት የሚገኝበት፣ ያደኩበት አካባቢ ነው። የመርካቶ ነጋዴዎችን ባህሪ በደንብ አውቃለሁ። በተለይ መጽሃፍ ተራ የመማሪያ መጸሃፍ በመግዛት፣ ተምሬ ያለፍኩትን በመሸጥም አውቀዋለሁ። ስገዛም ሰሸጥም “እኔ ጋር ና፣ አኔ ጋር” ብለው ተሻምተው አግባብተው ነበር የሚያስተናግዱኝ። የኦሮማይ መጽሃፍ የግዢ ጥያቄ ምላሽ ግን “ዞር በልልኝ!” የሚል ነበር። ግራ ያጋባበኝ ይህ ነው። መጨረሻ ላይ አንዱ ነጋዴ በሹክሹክታ “30 ብር ትገዛለህ?” ሲል ጠየቀኝ። እገዛበታለሁ በዬ ከገመትኩት 10 ብር ብእጅጉ የበዛ ዋጋ መጠየቄም አስገረመኝ። ይሄኔ ግን አንድ ነገር ገባኝ፤ መጽሃፉ እንዳይሸጥ መከልከሉን። በወቅቱ የሚከለከለው ነገር ብዙ ስለነበረ፣ መከልከሉ አልገረመኝም። የማንበብ ጉጉቴ ግን ጨመረ።

በዚህ ሁኔታ መዕሃፉን ሳልገዛ ተመልሼ ሁኔታውን ለታላለቆቼ አስረዳሁ። ቀድሞውኑ መከልከሉን ያውቁ ስለነበረ ምንም አላሉኝም። በነጋታው ግን 30 ብር ሰጥተው እንድገዛ ላኩኝ። በነጋታው በተመሳሰይ ሰአት ትላንት 30 ብር ጠይቆኝ የነበረው ነጋዴ ጋር ሄድኩ፤ የመግዛቱ ነገር ግን አልተሳካልኝም። ተመልሼ የመምጣቴ ነገር ስጋት አሳድሮበት ይመስለኛል፣ መጸሃፉ እንደሌለ ነገረኝ። ሌላ ነጋዴ ግን ጠጋ ብሎ በ80 ብር እገዛ እንደሆን ጠየቀኝ። በዚሀ ሁኔታ መጽሃፉን ሳልገዛ ተመለስኩ።

በኋላ ግን መጽሃፉ በየስርቻው በፎቶ ኮፒ ተባዝቶ ሰዎች ውስጥ ውስጡን እየተቀባበሉ ያነቡት ነበር። በስንት ልመና ወረፋ ጠብቄ መጽሃፉን በ1979 ዓ/ም መጨረሻ ላይ የማንበብ እድል አግኝቼያላሁ።

በድብቅ ከሚነበቡ የውጭ ሃገር መጻህፍት መሃከል የጆርጅ ኦርዌልን Animal Farm አስታውሳሉ። ይህች ትንሽዬ መጽሃፍ በድብቅ በፎቶ ኮፒ ተባዝታ ምንነቷ በማይታወቅበት ሁኔታ ተጠርዛ በድብቅ ከቦታ ቦታ፣ ከቤት ቤት እየተሽሎከሎከች ትነበብ እንደነበረ አስታውሳለሁ። እንግዲህ እነዚህን መጻህፍት ለአሰረጂነት አነሳሁ እንጂ የታገዱና ሳይታተሙ የቀሩ መጽሃፍት በርካቶች ናቸው።የሚገረመው ግንቦት 20፣ 1983 ዓ/ም የወታደራዊው ደርግ መንግስት ተወግዶ በጥቂት ወራት ውስጥ ኦሮማይና Animal Farm ገበያውን አጥለቅልቀውት ነበር። ባልሳሳት Animal Farm ወደአማርኛ ተተርጉሞ ታትሞ በ1984 ዓ/ም ሲሰራጭ ነበር።

ይህን የምተርክላችሁ የግል ገጠመኜን ላወጋችሁ አይደለም። በተለይ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ትውልድ ድሮ ሃሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት ምን ይመስል እንደነበረ ተጨባጭ አስረጂ እንዲኖረው ለማደረግ ያህል ያህል ነው።

ሃሳብን የመገለጽና ሃሳብን የመግለጽ ነዓነት እውን የሚሆንበት የፕሬስ ነጻነት ከመሰረታዊ ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ቀዳሚው ነው። ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት ባልተከበረበት ሁኔታ ዴሞክራሲ የማይጨበጥ ህልም ነው። የፈቀዱትን አመለካከትና ሃሳብ በነጻነት የመያዝ፣ የመግለጽ፣ የማራመድ መብት ባልተከበረበት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊደራጁ አይችሉም። ሃሳብን በነጻነት መግለጽ በማይቻልበት ሁኔታ የህዝብ በቸኛ የመንግስት ስልጣን ባለቤትነትና ምንጭነት የሚረጋገጥበትን ምርጫ ማካሄድ አይቻልም።

የወታደራዊው ደርግ መንግስት ግንቦት 20፣ 1983 ዓ/ም ተወግዶ በወሩ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩና በውጭ ሃገራት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንዲሁም ከደርግ መወገድ በኋላ በነበሩት ጥቂት ቀናት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት ጉባኤ የሽግግር መንግስት ተመሰረተ። የሽግግር መንግስቱ ዋና ተልዕኮ ህገመንግስት መቅረጽ ነበር። የሽግግር መንግስቱ እንደ ህገመንግስት ሲመራበት የነበረው “የሽግግር መንግስት ቻርተር” የተባለ ሰነድም ነበረው። ይህ ቻርተር በሁሉም የኢትዮጵያ ሃይሎች ስምምነት የጸደቀ ነበር።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀዱትን አመለካካትና ሃሳብ የመያዝ፣ የመግለጽ (የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ)፣ በአመለካካት የመደራጀትና አመለካካትን የማራመድ፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመወዳደር፣ . . . መብቶችና ነጻነቶች የተረጋገጡት በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ነበር። በዚህ ቻርተር መሰረት የፕሬስ ነጻነት አዋጅ ጸደቀ፤ በ1984 ዓ/ም። በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋጅ የተረጋገጠው በዚህ የ1984 ዓ/ም አዋጅ ነበር። ይህ አዋጅ መጽሃፍትን ጨምሮ የፕሬስ ውጤቶች ላይ የነበረውን ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) አነሳ። የግንቦት 20 ድል ይህን አዲስ ነገር አስገኘ።

የፕሬስ ነጻነት አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በርካታ መጽሄቶችና ጋዜጦች ታትመው ይሰራጩ ጀመር። ህዝቡም የመረጃ ጥማቱን ያህል እየተሻማ እየገዛ አነበባቸው። ከቅድመ ምርመራ ውጭ ሲታተሙ ከነበሩት መጽሄቶችና ጋዜጦች መሃከል የህዝቡን ስነምግባር የጣሰ ልቅ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውም ነበሩበት። ህዘቡ፣ በተለይ እነዚህ የተሰጣቸውን ነጻነት ያለአግባብ በተጠቀሙ የፕሬስ ውጤቶች ላይ አደባበይ ወጥቶ ተቃውሞውን ገልጾ እንደነበረም ይታወሳል። ከዚህ በተረፈ እጅግ ያሳዝን የነበረው፣ በመጀመሪያ ይህን የፕሬስ ነጻነት የተጠቀሙት፣ ነጻነቱን አግዶ የነበረውን አፋኝ ስርአት ሲያገለግሉ የነበሩ ካድሬዎችና ወታደራዊ መኮንኖች የነበሩ መሆኑ ነው። እነዚህ ካድሬዎችና ወታደራዊ መኮንኖች የፕሬስ ነጻነትን፤ ጅምሩን የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ለማጎልበት፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ ልማትን ለማቀላጠፍ በሚያስችል አኳኋን ከመጠቀም ይልቅ ነጻነቱን ያረጋገጠውን ስርአት ለማፍረስ ዓላማ ነበር የተጠቀሙበት። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፐሬስ አበቃቀል ላይ እስካሁንም በግልጽ የሚታይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል የሚል እምነት አለኝ።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅድመ ምርመራ ውጭ መጽሃፍት ታትመው መሰራጨት የጀመሩትም በዚህ ወቅት ነበር። የመድረክ ቲያትሮች፣ ዘፈኖች ወዘተ የመሳሰሉ የጥበብ ስራዎችም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሳንሱር ቀንበር ነጻ ሆኑ። በዚህም በርካታ መጻህፍት ታትመው የመሰራጨት እድል አግኝተዋል፣ ቲያትሮች ለመደረክ ቀርበዋል። ይህ የግንቦት 20 ድል ውጤት ነው።

የሽግግር መንግስቱ በህዝብ ተሳትፎ የኢፌዴሪ ህገመንግስትን አጽድቆ የሽግግር መንግስቱ በህዝብ ውክልና ስልጣን ለተሰጠው የኢፌዴሪ መንግስት ሥፍራውን ለቀቀ። በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው ሃሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት፣ የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝና አመለካካትን ከመሰሎች ጋር ተደራጅቶም ይሁን በግል የማራመድ፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ የመደራጀት፣ ዴሞክራሲያዊ መበቶችና ነጻነቶች በኢፌዴሪ ህገመንግስት ተረጋገጡ።

በዚህ መሰረት በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በይፋ አቋማቸውን ሲያራምዱ ቆይተዋል። በርካታ የፕሬስ ወጤቶች ታትመው ሲሰራጩ ቆይተዋል። በሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ እድሜ ውስጥ አንጋፋ ለመባል የበቁ የግል ጋዜጦች ተፈጥረዋል። በእነዚህ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች በመስራት ላይ ይገኛሉ። ባለፉት አስር አመታት ደግሞ የግል ሬደዮ ጣቢያዎች ተስፋፍተዋል።

እነዚህ የግል ፕሬሶች የተለያዩ አመለካከቶችን አስተናግደዋል። ህጋዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእነዚህ የፕሬስ ውጤቶች አማካኝነት አቋማቸውን ሲገልጹ፣ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። አሁንም ይህን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እውነቱን ለመናገር የግል የፕሬስ ወጤቶች ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ይልቅ ምናልባት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቋም  ሲያንጸባርቁ ነው የቆዩት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንዳንድ በግል ፕሬስነት የተደራጁ ሚዲያዎች ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ በይፋ አወጀው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም ማራመጃ ሆነው ያገለገሉበት ሁኔታ እንደነበረም ይታወቃል። ከእነዚህ ጋዜጦችና መጽሄቶች መሃከል የተወሰኑት አዘጋጆች ህግ በሚፈቅደው መሰረት ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ሁኔታው በሆደ ሰፊነት የታለፉበት ሁኔታ የሚያዘነብል ሆኖ ይሰማኛል።

ያም ሆነ ይህ አሁን ኢትዮጵያ ማንኛውም ግለሰብ፣ ወይም ድርጅት ሃሳቡን በነጻነት የሚገልጽባት ሃገር ነች። የጽንፈኛ ተቃዋሚነት አቋሞችን የሚያንጸባርቁ መጻህፍት ጭምር ያለምንም ቅድመ ምርመራ፣ ያለምንም የሽያጭ ገደብ በይፋ ታትመው የሚሰራጩባት ሃገር ነች። የመጽሃፍት ገበያውን መመልከት ለዚህ በቂ አሰረጂ ነው። አሁን እንደ በአሉ ግርማ ኦሮማይ መጽሃፍት እንዳይሰራጩ የሚከለከልበት፣ መጽሃፍት ብድብቅ የሚነበቡበት ጊዜ አይደለም።  ይህ የግንቦት 20 ድል ወጤት ነው። በነጻ የተገኘ ሳይሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የህይወት መስዋእትነት የተገኘ ውጤት ነው። የሳንሱር ቀንበር በግንቦት 20 ድል ተሰብሯል።