የሕብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።
ጊፍት ሪል ስቴት ከ850 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመንደር ቁጥር ሁለት የገነባቸውን ቤቶች ዛሬ ለደንበኞቹ አስተላልፏል።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ በቤቶቹ ምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ የመኖሪያ ቤት የመጠለያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ሃገራቸው ላይ ማግኘት የሚገባቸው ሁለንተናዊ የደህንነት ዋስትና ነው።
በመሆኑም መንግስት በያዘው የቤት ልማት መርሃ ግብር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ከመቶ ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አባዎራዎች ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም በሪል ስቴት ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ለግንባታ የሚሆን መሬት ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ ነው ብለዋል።
ባለሃብቶችም ዕድሉን ተጠቅመው የስራ እድል ከመፍጠርና ምቹ መኖሪያዎችን ገንብቶ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነም ገልጸዋል።
በተቃራኒው ቃል በገቡት ፍጥነትና ጥራት ቤቶቹን ካለማቅረብ ጀምሮ የደንበኞችን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ ህገ ወጦች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ህገወጥ ተግባሩን በሚፈፅሙት ላይ መንግስት ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በሃላፊነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ጊፍት ሪል ስቴት ዛሬ ለደንበኞቹ ያስተላለፋቸው ቤቶች፥ በ90 ሺህ 229 ካሬሜትር መሬት ላይ ያረፉ ሲሆን 350 የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ቪላና አፓርታማ ናቸው።
በፕሮጀክቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ድርጅቱን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።