NEWS

በመዲናዋ 128 የጤና ተቋማት እርምጃ ተወሰደባቸው

By Admin

May 03, 2017

በያዝነው አመት ከደረጃ በላይ እና በታች አገልግሎት ሲሰጡ በተገኙ 128 የጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድሃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ በባለሙያዎች፣ የፋርማሲ ቤቶች እና የጤና ተቋማት ላይ የኦዲት ፍተሻ በማድረግ ነው እርምጃውን የወሰደው።

በ100 የመድሃኒት ቤቶች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻም 12ቱ ላይ ምንጫቸው ያልታወቁ እና የአገልግሎት መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች ይዘው በመገኘታቸው ከአገልግሎት እንዲታገዱ ተደርጓል ብለዋል የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ።

ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ 1 ሺህ 17 ተቋማት ላይ የኦዲት ስራ ማከናወኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በመደበኛ እና ድንገተኛ ፍተሻውም በርካታ የጤና ተቋማት ላይ የአሰራር ግድፈቶች መሰተዋላቸውን አንስተዋል።

በ758 የመድሃኒት ቤቶች ላይ በተደረገ ኦዲት 72 የመድሃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች የአሰራር ግድፈት ተገኝቶባቸዋል።

በዚህም ከአንድ አመት ጀምሮ እስከ ሙሉ በሙሉ ፍቃድ ማገድ የደረሰ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው።

በተደረገው ፈተሻ በመዲናዋ ከሚገኙ 1 ሺህ 17 የጤና ተቋማት ውስጥ 462 ያህሉ ባለሙያዎችን ያላሟሉ መሆናቸው መረጋገጡንም ገልፀዋል።

በከተማዋ ከ30 ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ የሚለው ባለስልጣኑ፥ በየአምስት አመቱ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እድሳት እንዲያከናውኑ መመሪያው እንደሚያዝ አስታውሷል።

ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ ባካሄደው ኦዲት የሙያ ምስክር ወረቀትም ሆነ የሙያ ፍቃድ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ሲሰሩ የተገኙ በርካታ ናቸው ነው ያሉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር።

ባለሰልጣኑ እንዲህ ባለው ተግባር ላይ ተሰማርተው በተገኙ ባለሙያዎች ላይ እና ሲያሰሩ በተገኙ ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ለህግ የማቅረብ የደረሰ እርምጃ መውሰዱን አቶ ጌታቸው ወረቲ ተናግረዋል።