Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖቻችን ጉዳይ አሳስቦናል!

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖቻችን ጉዳይ አሳስቦናል!

ሰለሞን ሽፈራው

ድህነትና ኋላቀርነት ከሚገለፅባቸው አሳፋሪ ገፅታዎች መካከል ከራስ ሀገር ወገን እጅግ በጣም ርቆ መሄድን የሚጠይቀው የስደት ህይወት አንዱ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ምክንያቱም፤የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከመፈለግ በሚመነጭ ውስጣዊ ግፊት ተወልደው ካደጉበት ቀየ እጅግ ወደራቀ ባዕድ ሀገር ከተሰደዱ በኋላ ሊያጋጥም የሚችለውን ፈርጀ ብዙ ፈተና ማለፍ ምንኛ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ገፅታ እንዳለው የሚያውቅ ያውቀዋልና ነው፡፡

ይልቁንም ደግሞ ሕጋዊ መንገድን ባልተከተለ መልኩ የሚደረግ የሰዎች ፍልሰት ወይም ስደት የዘመናችን እጅግ አሰቃቂ ክስተት ከመሆኑ የተነሳ መላውን የዓለም ማህበረሰብ አንገት  እያስደፋ እንደሚገኝ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣ  ከሚነገርለት ሕገ ወጥ ስደት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አሰቃቂ የባህር ላይ አደጋዎች የዕለት ተዕለት ዓለም አቀፋዊ ዜና የሆኑበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡

ከዚህም ባሻገር፤የወቅቱ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢ የፀጥታ ስጋት ምንጭ ተደርጎ ከተወሰደ የሰነባበተውን የሽብር ፈጣሪ ቡድኖች አደገኛ እንቅስቃሴ ይበልጥ በማባባስ ረገድ ሕገወጥ ስደት የማይናቅ አሉታዊ  አስተዋፅኦ  እያበራከተ ነው ተብሎ በመታመኑ ምክንያት፤ጉዳዩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ወደሚያሰኝ ውስብስብ ችግርነት እየተቀየረ ስለመምጣቱ ተደጋግሞ ሲነሳ የሚደመጥ የመነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል፡፡ እናም ከዚሁ የዘመናችን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ መገለጫ ተደርጎ ሊቆጠር ከሚችል አጠቃላይ እውነታ አኳያ ሀገራችን ኢትዮጵያም የተጠቃሾቹ ችግሮች ገፈት ቀማሽ የሆነችበት አግባብ መኖሩ እምብዛም የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡

ይህን ስንልም ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ከትናንቱ የጦርነትና ዕርስ በርስ የመናቆር አሳዛኝ ታሪካችን በወረስነው እጅጉን ስር የሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ምክንያት፤አሁንም ድረስ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሀገራቸውን ጥለው በባሌም፤በቦሌም የሚሰደዱ ዜጎቻችን ቁጥር  ጥቂት እንዳልሆነ መጠቆማችን ነው፡፡ በተለይም ሕጋዊውን መንገድ ባልተከተለ መልኩ ከሀገር እየወጡ የተሻለ ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ወደ ተጣለበት የዓለማችን ክፍል ሁሉ ለመሰደድ የሚሞከርበት አግባብ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አሰቃቂ አሟሟት ምክንያት ሲሆን የሚሰተዋልበት አጋጣሚ እየተበራከተ ስለመምጣቱ ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እናም ከዚህ የዘመናችንን ዓለም ጭምር በእጅጉ እየተፈተነ ካለው ሕገ ወጥ የሰዎች ፍልሰት (ስደት) ጋር በተያያዘ መልኩ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ከፈርጀ ብዙ የድህነትና የኋላ ቀርነት ድቅድቅ ጨለማ  ለመውጣት የሞት ሽረት ትግል በማካሄድ ላይ የምትገኝ አፍሪካዊ ሀገር የሚመለከታት ተጨባጭ ችግር መኖሩ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም ካልን ዘንዳ፤ችግሩ ጎላ ባለገፅታው ስለሚስተዋልባቸው መንገዶች ለአብነት ያህል አንስተን ማየት ይጠበቅብናል ባይ ነኝ እኔ፡፡እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ የማልፈውም፤የዚህ ፅሁፌ ዋነኛ ትኩረት ወደ ሆነው ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ  በሚገኙና ግን ደግሞ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም ተብለው ከዚያች ሀገር እንዲወጡ ቀነ ገደብ በተቀመጠላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ስለተደቀነባቸው አሳሳቢ ችግር ወደ ማነሳበት ነጥብ ይሆናል፡፡

ስለዚህም “ከሕገ ወጥ ስደተኞች የፀዳች ሳዑዲ ዓረቢያን ማየት” በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ እቅድ ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ለመላው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ያሳወቀው የሪያዱ ንጉሳዊ መንግስት፤ በዚያች አገር ውስጥ ስለሚገኙት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ይፋ ያደረገውን ቅድመ ሁኔታ ተከትሎ ጉዳዩ በስፋት እያነጋገረ  ስለመሆኑና ይልቁንም ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች የውሳኔው ሰለባ የመሆን ዕጣ ስለሚገጥማቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ደህንነት እያሰብን ስንጨነቅ መሰንበታችን ይታወሳል፡፡ ምንም አንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ገና ዜናው ከመሰማቱ ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሳዑዲት ዓረቢያ ተጉዞ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የዚያች ሀገር መንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር፤ዜጎቻችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ስለሚችሉበት  አግባብ ዲፕሎማሲያዊ ምክክር እንዲያደርግ ያደረገበት ጥረት መኖሩንና ለዚሁ ተግባር የተቋቋመ ግብረ ሃይል እንዳለ ብንረዳም፤የችግሩ ሰለባዎች የመሆን አደጋ የተጋረጠባቸው ወገኖቻችን አሁንም ድረስ የነቁ አለመምሰላቸው ግን ያሳስበናል፡፡

ስለሆነም፤የሳዑዲ ዓረቢያው መንግስት “ማንኛውም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው የውጭ ሀገር ዜጋ በዘጠና ቀናት ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ሰርቶ ያፈራውን ሀብት ንብረት እየያዘ በይፋዊ የአውሮፕላን ጉዞ ወደ የመጣበት ሀገር እንዲመልሰው እድል ሰጥተናል”ሲል ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት (ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ነውና የቀረው)እዚያ የሚገኙት ወገኖቻችን ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እየሰጡ ራሳቸውን ኋላ ሊከተል ከሚችለው ፈርጀ  ብዙ ጉዳት እንዲታደጉ የማድረግ ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ድምፃችንን ማሰማት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ደግሞ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ እየተሰደዱ የባለ ፀጋ ዓረቦችን የቤት እንሳስት (በግ፤ፍየልና ከብት) በማገድ የእረኝነት ተግባር ላይ ከመሰማራት ውጭ ሌላ  አማራጭ ዕድል የሌላቸው አድርገው የሚቆጥሩት እጅግ በርካታ ወጣት አርሶ አደር ወገኖቻችን ጉዳይ ይበልጥ የሚያሳስብ ሆኖ ነው ለኔ የሚሰማኝ፡፡ይሄን ስልም ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፡፡

ይልቅስ አብዛኛዎቹ በሕገ ወጥ የባህር ላይ ጉዞ ህንድ ውቅያኖስን እንደምንም እየተሸገሩ ወደ ሳዑዲት ዓረቢያ ዘልቀው የሚገቡት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከገጠሩ የሀገራችን ክፍል የሚሔዱና ምናልባትም ፊደል የመቁጠር ዕድል ያልገጠማቸውም ጭምር ከመሆናቸው ተነሳ፤ እዚያ ሔደው የሚሰማሩበት የስራ መስክ ከከተማ ርቀው እንዲኖሩ የሚያስገድድ እንደሆነ ሲነገር ሰምቻለሁና ነው፡፡ ስለዚህም እንደኔ እንደኔ የሳዑዲ ዓረቢያው መንግስት በ90 ቀናት ውስጥ ያቺን ሀገር ለቅቀው ባልወጡት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ላይ እወስዳለሁ ሲል ያስቀመጠው ቅድመ-ሁኔታ ይዘት በተለይም ለእረኝነትና ለመሰል የመስክ ስራ ከከተሞቻቸው ርቀው እንዲሔዱ የሚገደዱትን ወገኖቻችንን ተደራሽ ባደረገ የመረጃ ስርጭት ዘዴ ታግዞ መቅረብ አለመቅረቡን የማረጋገጥ ተግባር ከኛ መንግስት አካላት የሚጠበቅ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

ይህን የምልበት ምክንያትም፤ በተለይም በ2007ዓ/ም የተከሰተውን የዝናብ እጥረትና እንዲሁም ደግሞ የድርቅ አደጋ ተከትሎ፤ ሕጋዊ ባልሆነ የባህር ላይ ጉዞ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የተሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣት አረሶ አደሮች አሁንም ድረስ እዚያው እንደሚገኙ የሚያመለክቱ መረጃዎች ስለመኖራቸው የተረዳሁበትአግባብ ስላለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔ ራሴ ተወልጄ ካደኩበት የገጠሪቱ ኢትዮጵያ አንድ አካባቢ ብቻ የ2007ቱን ድርቅ ተከትሎ ቤት ትዳራቸውን ለሚስቶቻቸው እየተው የባለ ፀጋዎቹን ዓረቦች በግና ፍየል አግደው የሚያገኙትን ገንዘብ ለማምጣት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መሰደድን የመረጡት ወጣት አርሶ አደሮች ጥቂት እንዳልሆኑ አውቃለሁ፡፡

ከነዚሁ ወገኖች መካከል፤በጣም የቅርብ ቤተሰቦቼ ልጆች ጭምር እንዳሉበትና አሁንም ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዳልተመለሱ ማረጋገጤንም ልብ ትሉልኝ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡ ስለሆነም የአብዛኛዎቹ ወጣት አርሶ አደሮች የትዳር አጋሮችን ጨምሮ መላው ቤተሰባቸው ከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ላይ ከወደቀ ወራት ተቆጥረዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ከሳዑዲ ዓረቢያው ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለማባረር፤አልያም ደግሞ፤ሰርተው ያገኟትን ሀብት ንብረት እየተወረሱ ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩና ፈርጀ ብዙ ቅጣት እንዲፈፀምባቸው ለማድረግ ያለመ ሰሞነኛ ዜና ጋር በተያያዘ  ምክንያት የተፈጠረ ስጋትና ጭንቀት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የስደተኛ ዜጎቻችን ቤተሰቦችን ሁሉ የሚያካትት እንጂ የኛ አካባቢ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡

መቸስ የሳዑዲ ዓረቢያም ሆነ የሌላ የማንኛውም ልዑዋላዊ ሀገር መንግስት፤ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች አስወጣለሁ ካለ የሚያግደው ምክንያት እንደሌለ እኔም እገነዘባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ግን እርምጃው እንብዛም ፈር በለቀቀና “የማያቀባብር” የህዝብ ለህዝብ ቅያሜን ሊያስከትል በሚችል የጭካኔ ስሜት የሚገለፅ ዓይነት  መሆን እንደማይኖርበት የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ስለዚህ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማስተላለፍ የሚጠበቅብኝ መልዕክት ሆኖ የሚሰማኝም፤ የኢፌዴሪ መንግስት፤የክልል መስተዳደሮችና እንዲሁም ደግሞ መላው የሀገራችን ህብረሰብም ጭምር እጅ ለእጅ ተያይዘው በመንቀሳቀስ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙት የእርምጃው ኢላማዎች የተደረጉ ወገኖቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ያልተገባ ቅጣትና እንግልት የሚያስቀር አንዳች መፍትሔ ማፈላለግ ይኖርባቸዋል የሚለውን ነው፡፡

አለበለዚያ ግን፤ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ያለፈቃድ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መካከል 20 ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው እስካሁን እድሉን ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ዝግጁ የሆኑት የሚለው ዜና ምንን እንደሚያመለክት ከወዲሁ ልብ ማለት ይጠበቅብናል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የባለ ፀጋዋ ዓረባዊት ሀገር መንግስት፤ያስቀመጠው የሶስት ወር የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ ለሚጀምረው ሕገ ወጥ ስደተኞችን እያደነና እያሳደደ የመያዝ እርምጃው ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ ዘጠኝ መቶ ያህል አዳዲስ እስር ቤት ገንብቶ እንደጨረሰም ጭምር ራሱው ነግሮናልና ነው፡፡ስለዚህ ያልፍልን ይሆናል ከሚል ተስፋ በመነጨ ድፍረት አደገኛውን የባህር ላይ ጉዞ አቋርጠው ሳዑዲ ዓረቢያ የገቡና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን በሰው ሀገር እስር ቤቶች ከመታጎር የመታደጉ ሃላፊነት እዚህ ባለነው ዜጎች ጫንቃ ላይ የወደቀ ሸክም እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተረፈ ግን የኢትዮጵያ አምላክ ረድኤቱን አይንፈጋቸው፡፡ አሜን!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy