በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎችን የመታገል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት፥ ከሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ አባላት የተውጣጡ እና የግንቦት 20 የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ፥ በክልሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ጉብኝት እያደረጉ ካሉ ምሁራን ጋር በነበራቸው ውይይት ነው፡፡
አቶ አባይ ከጎብኝዎቹ ጋር ባረጉት ውይይት የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ህዝብ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ የሚነዛው የተሳሳተ ሀሳብ፥ መሰረተ ቢስ እና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ሲባል ተቀነባብሮ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማምጣት ለከፈለው መስዋዕትነት ልዩ ተጠቃሚነት ሳይጠይቅ፥ እንደማንኛውም የሀገሪቱ ሕዝብ ራሱን ለማልማትና በስራው ልክ በመልማት እየተጠቀመ ያለ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት፡፡
አቶ አባይ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚነዛውን የሀሰት መረጃ ለማስቀረት፥ መፍትሔው እውነታውን መግለጽ እና በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ኪራይ ሰብሳቢዎችን መታገል ነው ብለዋል፡፡
ጎብኝዎቹ በበኩላቸው የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ለሰላምና ለዴሞክራሲ የከፈለው መስዋዕትነት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በክልሉ ያሉት የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
በሙሉጌታ አፅባሓ