NEWS

በኢሬቻ በዓል ላይ ሁከት በማስነሳት ለ55 ሰዎች ሞት ምክንያት ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

By Admin

May 26, 2017

በኢሬቻ በዓል ላይ ከሃገር ሽማግሌዎች ማይክ በመቀማትና ሁከት በማስነሳት ለ55 ሰዎች ሞት ምክንያት ናቸው የተባሉት ሁለት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተባቸው።

ተከሳሾች ቱፋ መልካ እና ከድር በዳሶ ሲሆኑ፥ ክሱ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቀረበባቸው።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው፥ 1ኛ ተከሳሽ ቱፋ መልካ በኢሬቻ በዓል ወቅት የሃገር ሽማግሌዎች ንግግር ሲያደርጉ ማይክ በመቀማት ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር በዓሉን አደናቅፏል።

2ኛ ተከሳሽ ከድር በዳሶ በበኩሉ ከመድረክ ጀርባ በመሆን በስልክ አመፁን ሲያስተባብር እንደነበር የአቃቢ ህግ ክስ ያስረዳል።

ተከሳሾቹ በወቅቱ በበዓሉ በተፈጠረው ግርግር ህይወታቸው ላለፈ 55 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆናቸውም በክሱ ተዘርዝሯል።

ከሳሽ አቃቢ ህግም የሽብር ወንጀል ድርጊት በመፈጸም ክስ አቅርቦባቸዋል

ተከሳሾቹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው ተነቦላቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያ ለመስማትም ለግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።